ዶናልድ ትረምፕ የፕሬዚዳንትነት ሥልጣን ዳግም እየተረከቡ ነው
ዶናልድ ትረምፕ ዛሬ ሰኞ ዋሽንግተን ውስጥ በሚካሄድ በዓለ ሲመት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንትነት ሥልጣናቸው ይመለሳሉ፡፡ ይህ እ.ኤ.አ. ከ1890ዎቹ ወዲህ ተከታታይ ባልሆነ የስልጣን ዘመን ያገለገሉ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ያደርጋቸዋል፡፡
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን፣ የ78 ዓመቱ ትረምፕ ለአዲሱ የአራት ዓመት የስልጣን ዘመን በዋይት ሀውስ ቃለ መሃላ ሲፈፅሙ ፣ የ82 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ደግሞ ከአንድ የስልጣን ዘመን በኋላ የፕሬዚዳንትነቱን ቦታ ሲለቁ፣ በቴሌቭዥን ይከታተላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የበዓለ ሲመቱ በተፈጠረው ቅዝቃዜ ምክንያት ከታቀደው አነስ ባሉ ታዳሚዎች ይካሄዳል፡፡ እንደወትሮው በመስክ ላይ በሚደረገው ዝግጅት ለመገኘት ትኬት የነበራቸው 250,000 ሰዎች ሲሆኑ፣ ከውጭ ወደ ምክር ቤቱ ህንጻ ውስጥ በተዛወረው በዓለ ሲመት በአካል የሚታደሙ ወደ 600 የሚጠጉ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡
የፔንሰልቬንያ ጎዳናን ይዞ ከምክር ቤቱ እስከ ዋይት ሐውስ ድረስ ይደረግ የነበረው ባህላዊ የመክፈቻ ሰልፍ በአየር ሁኔታ ለውጥ ምክንያት ተሰርዟል፡፡ ዛሬ ባንዶች ፣ የሰልፈኞች ቡድን ፣ የወታደራዊ እና የመሳሰሉ ትርኢቶችን የሚያሳዩ ሰልፈኞች 20,000 መቀመጫዎች ባሉት (Capital One Arena በተባለው) ሁለገብ የቤት ውስጥ አዳራሽ ትረምፕ፣ ባለቤታቸው ሜላኒያ ትራምፕ እና በአዲሱ አስተዳደር በተካቱት ሌሎች ባለስልጣናት ፊት ያልፋሉ ። ዛሬ ሰኞ ምሽት ላይ ትላልቅ ግብዣዎች ይካሄዳሉ፡፡
ትረምፕ ትላንት እሁድ አመሻሹ ላይ በዋሽንግተን ውስጥ ለደጋፊዎቻቸው እንደተናገሩት “ሀገራችን የገጠማትን እያንዳንዱን ችግር ሁሉ ለማስተካከል በታሪካዊ ፍጥነት እና ጥንካሬ” እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።
«ነገ እኩለ ቀን ላይ አሜሪካ የወደቀበችበት የአራት ረጅም ዓመታት መጋረጃ ይዘጋና አዲስ የአሜሪካ ጥንካሬ እና የብልጽግና ቀን እንጀምራለን» ሲሉም አክለዋል ትረምፕ በትላንቱ ንግግራቸው።
ወደ ቢሮ እንደተመለሱ የሚሻሩትን የባይደን አስተዳደር ፖሊሲዎችን ጨምሮ ብዙ የስራ አስፈፃሚ ትዕዛዞችን ለመፈረም ቃል ገብተዋል። በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ከገቡት ቃል መካከል ጎልቶ የታየው በሀገሪቱ በህገ ወጥ መንገድ የሚገኙ ዜጎችን በብዛት ማባረር ነበር።
ትረምፕ ካናዳ፣ ቻይና እና ሜክሲኮን ጨምሮ ቁልፍ በሆኑ የንግድ አጋሮች ላይ ወዲያውኑ ጠበቁ ያለ ታሪፎችን ለመጣል ቃል ገብተዋል።
መጪው ፕሬዚደንት እ.ኤ.አ ጥር 6፣ 2021 እኤአ በ2020 ምርጫ ባይደን ማሸነፋቸውን ምክር ቤቱ እንዳያረጋግጥ ለማገድ የምክር ቤቱን ህንፃ ከወረሩት 1,500 ደጋፊዎቻቸው መካከል፣ ለብዙዎቹ ይቅርታ ለማድረግ ማቀዳቸውንም ተናግረዋል፡፡ ትረምፕ ያለ አግባብ ክስ ቀርቦባቸዋል ያሏቸውን በቁጥጥር ስር የዋሉትን እና የተፈረደባቸውን «አርበኞች» እና «ታጋቾች» ብለዋቸዋል፡፡
ሪፐብሊካኑ ትረምፕ ባይደን እ.ኤ.አ. ያገኙትን የ2020 ምርጫ ውጤት በህገ ወጥ መንገድ ለመቀልበስ ሞክረዋል የሚለው ክስ ተቋርጧል፡፡ ክሱ የተቋረጠው ትረምፕ የዲሞክራቲክ ተቀናቃኛቸውን ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስን በ2024 ምርጫ በማሸነፋቸው ሥልጣን ላይ ያሉ ፕሬዚዳንቶች አይከሰሱም በሚለው በፍትህ ሚኒስቴር ፖሊሲ ምክንያት ነው።
ትረምፕ ባለፈው ዓመት ለወሲብ ፊልም ተዋናይ ስቶርሚ ዳንኤልን የተከፈለውን የ130,000 ዶላር የአፍ ማስያዣ ገንዘብ ለመደበቅ የቢዝነስ ሰነድ አጭበርብረዋል በሚል ተከሰዋል፡፡ በዚሁ ክስ በ34 የወንጀል ክሶች ጥፋተኛ ተብለው ከተፈረደባቸው በኋላ ምንም እንኳ ዳኛው እንደማይቀጧቸው ቢያሳውቁም ፣ በወንጀል የተፈረደባቸው የመጀመሪያው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ይሆናሉ።
ትረምፕ ስልጣን ከመረከባቸው በፊት ለወራት ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታደርገውን ጦርነት ለማስቆም ቃል ገብተዋል፡፡ ከቅርብ ቀናት ወዲህ ግን ረዳቶቻቸው በአስተዳደሩ የመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት በሚያዝያ ወር መጨረሻ ላይ ጦርነቱ ለማስቆም ከሰላም ስምምነት ለመድረስ መሞከር ነው ብለዋል ።
ምንም እንኳን እ.ኤ.አ. በ 2023 የአሜሪካ የኃይል አቅርቦት ምርት ከተመዘገበው መጠን በላይ ቢሆንም ትረምፕ አሜሪካ ውስጥ ተጨማሪ የነዳጅ ቁፋሮ እንዲደረግ ይፈልጋሉ ።
በውልደት ከነበራቸው ጾታ የተለየ የጾታ ማንነት የወሰዱ ሰዎችን የሚመለከቱ ሁለት ጉዳዮችም የትረምፕን ትኩረት ስበዋል።
ትረምፕ በውልደት የነበራቸውን ጾታቸውን ከወንድ ወደ ሴት የቀየሩ ሴቶችን እንደ ወንድ ደጋግመው በመጥቀስ ጾታቸውን የቀየሩት በሴቶች ስፖርት ውድድር ውስጥ መሳተፍ እንደማይችሉ እንደሚያረጋግጡ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል፡፡
ትረምፕ በአንድ የምርጫ ቅሰቀሳ መድረካቸው “ (ሥልጣን ከያዝኩበት) ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ወንዶች መቶ በመቶ በሴቶች ስፖርቶች እንዳይሳተፉ አደርጋለሁ” ብለዋል ። በተጨማሪም በውልደት ከነበራቸው ጾታ የተለየ የጾታ ማንነት ለወሰዱ ሰዎች የሚደረግ የጤና እንክብካቤን ብዙ ጊዜ ተቃውመዋል፡፡ «ሥልጣን በያዝኩበት የመጀመሪያው ቀን 'በውልደት ከነበራቸው ጾታ የተለየ የጾታ ማንነት ለወሰዱ ሰዎች የሚደረግ የተባለውን የጆ ባይደንን የጤና እንክብካቤን' መጥፎ ፖሊሲ እሽራለሁ።» ብለዋል፡፡