ባለፈው ዓመት በዓለም እጅግ አውዳሚ መሆኑ የተነገረለት የአሸባሪዎች ጥቃት በአፍሪካ ሲፈፀም፤ የዓለም የምጣኔ ሃብት እና የሰላም ተቋም ይፋ ያደረገው የ2025 የዓለም አቀፍ የሽብር ጥቃቶች ጠቋሚ ሪፖርት እንዳመለከተው፤ በአጠቃላይ ከሽብር ጋር ከተዛመዱ ግድያዎች ከገሚስ በላይ የሚሆኑት የተፈጸሙት የዓለም አቀፍ የሽብር ጥቃቶች መናሃሪያ ሆኖ በቆየው የሳሕል ክልል ነው። በሁለት ሀገራት የደረሱትን 3 አደገኛ የሽብር ጥቃቶች ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ከተዘገቡት 20 ያህል እጅግ የከፉ ጥቃቶች ውስጥም 17ቱ የተፈጸሙት በአፍሪካ ነው። ባለፈው ዓመት በሰኔ፣ በሀምሌ እና በነሀሴ ወር በኒጀር እና ቡርኪና ፋሶ የተፈጸሙት ጥቃቶች ለ607 ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክኒያት መሆናቸውን አክሎ ዋና መሥሪያ ቤቱን በአውስትራሊያ ያደረገው ይሄው የጥናት ቡድን አረጋግጧል። በዚሁ ዓመት በሳህል ክልል ከግጭቶች ጋር ተያይዘው የደረሱ ሞቶች ቁጥር ከ25,000 በላይ ሰዎች የጠፋባቸው ድንገቶች ዓመታዊው ጥናታዊ ሪፖርት ይፋ መደረግ ከጀመረ ወዲህ ከተዘገቡት ሁሉ እጅግ ግዙፍ መሆኑ እና ከእነዚህም ውስጥ 3,885 ያህሉ በአሸባሪዎች የተፈጸሙ መሆናቸው ተመልክቷል። በመሰል የአሸባሪዎች ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ሃገራት ቀዳሚዋ ቡርኪና ፋሶ ስትሆን፤ ብርቱ ጉዳት ከደረሰባቸው ጥቂት የአፍሪካ ሀገሮች ማሊ፣ ኒጀር፣ ናይጄሪያ፣ ሶማሊያ እና ካሜሩን እንደሚገኙባቸው ታውቋል። ቡርኪና ፋሶ በዘገባዎች እንደተገለጸው ክፉኛ የተጎዳች ሀገር ብትሆንም፤ አጠቃላይ የጥቃት እና የሟቾች መጠን የሚያመለክቱ አሃዞች በጠቅላላው በ21 በመቶ እና በ57 ቀንሰዋል። ያም ሆኖ ቡርኪና አሁንም በአለም አቀፍ ደረጃ በአሸባሪዎች በሚደርሱ ጥቃቶች የከፋ አደጋ ከሚደርስባቸው አምስተኛዋ አገር ነች። በዓመቱ ውስጥ ቢያንስ አንድ የሽብር ጥቃት የደረሰባቸው ሀገራት ቁጥር ከ58 ወደ 66 ከፍ ማለቱንም ሪፖርት አክሎ አስፍሯል። ከዚህም ውስጥ ከእስላማዊው ጽንፈኛ ቡድን አይሲስ ጋር ቁርኝት ያላቸው ቡድኖች በዓለም ዙሪያ በ22 የተለያዩ አገሮች ውስጥ ባደረሷቸው የሽብር ጥቃቶች 1, 805 ሰዎች ተገድለዋል። በሌላ በኩል እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2024 በሽብርተኞች የተፈጸሙ ጥቃቶች ቁጥር ወደ 7,555 ዝቅ ማለቱ ሲዘገብ፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ13 በመቶ ያነሰ መሆኑ ታውቋል።
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ፣ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የታክስ ዕዳ አለባቸው ባላቸው 62 ግብር ከፋዮች ላይ ከሀገር እንዳይወጡ የእግድ ትዕዛዝ ማስተላለፉን አስታወቀ፡፡ ስለጉዳዩ ለአሜሪካ ድምፅ ማብራሪያ የሰጡት፣ የተቋሙ የኮምዩኒኬሽንስ ዲሬክተር አቶ ሰውነት አየለ፣ ከጉዞ እግዱ በተጨማሪ ቢሮው ሌሎች አስተዳደራዊ ርምጃዎችንም እየወሰደ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ በእግዱ ዙርያ አስተያየት የሰጡን አንድ የሕግ ባለሞያ ደግሞ፣ ቢሮው ይህን የማድረግ ሥልጣን በዐዋጅ እንደተሰጠው ገልጸው፣ ነገር ግን የዚህ ዐይነት ውሳኔ የሚተላለፈው፣ ታክስ ከፋዩ ግለሰብ ከሀገር ሊወጣ ይችላል የሚል በቂ ምክንያት ሲኖር ብቻ ነው ብለዋል፡፡ ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
ቤጂንግ «በዘፈቀደ የተፈጸመ» ላለችው የትራምፕ አስተዳደር ለደነገገው ተጨማሪ የቀረጥ የአጸፋ መልስ እሰጣለሁ ስትል አስጠንቅቃለች። የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዛሬው ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “መልካምን በክፉ ትመልሳለች” ሲሉም ዩናይትድ ስቴትስን ወንጅለዋል። የአሜሪካ ድምጹ ቢል ጋሎ እንደዘገበው፣ ይህ ቤጂንግ ራሷን ለዓለም መረጋጋት የቆመ ኃይል አድርጋ ለማሳየት የምታደርገው ጥረት አካል መሆኑን ጠቁሟል። ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
በኢትዮጵያ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጩ እና በሀገር ውስጥ ለሚካሄዱ የተለያዩ ግጭቶች መባባስ ምክንያት እየሆኑ መሄዳቸውን ተከትሎ፣ ስለሀሰተኛ መረጃ ምንነት እና መረጃን ከተለያዩ ምንጮች የማጣራት ክህሎት የሚያስጨብጥ የሚዲያ አጠቃቀም ትምህርት ወሳኝ መሆኑን በርካታ ጥናቶች ያመለከታሉ። ተማሪዎች እና ወጣቶች በማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ዙሪያ ያላቸው እውቀት ምን እንደሚመስል ጠይቀናቸዋል። ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ከኢራን ጋራ የኑክሌር ድርድር ማድረግ እንደሚሹ ለሀገሪቱ መሪዎች ትላንት ሐሙስ ደብዳቤ መላካቸውን አስታውቀዋል። የኢራን መሪዎች ለመነጋገር ይስማማሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ትረምፕ አስታውቀዋል። ትረምፕ ከፎክስ ኒውስ ጋራ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ ኢራን ለድርድር ትቀርባለች ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉና፣ ይህም ለኢራን መልካም ሁኔታዎችን ሊፈጥር እንደሚችል ጠቁመዋል። “ደብዳቤውን ለማግኘት የፈለጉ ይመስለኛል፣ ሌላው አማራጭ ግን አንድ ነገር ማድረግ ይኖርብናል፣ ምክኒያቱም የኑክሌር መሣሪያ እንዲኖራቸው መፍቀድ አይቻልም “ ብለዋል ትረምፕ፡፡ ደብዳቤው የተላከው ለኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላ ኻሚኒ እንደሆነ የተገመተ ሲሆን፣ ይህንኑ ከኋይት ሃውስ ለማጣራት የተደረገው ሙከራ መልስ ባለመገኘቱ እንዳልተሳካ የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል። የሩሲያው ምክትል የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ርያብኮቭ የኢራንን የኑክሌር ፕሮግራም አስመልክቶ የተፈጠረውን ውዝግብ ለመፍታት የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጥረት በተመለከተ ከኢራኑ አምባሳደር ካዜም ጃላሊ ጋራ እንደተወያዩ የሩሲያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ዓርብ አስታውቋል።
የኬንያው ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ከቀድሞው ዋና ተፎካካሪያቸው ከራይላ ኦዲንጋ ጋራ በፖለቲካ ጉዳዮች ትብብር ለማድረግ ስምምነት ተፈራርመዋል። ሁለቱ ወገኖች እየጨመረ ያለውን የሃገሪቱን ዕዳ እና ሙስናን ጨምሮ ሌሎቹንም ሃገሪቱን የገጠሟትን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ አብረው ለመሥራት ተስማምተዋል። ሩቶ የግብር ጭማሪ እንደሚያደርጉ ማስታወቃቸውን ተከትሎ በሃገሪቱ በተነሳው ተቃውሞ ቢያንስ 60 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። የነበራቸው የሕዝብ ድጋፍም እያሽቆለቆለ መጥቷል። ተቃውሞው በመበርታቱም ሩቶ ከተቃዋሚያቸው ከኦዲንጋና ከበርካታ የፓርቲ አባሎቻቸው ጋራ”ሰፊ መሠረት ያለው” መንግሥት ለመመስረት እንዲሠሩ አስገድዷቸዋል። ይህንን ስምምነትም ዛሬ በይፋ በመፈረም ሃገሪቱ የገጠማትን ችግሮች ለመቅረፍ በጋራ እንደሚሠሩ አስታውቀዋል። ጉምቱ የተቃዋሚ ፖለቲከኛው ራይላ ኦዲንጋ በኬንያ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ አምስት ጊዜ ተሳትፈው ሳይቀናቸው ቀርቷል። ስምምነቱ በሃገር ውስጥ ያለውን ውጥረት ለማርገብ ያለመ እንደሆነ የ80 ዓመቱ ኦዲንጋ አስታውቀዋል። ሩቶ በበኩላቸው ስምምነቱ “ነፃነትና መልካም አጋጣሚዎች ለሁሉም መድረሳቸውን ማረጋገጫና ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚወስድ መንገድም ነው” ብለዋል። የፖለቲካ ተንታኞች ስምምነቱን «እየተንኮታኮተ ያለው አገዛዝ እንዲያንሰራራ የተደረገ ሙከራ» ሲሉ ገልጸውታል።
በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ በተደጋጋሚ ባጋጠመው ርእደ መሬት የመፍረስ ጉዳት የደረሰበት የከሰም ስኳር ፋብሪካ፣ በሺሕ ለሚቆጠሩ ሠራተኞቹ የመጨረሻ የስንብት ማስታወቂያ አወጣ፡፡ የፋብሪካው ሠራተኞች ማኅበር ውሳኔውን «አግባብነት የሌለው» ሲል ተችቷል፡፡ «ፋብሪካው ለሠራተኞቹ የስንብት ማስታወቂያ ከማውጣቱ በፊት ሌሎች አማራጮችን መመልከት ነበረበት፤» ብሏል ማኅበሩ፡፡ የፋብሪካው ሠራተኞች በበኩላቸው፣ «በስንብት ማስታወቂያው ተደናግጠናል፡፡ ውሳኔው አኹን ያለውን የኑሮ ውድነት እና የጸጥታ ስጋት ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው፤» ሲሉ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡ የፋብሪካው አመራሮች፣ ውሳኔያቸውን አስመልክቶ እስከ አኹን ለብዙኃን መገናኛ የሰጡት መግለጫ የለም፡፡ የአሜሪካ ድምፅም ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጎ አልተሳካለትም፡፡ የአገሪቱን የስኳር ፋብሪካዎች በበላይነት የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ፣ ፋብሪካው ሠራተኞቹን ለማስቀጠል በሚያስችል ቁመና ላይ አይደለም፤ ብሏል፡፡ የአገር አቀፍ እርሻ እና አግሮ ኢንዱስትሪ ሠራተኛ ማኅበራት ፌዴሬሽን ደግሞ፣ በሠራተኞቹ ላይ ስለደረሰው ጉዳት እና በመጻኢ ዕድላቸው ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋራ እየተወያየ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
በጋምቤላ ክልል በኑዌር ዞን በተከሠተው የኮሌራ ወረርሽኝ፣ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ30 በላይ ሰዎች መሞታቸውንና ከአንድ ሺሕ በላይ የሚደርሱ ደግሞ በበሽታው መታመማቸውን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ። የኑዌር ዞን ጤና መምሪያ ሓላፊ አቶ ጋትቤል ግርማ ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፣ ወረርሽኙ ቀድሞ የተከሠተባቸው ዋንታዎ እና አኮቦ ወረዳዎች፣ አኹንም ስርጭቱ ከፍተኛ እንደኾነ ጠቅሰው፣ መድኃኒትም በበቂ ኹኔታ አልቀረበም፤ ብለዋል። ከጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት፣ ወደ ከፍተኛ አመራሮች ስልክ ብንደውልም ጥሪው ባለመነሣቱ ምክንያት ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም።
የዩናይትድ ስቴትስ እና የካናዳ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ትላንት ረቡዕ በንግድ እና ሌሎች ጉዳዮች ውይይት አካሂደዋል፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕም፣ ከካናዳ እና ከሜክሲኮ በሚገቡ ተሽከርካሪዎች ላይ አዲስ የተጣለውን የ25 ከመቶ ቀረጥ ለአንድ ወር አዘግይተዋል ። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና የካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜላኒ ጆሊ «በጋራ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች፣ በድንበር ደህንነት መጠናከር ፣ በንግድ ልውውጥ እና የኢኮኖሚ ብልጽግና» ሁለቱ ሀገሮች በትብብር መሥራታቸውን ለመቀጠል ስለሚችሉበት መንገድ መወያየታቸውን የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ትረምፕ ቀረጡን ማዘግየታቸውን ከማስታወቃቸው በፊት ከትላልቆቹ የዩናይትድ ስቴትስ መኪና አምራቾች፣ ከፎርድ፣ ጀነራል ሞተርስ እና ስቴላንቲስ የሥራ አስፈፃሚዎች ጋር መነጋገራቸውን የኋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ካሮላይን ሌቪት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ ትረምፕ መኪና አምራቾቹ፣ የማምረቻ ቦታዎቻቸውን ከሜክሲኮ እና ካናዳ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በማዞር የሚጣልባቸውን ቀረጥ በጠቅላላ ማስወገድ እንዲችሉ ያሳሰቧቸው መሆኑንም ቃል አቀባይዋ አክለዋል፡፡ ትረምፕ በሁለቱ ትላልቆቹ የአሜሪካ የንግድ ሸሪኮች ሌሎች ምርቶች ላይ የጣሏቸው አዲሶቹ ቀረጦች እንዳለ እንደሚቆዩ ሌቪት ገልጸዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሌሎችንም ምርቶች ከቀረጥ ነጻ ማድረግ የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ካሉ ለማጤን ዝግጁ መሆናቸውን ቃል አቀባይዋ ተናግረዋል፡፡ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ሀገራቸው ላይ የተጣሉ ሁሉም የአሜሪካ ቀረጦች እስካልተነሱ ድረስ፣ ካናዳ በአጸፋው የጣለቻቸውን ቀረጦች ለማስወገድ ፈቃደኛ አልሆኑም ። የኦንታርዮ ክፍለ ግዛት አገረ ገዥ ደግ ፎርድ “ወደ አሜሪካ በሚላኩ የካናዳ ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው ቀረጥ ባለበት ከቀጠለ በካናዳ የሚገኙ የተሽከርካሪ ማምረቻዎች በ10 ቀናት ውስጥ መዘጋት ይጀምራሉ” ብለዋል፡፡ “ሰዎች ሥራቸውን ያጣሉ” ሲሉም ፎርድ አክለዋል፡ የካናዳ የክልል መሪዎች በዩናይትድ ስቴትስ ገበያ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ ከሌሎች አገሮች ጋር የንግድ ልውውጥን ለማስፋት እየሰሩ ነው፡፡ ትረምፕ በቻይና ምርቶች ላይ የጣሉትን ቀረጥ በእጥፍ በማሳደግ 20 ከመቶ በማድረሳቸው የአክሲዮን ገበያው እንዲያሽቆለቁል እና ሸማቾች ላይ ዋጋ የመጨመር ስጋት እንዲፈጠር አድርጓል። ሜክሲኮ፣ ካናዳ እና ቻይና ለትረምፕ እርምጃ በአሜሪካ ምርቶች ላይ የአጸፋ ቀረጥ እንደሚጥሉ አስታውቀዋል። ፕሬዝደንት ትረምፕ በትሩዝ ሶሻል መድረካቸው ላይ ባወጡት ጽሁፍ «ትሩዶ ሀገራቸው ላይ የተጣሉትን አዳዲስ ቀረጦች በሚመለከት ምን ማድረግ እንደሚቻል ትላንት ረቡዕ ስልክ ደውለው ጠይቀውኝ ነበር፡፡ እኔም በካናዳ እና በሚከሲኮ ድንበር በኩል የሚገባው ፈንቲኔል ብዙ ሰው ገድሏል፡፡ ያ መቆሙን የሚያሳምን ነገር አላገኘሁም አልኳቸው፡፡ ከበፊቱ ተሻሽሏል አሉ፡፡ እሱ በቂ እንዳልሆነ ነግሬአቸዋለሁ » ብለዋል፡፡
የፈረንሳይ መከላከያ ሚኒስትር ሴባስቲየን ለኮርኑ ሀገራቸው ለዩክሬን የስለላ መረጃ እያጋራች መሆኗን ዛሬ ሐሙስ ተናገሩ፡፡ ርምጃው ዩናይትድ ስቴትስ ከዩክሬን ጋራ የምታደርገውን የመረጃ ልውውጥ አቋርጫለሁ ማለቷን ተከትሎ የተሰማ ነው። ርምጃው የተወሰደው የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች በብራሰልስ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ በተገኙበት የመከላከያ ወጪያቸውን በማሳደግ እና ዩክሬን ከሩሲያ ጋራ በምታደርገው ጦርነት ድጋፍ ለመስጠት ቃል ስለ መግባት ውይይት ባደረጉበት በዛሬው ዕለት መሆኑ ነው፡፡ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከውይይቱ በፊት የአውሮፓ ኅብረት አባላት “ወደፊት ወሳኝ ርምጃዎችን እንደሚወስዱ” ተናግረዋል፡፡ በአዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን ስለምትሰጠው ድጋፍ በወሰደው የአቋም ለውጥ ስጋት ያላቸው መሆኑንም ማክሮን ገልጸዋ፡፡ «የአውሮፓ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በዋሽንግተን ወይም በሞስኮ መወሰን የለበትም» ብለዋል ማክሮን፡፡ ትረምፕ ባለፈው ሳምንት ከዘሌንስኪ ጋራ በኋይት ሀውስ ካደረጉት አወዛጋቢ ውይይት በኋላ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ለኪቭ ተዋጊዎች የምትሰጠውን ወታደራዊ ርዳታ እንድታቆም በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ አዘዋል። የየዩናይትድ ስቴትስ የማዕከላዊ ስለላ ድርጅት (ሲአይኤ) ዳይሬክተር ጆን ራትክሊፍ ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ለጊዜው የስለላ መረጃ ለኪቭ መረጃ ማጋራቷን ማቆሟን ትላንት ረቡዕ ተናግረዋል:: ሆኖም ዘሌንስኪ በኋይት ሀውስ ከትረምፕ ጋራ የነበራቸውን ልውውጥ “የሚጸጽት” በማለታቸውን እና ሀገራቸው ከሩሲያ ጋራ ለሚደረገው የሰላም ድርድር ዝግጁ መሆኗን በመናገራቸው የመረጃ ልውውጡ መቋረጥ ለረጅም ጊዜ ላይቆይ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሐማስ “የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ ዛቻዎች እስራኤል ከጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንድትወጣ እያበረታታ ነው” ሲል ዛሬ ሐሙስ ተናገረ። ሐማስ ይህን የገለጸው፣ ትረምፕ ሐማስ ጋዛ የሚገኙ ቀሪዎቹን ታጋቾች ካልፈታ “ ከባድ ቅጣት ያገኘዋል” ካሉ አንድ ቀን በኋላ ነው። ትረምፕ ትሩዝ ሶሻል በተባለው የማኅበራዊ መገናኛ መድረካቸው ላይ “ሁሉንም ታጋቾች ሳይዘገይ፣ አሁኑኑ ልቀቁ ፣ የገደላችኋቸውን ሰዎች አስከሬንም በሙሉ አሁኑኑ መልሱ፡፡ ካልሆነ አለቀላችሁ።” ብለዋል፡፡ ትረምፕ አክለውም “እስራኤል ሥራውን ለማጠናቀቅ የሚያስፈልጋትን ሁሉን ነገር እየላኩ ነው፡፡ ያልኩትን ካላደረጋችሁ አንድም የሐማስ አባል አይተርፍም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡ የተኩስ አቁሙ የመጀመሪያው ምዕራፍ ባለፈው ቅዳሜ አብቅቷል። በስምምነቱ መሠረት ሐማስ 33 እስራኤላውያን ታጋቾችን እና አምስት የታይላንድ ዜጎችን ሲለቅ፣ እስራኤል 2 ሺሕ የሚጠጉ የፍልስጤም እስረኞች ለቃለች። ኋይት ሀውስ ከሐማስ ጋራ በቀጥታ ውይይት ማድረጉን ትላንት ረቡዕ አረጋግጧል። “ውይይቱ ያተኮረው አሁንም በጋዛ ታግተው የሚገኙ አሜሪካውያንን ስለ መልቀቅ ነው” ሲሉ፣ ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ምንጮች ገልጸዋል። የኋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ካሮላይን ሌቪት ንግግሮቹን “ለአሜሪካ ሕዝብ የሚጠቅመውን ለማድረግ በቅን ልቦና የተደረገ ጥረት ነው” ሲሉ ገልፀውታል። የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት በሰጠው መግለጫ ደግሞ እስራኤል «ከሐማስ ጋራ በቀጥታ መነጋገርን በሚመለከት ያላትን አቋም ለአሜሪካ አስታውቃለች» ብሏል። የጋዛ ጦርነት የጀመረው፣ ሐማስ እ.ኤ.አ ጥቅምት 2023 እስራኤል ላይ ባደረሰው ድንገተኛ ጥቃት፣ 1ሺሕ 200 የሚጠጉ ሰዎችን ከገደለ እና 250 ሰዎች አግቶ ከወሰደ በኋላ ነበር። እስራኤል በአፀፋው ጋዛ ላይ በወሰደችው ጥቃት ከ48 ሺሕ 400 በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ሲል የጋዛው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ ትላንት ማክሰኞ ምሽት ለዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤቶች ጣምራ ጉባኤ ባሰሙት ንግግር የፌዴራል መንግሥቱን መጠን እና ተጽዕኖ ለመቀነስ አስተዳደራቸው የወሰዳቸውን ቀዳሚ ርምጃዎች በማድነቅ አውስተዋል፡፡ በአሜሪካ የቅርብ የንግድ አጋሮች ላይ የጣሉትን ከፍተኛ ቀረጥ እና ዩክሬን የሩሲያን ወረራ ለመመከት የገባችውን ጦርነት እንድታቆም የሚያደርጉትን ግፊት ጨምረው ዘርዝረዋል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የታደሙ ዲሞክራት የምክር ቤቶቹ አባላት በበኩላቸው ተቃውሟቸውን ግልጽ አድርገዋል። የአሜሪካ ድምጽ የኋይት ሀውስ ቢሮ ኃላፊ ፓትሲ ዊዳኩስዋራ ያደረሰችንን ዘገባ አሉላ ከበደ እንደሚከተለው ያቀርበዋል።
ቻይና የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት የሚያስችሏትን ፕሮጀክቶች እንደምታዘጋጅ ዛሬ ረቡዕ አስታውቃለች። ፕሮጀክቶቹ እ.አ.አ ከ2030 አስቀድማ የካርበን ዳይኦክሳይድ በካይ ጋዝ ልቀቷን መጠን በመገደብ በ2060 ደግሞ ከካርበን ልቀት ነፃ የሚያደርጋት መሆኑን አመልክታለች። ሙቀት አማቂ ጋዞችን በብዛት ወደ አየር በመልቀቅ ከዓለም ቀዳሚ የሆነችው ቻይና፣ በባሕር ዳርቻዎች ላይ አዳዲስ የንፋስ ኃይል ማመንጫዎችን እንደምታለማ እና በበረሃማ አካባቢዎች «አዳዲስ የኃይል መሠረተልማቶችን» እንደምትገነባ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እቅድ አውጪ ኮሚሽን ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል። ሪፖርቱ አክሎ «ቻይና የካርበን ልቀትን ለመቀነስ እና በሂደት ሙሉ ለሙሉ ለማቆም በንቃት እና በጥንቃቄ ትሰራለች» ብሏል። ሆኖም በሀገሪቱ የድንጋይ ከሰል ቁልፍ የኃይል ምንጭ ሆኖ እንደሚቀጥል ያመለከተው ሪፖርቱ፤ የካርበን ልቀትን ለመቀነስ የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችን እያቀደች ባለችበት ወቅትም በዚህ ዓመት የድንጋይ ከሰል ምርትና አቅርቦትን ማሳደጓን እንደምትቀጥል ገልጿል።
ጀርመን ለሩዋንዳ የምትሰጠውን አዲስ የልማት ርዳታ ማቆሟን እና ቃል የገባቻቸውን ድጋፎችም እየገመገመች መኾኑን ዛሬ ማክሰኞ አስታውቃለች። ጀርመን ይህን ርምጃ የወሰደችው፣ ሩዋንዳ በጎረቤቷ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሚካሄደው ግጭት ውስጥ ላላት ሚና ምላሽ ለመስጠት ነው። የጀርመን ልማት ምኒስትር ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ በርሊን ውሳኔዋን አስቀድማ ለሩዋንዳ ማሳወቋን እና በምስራቅ ኮንጎ የበላይነት እያገኘ ላለው የኤም 23 አማፂ ቡድን የምትሰጠውን ድጋፍ እንድታቆም ማሳሰቧን አመልክተዋል። ኮንጎ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሞያዎች እና የምዕራብ ኃያላን ሀገሮች ሩዋንዳ አማፂውን ቡድን ትደግፋለች በማለት ይከሷታል። ክሱን የምትቃወመው ሩዋንዳ በበኩሏ በኮንጎ የቱትሲ ተወላጆችን ለመጨፍጨፍ እና ለሩዋንዳ ስጋት ለመፍጠር ከሚንቀሳቀሱ የሁቱ ተወላጅ ታጣቂዎች እራሷን እየተከላከለች እንደሆነ ትገልጻለች። የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያቤት የጀርመን ውሳኔ «የተሳሳተ እና አሉታዊ ውጤት ያለው ነው» ሲል ምላሽ ሰጥቷል። መስሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ «በቀጠናው በተደጋጋሚ ለሚከሰቱ አለመረጋጋቶች ታሪካዊ ኃላፊነት የተሸከሙ እንደ ጀርመን ያሉ ሀገራት ለአንድ ወገን ያደላ አስገዳጅ ርምጃዎችን ከመተግበር የተሻለ ማወቅ ነበረባቸው» ብሏል። የጀርመን ምኒስቴር እንደገለፀው በርሊን፣ እ.አ.አ ከጥቅምት 2022 እስከ 2024 ላለው ጊዜ የ98 ሚሊየን ዶላር ርዳታ ለሩዋንዳ ለመስጠት ቃል ገብታ ነበር።
ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝደንት ሪክ ማቻር ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያለው የታጠቀ ቡድን፤ በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኝ የጦር ሠፈር መውረሩን ተከትሎ፣ የመንግሥቱ ወታደሮች ዛሬ በዋና ከተማዋ ጁባ የሚገኘውን የምክትል ፕሬዝደንቱን መኖሪያ ቤት ከበዋል፡፡ በርካታ አጋሮቻቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል። ማቻር፤ ባለፈው ወር የመንግሥት ባለስልጣን የነበሩ በርካታ አጋሮቻቸው መባረራቸው እ.አ.አ በ2018 በእሳቸው እና በፖለቲካ ተቀናቃኛቸው ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አደጋ ላይ ይጥላል ብለው ነበር። በሁለቱ ተቀናቃኞች መካከል ለአምስት ዓመታት በተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ለማቻር ታማኝ የነበሩት የጦሩ ምክትል አዛዥ ጀነራል ጋብሪኤል ዱፕ ላም በሰሜኑ ግዛት ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ ትላንት ማክሰኞ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን በተመሳሳይ የማቻር አጋሩ የነዳጅ ዘይት ሚኒስትር ፑት ካንግ ቾል ከጠባቂዎቻቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ዛሬ ረቡዕ በቁጥጥር ስር ውለዋል። የታሰሩበት ምክንያት ግን እስካሁን አልተገለጸም። የምዕራብ ሀገራት ልዑካን መሪዎቹ ውጥረቱን እንዲያረግቡ ባለፈው ሳምንት አሳስበው ነበር። ደቡብ ሱዳን እ.አ.አ በ2018 የተደረሰውን ስምምነት እስካሁን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ያላደረገች ሲሆን ባለፈው ዓመት ሊካሄድ የነበረው ምርጫም በገንዘብ እጦት ምክንያት ለሁለት ዓመት ተራዝሟል።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ማክሰኞ ምሽት በአሜሪካ የሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ያደረጉትንን ንግግር «አሜሪካ ተመልሳለች» በማለት የጀመሩት ሲኾን፣ የሪፐብሊካን ሕግ አውጪዎች «ዩ ኤስ ኤ» በሚል ዝማሬ አጅበዋቸዋል። «ከስድስት ሳምንት በፊት እዚህ ቆሜ የአሜሪካን ወርቃማ ዘመን ዐውጄ» ነበር ያሉት ትራምፕ ከዚያን ጊዜ ወዲህ በሀገራችን ታሪክ ውስጥ ታላቅ እና ስኬታማ ዘመን ለማምጣት ፈጣን እና የማያቋርጥ ተግባራት ተከናውነዋል« ብለዋል። »አስተዳደራቸው በ43 ቀናት ውስጥ ብቻ ሌሎች ብዙ አስተዳደሮች በአራት እና ስምንት ዓመታት ውስጥ ካከናወኗቸው የበለጠ መሠራቱን« የገለጹት ትረምፕ »ገና እየጀመርን ነው« ብለዋል። ትረምፕ እስካሁን 76 የፕሬዝደንት ማዘዣዎችን የፈረሙ ሲሆን አብዛኞቹ በፍርድቤት ክስ ተመስርቶባቸዋል። ትረምፕ ንግግራቸውን ከጀመሩ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ በምክር ቤቱ አዳራሽ ከተሰበሰቡ ሰዎች በተሰማ የስላቅ ድምፅ ንግግራቸው በመስተጓጎሉ የተወካዮች ምክርቤቱ አፈ-ጉባኤ ማይክ ጆንሰን የምክርቤቱ ሥነ ስርዐት አስከባሪዎች፣ በቴክሳስ ዲሞክራት ፓርቲን ወክለው ለምክርቤት አባልነት የተመረጡትን አል ግሪን ከምክርቤቱ እንዲያስወጧቸው አዘዋል። ሌሎች የምክር ቤቱ አባላትም ሥነ-ስርዐት እንዲከተሉ አሳስበዋል። ግሪን ከምክርቤቱ አዳራሽ ከወጡ በኋላ ትረምፕ ንግግራቸውን ቀጥለዋል። ተረምፕ በዚኹ የማክሰኞ ምሽት ንግግራቸው »የመጀመሪያው ወር የፕሬዝደንትነት ዘመኔ፣ በሀገራችን ታሪክ እጅግ ስኬታማው መሆኑን ብዙዎች ገልጸውታል« ያሉት ትራምፕ፣ በድንበር በኩል የሚፈፀም ሕገወጥ ሽግግርን ለማስቆም የወሰዱትን ርምጃም አብራርተዋል። »በሀገራችን ላይ የሚፈፀመውን ወረራ ለመመከት« በደቡባዊ ድንበር ላይ ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ማወጃቸውን እና የዩናይትድ ስቴትስ ጦር በድንበር ላይ እንዲሰፍ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት »ባለፈው ወር በሕገወጥ መንገድ ድንበር አያርጠው የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር እስከዛሬ ከተመዘገበው ዝቅተኛ ነው« ብለዋል። በተጨማሪም ወደ ዋይት ሐውስ እንደተመለሱ የፌደራል ቅጥር ሂደቶች እና የውጭ ርዳታዎች ላይ እግድ መጣላቸውን ገልጸዋል። የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ቁጥር እና ሠራተኞችን ለመቀነስ፣ በምፅሃረ ቃሉ 'ዶጅ' በመባል የሚጠራ በኢላን መስክ የሚመራ ተቋም መመስረታቸውን የተናገሩት ትረምፕ በቢሊየኖች የሚቆጠር የመንግሥት ገንዘብ እያዳነ መሆኑንም አመልክተዋል። ትረምፕ በንግግራቸው በዩናይትድ ስቴትስ በ48 ዓመት ውስጥ ያልታየውን የዋጋ ግሽበት ለማስተካከል ከወሰዷቸው ርምጃዎች መካከል »ወርቃማ ፈሳሽ« ሲሉ የጠሩትን የነዳጅ ጋዝ ቁፋሮ እያካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል። »የወሳኝ እና ብርቅዬ ማዕድናት« ምርት እንደሚፋጠንም ገልጸዋል። »ቀጣዩ የግብር ቅነሳ ነው« ያሉት ትራምፕ፣ ከገቢ ግብር፣ ከቲፕ ገንዘብ እና ከትርፍ ሰዓት ክፍያ ላይ ግብር እንደሚያነሱም ተናግረዋል። ትረምፕ አክለው አሜሪካን »ኢ-ፍትሃዊ« ሲሉ ከገለጹት የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት፣ »ሙሰኛ« ካሉት የዓለም ጤና ድርጅት እና »ፀረ-አሜሪካዊ« ሲሉ ከገለፁት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ማስወጣታቸውን አብራርተዋል። የፕሬዝደንት በዓለ ሲመት ባልተካሄደባቸው ዓመታት »ዘ ስቴት ኦፍ ዘ ዩኒየን« በመባል የሚጠራው እና የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች ለጋራ ምክርቤቱ የአሜሪካን አኹናዊ ሁኔታ በሚያብራሩበት በዚህ ንግግር፤ ትራምፕ ለዩናይትድ ስቴትስ ኢኮኖሚ እና ኢሚግሬሽን ፖሊሲ ያላቸውን ርዕይ ለሕዝብ የሚያቀርቡበት እና የፌደራል ሠራተኞችን ቅነሳ እና ከዩክሬን ፕሬዝደንት ጋራ የነበራቸውን እሰጥ አገባ አስመልክቶ የሚያብራሩበት ዕድል ፈጥሮላቸዋል። ትረምፕ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮለድሚር ዜለንስኪ ጋራ ያደረጉትን ኃይለቃል የተሞላበት ውይይት ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የምትሰጠውን ወታደራዊ ርዳታ አቋርጣለች። »አውሮፓውያን ዩክሬንን ከመደገፍ ይልቅ ከሩስያ ለሚገዙት ነዳጅ እና ዘይት የበለጠ አውጥተዋል« ያሉት ትራምፕ የዩክሬን ፕሬዝደንት ለሰላም ዝግጁ መሆናቸውን የሚገልፅ ደብዳቤ እንደፃፉላቸው አመልክተዋል። ትረምፕ አክለው »በተመሳሳይ ጊዜ ከሩሲያ ጋራ ጠንከር ያለ ውይይት አድርገን ለሰላም ዝግጁ መኾናቸውን የሚያሳይ ምልክቶች አግኝተናል" ብለዋል።
እስራኤል ከውሃ በስተቀር ማንኛውም የሰብአዊ ዕርዳታ ወደ ጋዛ ሰርጥ እንዳይገባ ማገዷ፣ ወትሮውንም በሕይወት ለመቆየት ትግል ላይ ባሉት ሕፃናትና ቤተሰቦቻቸው ላይ አደገኛ ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) አስታውቋል። “ትላንት በዕርዳታ ላይ የተጣለው እገዳ የሲቪሎችን ሕይወት ለመታደግ በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል” ሲሉ የቀጠናው የዩኒሴፍ ኅላፊ ኤድዋርድ ቤግበደር አስታውቀዋል። የሕፃናትን ደህንነት ለመጠበቅ ወሳኝ የሆነው የተኩስ አቁም መቀጠሉ አስፈላጊ እንደሆነም ኅላፊው ጨምረው ተናግረዋል። በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ ልዑክ የሆኑት ስቲቨን ዊትኮፍ ተኩስ አቁሙ እስከ እ.አ.አ ሚያዚያ 20 ድረስ እንዲራዘም መጠየቃቸውን ያወሱት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ፣ ይህም የረመዳን ወር እና የአይሁድ በዓላትን የሚሸፍን ሲሆን፣ በዚህ ወቅት በመጀመሪያው ቀን ሃማስ ግማሽ የሚሆኑ ታጋቾችን እንደሚለቅ፣ በመቀጠል ቋሚ የተኩስ ማቆም ሲፈጸም ደግሞ የተቀሩትን ታጋቾች እንደሚለቅ ተናግረዋል። “ይህን ሃሳብ እቀበላለሁ፣ ሃማስ ግን እስከ አሁን እየተቃወመው ነው” ሲሉ አክለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። እስራኤል ዕርዳታ እንዳይገባ ያገደችው ሃማስ ዕርዳታውን በመስረቁ እና ፍልስጤማውያን እንዳያገኙት በማድረጉ እንደሆነም ኔታንያሁ አስታውቀዋል። “ዕርዳታውን ለሽብር ተግባር እየተጠቀመብት ነው” ሲሉም ክስ አሰምተዋል። የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ ኔታንያሁ የጠቀሱት ጉዳይ ስለመከሰቱ በሥፍራው የሚገኙ ባልደረቦቻቸው ሪፖርት እንዳላደርጉ አስታውቀዋል።
የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ አዲስ ቀረጥ መጣላቸውን ተከትሎ ካናዳ፣ ሜክሲኮ እና ቻይናም በየበኩላቸው የአጸፋ እርምጃ እንወስዳለን ሲሉ አስጠነቀቁ። ዩናይትድ ስቴትስ ሁለቱ ዋና ዋና የንግድ ሸሪኮቿ ሜክሲኮ እና ካናዳ በሚልኳቸው ምርቶች ላይ የጣለችው አዲስ የ25 በመቶ ቀረጥ ዛሬ ተግባራዊ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ዛሬ የሚጀምረው እና በቻይና ምርቶች ላይ የጣለችውን ቀደም ሲል 10 በመቶ የነበረውን ተጨማሪ ቀረጥ በእጥፍ አሳድጋው 20 በመቶ ማስገባቷ ታውቋል። ትረምፕ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የሚፈልሱትን ሕገ-ወጥ ስደተኞች እና ድንበር ተሻግሮ የሚጓጓዘውን ሕገ ወጥ እና አደገኛ መድሃኒት ዝውውር እንዲያግዱ የጠየቋቸው ሁለቱ የዩናይትድ ስቴትስ የቅርብ ጎረቤቶች ሜክሲኮ እና ካናዳ የተባለውን ማድረጋቸውን ይፋ ካደረጉም በኋላ አዲሱን ቀረጥ ጥለውባቸዋል። ትረምፕ በትላንትናው ዕለት ይህንኑ ማስታወቃቸውን ተከትሎም ሦስቱ የዩናይትድ ስቴትስ ዋና ዋና የአክሲዮን ገበያዎች ከፍተኛ ውድቀት ሲያስመዘግቡ፤ ዛሬ ማለዳ በአክሲዮን ገበያዎቹ መክፈቻ ላይም እያንዳንዳችው በ2 በመቶ አዘቅዝቀው ታይተዋል። ከሦስቱ ሀገራት በሚገቡ ምርቶች ላይ በጣሉት ከፍተኛ የቀረጥ ጭማሪ የተነሳ አሜሪካውያን ሸማቾች እና የንግድ ድርጅቶች አንዳንድ ጊዜያዊ የኢኮኖሚ ፈተና ሊገጥማቸው ይችላል’ ያሉት ትረምፕ «ነገር ግን በሦስቱ አገሮች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ኩባንያዎች የቀረጥ ክፍያውን ለማስቀረት ሲሉ ፋብሪካዎቻቸው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለማዘዋወር ይገደዳሉ» ሲሉ ተናግረል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ትረምፕ ለወሰዱት የቀረጥ ጭማሪ አገራቸው አፀፋ እንደምትሰጥ የተናገሩት የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ "ይህ ፍትሃዊነት የጎደለው እርምጃ በዋዛ አይታለፍም”ብለዋል። አክለውም አገራቸው 107 ቢሊዮን ዶላር በሚገመቱ የአሜሪካ ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ቀረጥ የምትጥል መሆኗን ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በግጭት ወቅት የሚፈጸሙ ፆታዊ ጥቃቶች ጉዳይ ልዩ ተወካይ ፣”በዓለም አቀፍ ደረጃ ወታደራዊ ወጪ እያደገ ሲሄድ ፣ ግጭት ይጨምራል፡፡ በዚያ ደግሞ በዋናነት የሚጎዱት ሴቶች እና ህጻናት ናቸው« ሲሉ ተናገሩ። ኮሎምበስ ማቭሁንጋ እንደዘገበው፣ በግጭት ቀጣና ውስጥ ያለውን ስቃይ ለማስታገስ የሰብአዊ ረድዔት ድርጅቶች፣ እንደ ሳዑዲ አረቢያ ያሉ ከተለመዱት የተለዩ አዳዲስ የገንዘብ ድጋፍ ምንጮችን በመፈለግ ላይ ናቸው። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በግጭት ውስጥ የሚፈጸሙ የፆታዊ ጥቃቶች ጉዳይ ልዩ ተወካይ ፕራሚላ ፓተን በሪያድ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ርዳታ መድረክ ላይ ለቪኦኤ ሲናገሩ “ዓለም አቀፋዊ ግጭቶች በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ” እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል፡፡ »እያየን ያለነው በግጭቶች ወቅት ፆታዊ ጥቃት በብዛት እንደሚፈጸም ነው፣” ያሉት ፓተን “ በዚህ ደግሞ ሰላማዊ ዜጎች በሙሉ በጣም ይጎዳሉ፣ በይበልጥ የሚጎዱት ግን ሴቶች እና ልጃገረዶችው። በመከላከል ላይ የበለጠ መሥራት ይኖርብናል። መገለልን፣ ድህነትን፣ የፆታ እኩልነት መዛባትን ዋና መንስኤ ለመፍታት መሥራት አለብን። በእርግጥ ምላሽ መስጠት ይኖርብናል፣ መከላከል ግን ላይ የበለጠ መሥራት ያለብን ይመስለኛል።” ብለዋል። በተባበሩት መንግሥታት ስር ያሉና በሳዑዲ አረብያ በተዘጋጀው መድረክ ላይ የተሳተፉ ብዙ የሰብአዊ ቡድኖች ነባሮቹ «የምዕራባውያን» ለጋሾች የገንዘብ ድጋፋቸውን ቀንሰዋል ወይም አቁመዋል ሲሉ ተናግረዋል። ምንም እንኳን በፍርድ ቤቶች በኩል ሕጋዊ ተግዳሮቶች ቢያጋጥሙትም፣ የትረምፕ አስተዳደር በብዙ 10 ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር የውጭ ርዳታን ለማቁረጥ ተንቀሳቅሷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የዩኒሴፍ የተመድ የህጻናት እርዳታ ድርጅት አቅርቦት ክፍል ዳይሬክተር ሌይላ ፓካላ ተቋማቸው “ከ109 ሚሊዮን በላይ ተጋላጭ ህጻናትን እና ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት 9.9 ቢሊዮን ዶላር እየፈለገ ነው” ብለዋል። «በዚህ ዓመት በሰብአዊነት ዙሪያ የሚያስፈልገውን ሁሉ ስንመለከት በአመጋገብ ይሁን፣ በውሃ እና በንፅህና አጠባበቅ ይሁን፣ በጤና ተደራሽነት፣ እና ህጻናት ክትባት እንዳያጡ ለማድረግ ተጨማሪ ፍላጎቶች መኖራቸውን እንመለከታለን፣ “ ሲሉ ፓካላ ያለው አቅም ከፍላጎቶች ጋር እየተራመደ እንዳልሆነም አክለዋል። ፓካላ አያይዘውም »በዓለም ዙሪያ በከባድ አጣዳፊ የምግብ እጦት የሚሰቃዩ ህጻናት ቁጥር እየጨመረ ነው። በግጭት ዞኖች እና ያልተረጋጉ ሁኔታዎች ወይም በደቡባዊ አፍሪካ እንዳየነው በማያቋርጥ ድርቅ ፣ ጎርፍ እና የከባድ አውሎ ነፋስ በመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ በሚሰጥ የመጀመሪያው አጣዳፊ ምላሽ እጥረት ህጻናትና ቤተሰቦች እየተጎዱ ነው።” በማለት “ያለው ፍላጎት ምላሽ ከመስጠት አቅም በላይ ነው።” ብለዋል። ኤስ.ኦ. ኤስ ኢንተርናሽናል የህፃናት መንደር የተባለው ለትርፍ ያልተቋቋመው ድርጅት ፕሬዝደንት፣ ደረጀ ወርዶፋ፣ “የአየር ንብረት ለውጥ ለአጠቃላዩ ሰብአዊ ቀውስ አስተዋፅዖ እያደረገ ነው” ይላሉ።“ሁኔታው “በተለይም በምስራቅ እና በደቡባዊ አፍሪካ እየተባባሰ ነው። ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ በሰብአዊ ቀውስ የተጎዱ ብዙ ሰዎች አሉ። “ የሚሉት ደረጀ “ለእነዚህ የተጎዱ ማኅበረሰቦች አገልግሎቶችን እና ቁሳቁሶችን ለማምጣት የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን በጣም በጣም ከፍተኛ ነው። የዓለም አቀፍ የሰብአዊ ድጋፍ ወደዚህ ደረጃ እና የፍላጎት መጠን እየመጣ አይደለም” ይላሉ። አንዳንድ ቡድኖች የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ፊታቸውን ወደ ሳዑዲው- የንጉሥ ሳልማን የሰብአዊ እና የአስቸኳይ ርዳታ ማእከል (KSRelief) ወደ መሳሰሉ ድርጅቶች ፊታቸውን እያዞሩ ነው። የዚህ ድርጅት (KSRelief) የአጋርነት እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ሃና ኦማር፣ “ግጭቶች እና የአየር ንብረት ለውጥ ብዙ ሰዎችን ለችግር መዳረጉን” ገልጸው፣ ድርጅቱ ብዙ የአፍሪካ ሀገራትን እየረዳ ነው ይላሉ። ኦማር አክለውም “ርዳታ ለማድረስ፣ ለእነዚህ ሰዎች መብት የምንሟገትበትን መንገዶች ለመፈለግ እና ለተቸገሩት መድረሳችንን ለማረጋገጥ ቁርጠኞች ነን። ሰዎች አሁንም እነዚህን ሁሉ ተግዳሮቶች ለመፍታት እና መፍትሄዎችንም እንደሚፈልጉ ተስፋ አለ።” ብለዋል። በዚህ ዓመት ድርጅቱ (KSRelief) ከሳውዲ አረቢያ ውጪ የሰብአዊ ሥራውን የጀመረበትን 10ኛ ዓመት ሲያከብር “የሰብአዊ ምላሽን የወደፊት እጣ ፈንታን ማሰስ” በሚል መሪ ቃል ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር የሰአብ አዊ ውይይት መድረክ አዘጋጅቷል።
ዋሽንግተን ለዩክሬን የምትሰጠው የጦር መሣሪያ ዕርዳታ በድንገት እንዲቋረጥ በተደረገበት፤ ሃሳብ የገባቸው የአውሮፓ ሕብረት መሪዎች ከሩስያ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ጋር በተዛመደ የሕብረቱን የመከላከያ አቅም ለማጎልበት በሚያስችሉ መንገዶች ዙሪያ ለመምከር የፊታችን ሃሙስ ብረስልስ ላይ እንደሚሰበሰቡ ተገለጠ። “ጥያቄው የአውሮፓ ደኅንነት በተጨባጭ አደጋ ላይ ወድቋል፣ ወይም አውሮፓ ደህንነቷን ለማስከበር የምትወስደውን ኃላፊነት ማሳደግ አለባት’ የሚለው አይደለም” ያሉት የአውሮፓ ኮሚሽነር ኡርሱላ ቮን ደር ሊን “ከፊታችን ያለው ትክክለኛ ጥያቄ አውሮፓ ሁኔታው በሚጠይቀው ደረጃ ቁርጠኛ ምላሽ ለመስጠት፣ ብሎም በሚፈለገው ፍጥነት እና እቅድ ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን ማረጋገጥ ነው” ብለዋል። የሕብረቱ ኮሚሽነር ከጉባኤው አስቀድሞ በሰጡት አስተያየት፣ በርካታ ዝርዝሮች ያቀፈውን የ840 ቢሊዮን ዶላር የመከላከያ በጀት ዕቅድ 27 አባል አገራት ላሉት ሕብረት አቅርበዋል። ኮሚሽነሯ ያስተላፉት ይህ መልእክት ‘የዩናይትድ ስቴትስ የአጋርነት ተሳትፎ የሚጓደልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል’ በሚል ሥጋት የአሕጉሪቱ መሪዎች በተገኙባቸው በርከት ያሉ አስቸኳይ ስብሰባዎች ላይም ተስተጋብቷል። ዋሽንግተን ‘የአውሮፓ መሪዎች ተጨማሪ ኃላፊነት እንዲወስዱ’ በሚል ለዓመታት ስታሰማ የቆየችው ጥሪ እና የወቅቱ ሁኔታ አዲሱን የአውሮፓ የመከላከያ ወጪ ዕቅድ ቅርብ አድርገውታል። ይሁንና የሕብረቱ አባላት አንዳንድ ፈተና ከገጠማቸው መንግሥታት እና ኢኮኖሚዎች፤ ሁኔታውን አስመልክቶ የጎላ ጥርጣሬ የሚያንጸባርቁ ማሕበረሰቦች እስካሉባቸው፤ እና በአመዛኙ ለሩስያ ተስማሚ የሆነ ቀኝ ዘመም አመለካከት ያላቸው ኃይሎች እየገነኑ የመጡባቸው አገራት የደቀኑት ፈተና ድረስ የአሕጉሪቱን መከላከያ የማጎልበቱን ጥረት አቀበት ያደርጉታል ተብሏል።
ሰሜን ኬንያ በሚገኘው ካኩማ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ በተቃውሞ እንቅስቃሴ ወቅት ፖሊስ በወሰደው ርምጃ አራት ሰዎች መቁሰላቸው ተገለጸ። በትላንቱ የምግብ ዕደላ ላይ የተቀሰቀሰው ግጭት ለስደተኛው ከሚሰጠው የምግብ ርዳታ እጥረት ጋራ የተያያዘ መኾኑም ተመልክቷል። ከኬንያ አጎራባቾች ደቡብ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ ቡሩንዲ እና ኮንጎ ግጭቶችን በመሸሽ እና በድርቅ ሳቢያ የሚሰደዱ ወገኖችን በሚያስጠልለው ካምፕ ውስጥ ለሚገኙት በብዙ ሺሕዎች የሚገመቱ ስደተኞች ይሰጥ የነበረው የምግብ አቅርቦት፤ በተፈጠረው የርዳታ ገንዘብ እጥረት የተነሳ የወትሮ አሠራሩ መስተጓጎሉ ተዘግቧል። በካምፑ ለስደተኞች የሚሰጠውን ምግብ የሚያከፋፍለው የዓለም የምግብ ፕሮግራም ባለፈው ታኅሣሥ ወር ለስደተኞች ከሚሰጠው ምግብ "በገጠመው የአቅርቦት እጥረት የተነሳ ከሚያስፈልገው ከ45 በመቶ በታች እንደነበር አመልክቷል። የዓለም የምግብ ፕሮግራም ከለጋሽ አገሮች መንግሥታት ያገኝ የነበረው መዋጮ እጥረት እንደሚገጥመው ለዓመታት ሲያሳስብ መቆየቱ ይታወቃል።
ዩናይትድ ስቴትስ በቻይና ላይ የጣለችው ተጨማሪ ቀረጥ በጀመረበት እና ፕሬዝዳንት ሺ «ውስብስብ እና ዘርፈ ብዙ» ያሏቸውን የምጣኔ ፈተናዎች ለመፍታት የሚያስችሉ መላዎች ፍለጋ በያዙበት ባሁኑ ወቅት፤ ቻይና ዓመታዊውን ታላላቅ የፖለቲካ ጉባኤዋን ጀምራለች። ከዛሬ አንስቶ በሺዎች የሚቆጠሩ የቻይና ልሂቃን እና የሃገሪቱ ምክር ቤት አባላት የ2025ቱን የፖሊሲ አጀንዳዎች ለመቅረጽ የሚያግዝ መሆኑ በተነገረለት ጉባኤ መሳተፍ ይዘዋል። ከንግዱ ማሕበረሰብ እና ከከፍተኛ የትምሕርት ተቋማት እስከ የአገሪቱ መንግሥት እና የፓርቲው የፖለቲካ አማካሪዎች ጉባኤ ሰፊ የሕዝብ ውክልና ያላቸው ከተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተሳታፊዎች ተገናኝተዋል። ነገ ረቡዕ በአመዛኙ የመንግሥቱን አመለካከት የሚያስተጋባው ብሔራዊ ምክር ቤት፣ ዓመታዊውን የሕግ አውጭዎች ጉባኤ ይጀምራል። ጠቅላይ ሚንስትር ሊ ኪያንግ በበኩላቸው በሥፋት የሚጠበቀውን የመንግሥቱን የ2025 የኢኮኖሚ እድገት እና ሌሎች ቁልፍ የምጣኔ ሃብት ፖሊሲዎች የሚያስረዳውን የመንግሥቱን የሥራ ሪፖርት በምክር ቤቱ የመክፈቻ ጉባኤ ላይ ያቀርባሉ። የዘንድሮው ጉባኤ የሚካሄደው የሃገሪቱ ኢኮኖሚ በእጅጉ በተዳከመበት፣ የአገር ውስጥ ገበያ ፍላጎት በተቀዛቀዘበት፣ ባለ ሃብቱ እና ሸማቹ በኢኮኖሚው ይዞታ ላይ ያለው ዕምነት ባዘቀዘቀበት፣ በንብረት ባለቤትነቱ ዘርፍ የታየው ቀውስ በቀጠለበት ብሎም በዓለም አቀፉ የንግድ ዘርፍ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የተጀመረው የንግድ ጦርነት አንድምታ እያጠላ ባለበት ባሁኑ ወቅት ነው። የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በሁሉም የቻይና ምርቶች ላይ የጣለው ተጨማሪ የ10 በመቶ ቀረጥ ዛሬ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል። በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ፈተናዎች በተደቀኑበት የሚካሄደው የዘንድሮው የብሔራዊ ምክር ቤቱ ጉባኤ፣ የቻይና መሪዎች “የፖለቲካ አንድነት” ፕሮጀክት ለመንደፍ እና አገሪቱ “በሺ ጂንፒንግ አመራር ታላቅ ሃገር ለመሆን በሚያበቃት ትክክለኛ መንገድ ላይ መሆኗን ለማሳየት መልካም አጋጣሚ ለማድረግ ይጠቀሙበታል” ሲሉ ተንታኞች አስተያየታቸውን ፈንጥቀዋል።
በአንድ ወር ዕድሜ ውስጥ አራት ሕጻናት ልጆቻቸውን በወባ ወረርሽኝ መነጠቃቸውን ሳግ እየተናነቃቸው የተናገሩት አቶ ለማ ተፈራ፤ በሚኖሩበት የኦሮሚያ ክልል የቀጠለው ግጭት ባይኖር ኖሮ የልጆቻቸውን ሕይወት ማትረፍ ይቻል ነበር ብለው እንደሚያምኑ ያስረዳሉ። አርሶ አደሩ አክለውም “በግጭቱ ሳቢያ መንደራችን ውስጥ ለወባ መከላከያ የሚረዳው መድኃኒት እና የሕክምና አገልግሎት አልነበረም" ሲሉ በስልክ ላነጋገራቸው የኤኤፍፒ ዘጋቢ አስረድተዋል። በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ ከሚከሰተው ቁጥሩ ከ250 ሚሊዮን በላይ የወባ ተጋላጭ እና በዚሁ ወረርሽኝ ሳቢያ ለሕልፈት ከሚዳረገው ከ600 ሺሕ በላይ ሕዝብ 95 በመቶው አፍሪካውያን መሆናቸውን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል። ባለፉት በርካታ ዓመታት በኦሮሚያ ክልል በመንግሥቱ ኃይሎች እና በአማፂው የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ኦላ) መካከል ተባብሶ የቀጠለው ግጭት የጤና አገልግሎት አቅርቦቱን ክፉኛ እያስተጓጎለ መኾኑን ባለሞያዎች ይገልጻሉ። በርካታ ልጆቻቸውን በወባ ወረርሽኝ ሳቢያ ላጡት እና የሰባት ልጆች አባት እንደሆኑት እንደ አቶ ለማ ላሉ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ገቢ ለሚተዳደሩ አርሶ አደሮች ሁኔታው ቀድሞውንም ከባድ እንደነበር ያስረዱት ሃኪሞች፣ ሌሎች ባለሞያዎች እና የርዳታ ሠራተኞች ለኤኤፍፒ በሰጡት አስተያየት አክለውም፤ የአየር ንብረት ለውጡ እና በአካባቢው የቀጠለው ግጭት ተዳምረው ሁኔታውን እጅግ የከፋ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል። በተያያዘ ዜና ካለፈው ዓመት ጥር ወር አንስቶ እስከ ጥቅምት ድረስ በነበረው ጊዜ ውስጥ ከ7.3 ሚሊዮን በላይ የወባ ወረርሽኝ ተጋላጮች እና 1,157 የሚደርስ የሟች ቁጥር መመዝገቡን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል። ይህም አሃዝ በቀደመው የአውሮፓውያኑ 2023 ከተመዘገበው በእጥፍ መጨመሩ እና በአጠቃላይ በሀገሪቱ ከታየው እና ለሕልፈት ከተዳረጉት ግማሽ ያህሉ በኦሮሚያ መሆኑ ተመልክቷል።
በመተንፈሻ አካላት ሕመም ሳቢያ ጥብቅ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ለሚገኙት የሮማ ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ አባ ፍራንሲስ ለመጸለይ ከዓለም ዙሪያ የተጓዙ፣ በርካታ ምእመናን ዛሬ ማክሰኞ ሮም በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ተሰባስበዋል። ቫቲካን በትላንትናው ዕለት ይፋ እንዳደረገችው በሮሙ የጌሜሊ ሆስፒታል የሚገኙ ሃኪሞች ከሊቀ ጳጳሱ ሳንባ ከፍተኛ መጠን ያለው ፈሳሽ አውጥተዋል። የሕክምና አገልግሎቱ በተደረገላቸው ወቅት አባ ፍራንሲስ እንደነበሩ እና ቆይቶም ሰውነት ውስጥ ዘልቆ ሳይገባ መደረግ የሚችል አጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያ እንደተደረገላቸው ታውቋል። አባ ፍራንሲስ ካለፈው የካቲት 7 ጀምሮ፣ ሁለቱንም ሳንባቸውን ላጠቃ የሳንባ ምች እና የተወሳሰበ የመተንፈሻ አካላት ሕመም ሕክምና ሲደረግላቸው ቆይተዋል። እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር መጋቢት 2013 ጀምሮ የጵጵስና ሥልጣናቸውን የተረከቡት አባ ፍራንሲስ፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ፣ ለረዥም ጊዜ ከአደባባይ ለመራቅ የተገደዱበት የአኹኑ የመጀመሪያው ነው። አባ ፍራንሲስ ሌሊቱን ሙሉ በጥሩ ሁኔታ ተኝተው ማደራቸውን ቫቲካን ይፋ አድርጋለች። ማምሻው ላይም የተሟላ የጤና ሁኔታቸውን የሚያሳይ የሕክምና መረጃ ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል። አባ ፍራንሲስ ገና ወጣት ሳሉ የሳምባቸው ክፍል ተቆርጦ እንዲወጣ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ለመተንፈሻ አካላት ሕመም ሲጋለጡ ቆይተዋል።
አኖራ” የተሰኘው ፊልም እሑድ ምሽት 97ኛው የኦስካር አካዳሚ ሽልማቶች (አካዳሚ አዋርድስ) ላይ የምርጥ ፊልም አሸናፊ ሆኗል። አስቂኝና የመረረ የህይወት የተሞላበት የብሩክሊኑ ፊልም ዳይሬክተር ሾን ቤከርን፣ በሆሊውድ ትልቁንና ተደራራቢውን ሽልማት እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡ እርቃን በሚደነስበት ቤት (strip club) ውስጥ ያጠነጠነው የሲንደሬላ ገጸባህርይ ታሪክ፣ በአዲስና ባልተለመደ አጨራረስ የቀረበ ፊልም ነው፡፡ ከጥንታዊው የሲንደሬላ ተረት በጣም በተለየ መልኩ፣ ነባሩ ታሪክ ላይ ቆሞ፣ አዲሱን ያሳየ ዘመናዊ ፊልም ነው፡፡ በሽልማት ስነስርዐቱ ላይ የነበሩ ብዙ ሰዎች በጣም የተለየ ሥራ ነው ሲሉ አድንቀውታል። ምክንያቱም አቀራረቡ የተለየ ነበር፡፡ ፊልሙ በህይወት ውስጥ ብዙ ፈተናዎች ስላጋጠሟት አንዲት ወጣት ታሪክ ይተርካል። በሲንደሬላ ታሪክ ሲገለጽ እንደቆየው ህይወት ሄዶ ሄዶ ፍፃሜዋ በአስደሳች አስማት ይቋጫል፡፡ የሲንደሬላ ታሪክ እንዲያ ሆኖ ሲተረክ ቢኖርም፣ የአኖራ ህይወት ግን ውስብስብ ሆኖ የህይወት ማለቂያው የተለየ ሊሆን እንደሚችል አሳይቷል፡፡ በተረት ላይ የተመሰረተው ፊልም ህይወትን ግን ተረት ተረት አላደረጋትም፡፡ እውነተኛ ሕይወት ፍጹም ባይሆንም አስደሳች እንደሚሆን አስተምሯል። ፊልሙ ጠንክሮ መሥራት እና መታገል ታሪክን ጠንካራ እንደሚያደርገው አሳይቷል። ሕይወት ውጣ ውረዶች እንዳላት ለሁሉም አስታውሷል፡፡ አሸናፊው ማን እንደሆነ ግራ መጋባት በሰነፈነበት የኦስካር ወቅት፣ አኖራ ባልተጠበቀ መልኩ አሸናፊ ሆኖ ወጥቷል፡፡ በርግጥ ቀደም ሲልም በካነስ ፊልም ፌስቲቫል አሸናፊ ሆኗል፡፡ የቤከር ፊልም ከሩሲያው ባለጸጋ ጋር በፍቅር ነሁልላ ስለከነፈቸው የምሽት ዳንሰኛ ይተርካል፡፡ 6 ሚሊዮን ዶላር ብቻ የፈጀው ፊልም ያን ለመሰለ ድል መብቃቱ አስገርሟል፡፡ አሸናፊዎቹን የሚወስኑት የኦስካር ድምጽ ሰጭዎች ግን እንደ ዊክድ ወይም ዱን ክፍል ሁለት የመሳሰሉትን ትላልቆቹን (“የብላክባስተር”) ፊልሞችን አልመረጡም፡፡ ቤከር ትላንት እሁድ አራት የኦስካር ሽልማቶችን በማሸነፍ እኤአ በ1954 አራት ሽልማቶችን ያሸነፈው ዎልት ዲሲን ያስመዘገበውን ሪከርድ ደግሟል፡፡ ሌላው “ዘ ፍሎሪዳ ፕሮጀክት” የተሰኘው የቤከር ፊልም የተሰራው ፍሎሪዳ ውስጥ ከዲዝኒላንድ ብዙም በማይርቀው ትንሽ ሞቴል ውስጥ ነው። በትላንቱ ምሽት ሌሎች በርካታ ሽልማቶች የተሰጡ ሲሆን “ዘ ፒያኒስት” በተሰኘው ፊልም ላይ አሸናፊ የነበረው ተዋናዩ አድሪያን ብራዲ ተመሳሳይ የኦስካር ሽልማት አሸነፏል፡፡ ብራዲ ያሸነፈው የሆሎኮስት እልቂት እስረኛ ሆኖ በተጫወተው “ዘ ብሩታሊስት” በተሰኘው ሌላ ተመሳሳይ ፊልም ነው፡፡ ሚኪ ማዲሲን “አኖራ” ላይ ባሳየችው ትወና ምርጥ የሴት ተዋናይ በመሆን አሸንፋለች፡፡ ሾን ቤከር ምርጥ ዳይሬክተር ፣ ምርጥ ስክሪፕት ጸሀፊና ምርጥ ኤዲተር በመሆን ተደራራቢ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡ ለምርጥነት ከታጩት 10 ፊልሞች ስምንቱ ቢያንስ አንድ ሽልማት አግኝተዋል፡፡ የሁለት ሽልማቶች አሸናፊ በሆነው ዊክድ ፊልም ላይ የተጫወተችው እውቋ ድምጻዊ አሪያና ግራንዴ እና ሲንቲያ ኢሪቮ የሽልማቱን ስነስርዓቱን የጀመሩት በዚህ ዓመት መግቢያ ላይ በደቡብ ካሊፍሮኒያው እሳት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን በማሰብ ነው፡፡ ግራንዴ Somewhere Over the Rainbow« የተሰኘው ዜማዋን የተጫወተች ሲሆን ኢርቪም የዳያና ሮስን “Home» አዚማለች፡፡ የፊልም ኢንደስትሪው ዙሪያ በጣም አስቸጋሪ የሆኑ በርካታ ነገሮች በመከሰታቸው የዘንድሮው የኦስካር ሽልማት በጣም ያልተጠበቀ ነበር። የቲኬት ሽያጩ ከአምናው በ3 በመቶ የቀነሰ ሲሆን ከኮቪድ ወረርሽኙ በፊት ከነበረው በጣም አንሷል። እ.ኤ.አ. በ2023 የተከሰቱት የሥራ ማቆም አድማዎች በ2024 ፊልሞችን ለመለቀቅ አስቸጋሪ አድርጎታል። ብዙ ስቱዲዮዎች አነስተኛ ፊልሞችን ሰርተዋል፣ ብዙ ሰዎች ሥራቸውን አጥተዋል። በጥር ወር የተከሰቱት የእሳት ቃጠሎዎችም ሁሉንም ነገር የበለጠ ከባድ አድርገውታል።
በምዕራባዊ ጀርመን ማንሃይም ከተማ ውስጥ አንድ መኪና በዓል ለማክበር ወደተሰበሰበው ሕዝብ ጥሶ ገብቶ ባደረሰው ጥቃት አንድ ሰው ሲሞት በርካቶች መቁሰላቸውን የፖሊስ ቃል አቀባይ ዛሬ ሰኞ አስታወቁ። ቃል አቀባዩ ፣የመኪናው አሽከርካሪ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸው ፣ በድርጊቱ ላይ የተሳተፉ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ስለመኖር አለመኖራቸው የታወቀ ነገር አለመኖሩን ተናግረዋል። ፖሊስ ሰዎች ከስፍራው እንዲርቁ ጠይቋል። ክስተቱ የፈጠረው በምዕራብ ጀርመን ራይንላንድ ከተሞች የሚኖሩ ዜጎች የአደባባይ ከብረበዓል ለማክበር ሰልፍ በመውጡበት እና ሕዝብ በተሰበሰበበት ወቅት ነው። ፓራዴፕላትዝ ከተሰኘው የከተማው መሀል አደባባይ ተነስተው፣ ፏፏቴ ወደሚገኝበት ቦታ በመጓዝ ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ፣ አንድ ጥቁር ኤስ.ዩ.ቪ ተሽከርካሪ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ሰዎች ላይ እያበረረ መንዳቱን የሀገር ውስጥ ብዙኅን መገናኛ ዘግበዋል። በጀርመን በዚህ ዓመት በታኅሣሥ ወር በማግደበርግ እና በሙኒክ የመኪና ግጭት የተገደሉትን ጨምሮ፣ የቦንብ ጥቃቶች እንዲሁም በጎርጎሮሳውያኑ ግንቦት 2024 በማንሃይም በጩቤ የተገደለውን ጨምሮ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ተከታታይ የኃይል ጥቃቶችን መፈጸማቸውን ተከትሎ በጀርመን የደኅንነት ጉዳይ አሳሳቢ ሆኗል። እስላማዊ መንግሥት ተብሎ ከሚታወቀው ታጣቂ የሽብር ቡድን ጋራ ግንኙነት ያላቸው የማኅበራዊ መገናኛ፣ በኮሎኝ እና ኑረምበርግ በተደረጉት ዝግጅቶች ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር ከጠየቁ በኋላ፤ ፖሊስ ለዘንድሮው የጎዳና ዐውደ-ትሪዒት በተጠንቀቅ ላይ ነው።
አርተራይተስ ወይም የአጥንት ብግነት መገጣጠሚያ ላይ የሚከሰት እብጠት፣ የአጥንት ድርቅ ብሎ የመሰማት ስሜት፣ የእንቅስቃሴ ማዳገት ምልክቶቹ ሲሆኑ፤ በአለም ላይ ብዙዎችን ለህመም ብሎም ለአካል ጉዳት የዳረገ በሽታ ነው። ከመቶ በላይ የአጥንት ብግነት ዓይነቶች ሲኖሩ ከሁሉም ልቆ የሚታወቀው በእንግሊዘኛው ኦስቴዮ አርተራይተስ ተብሎ የሚጠራው ዓይነት ነው።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ትላንት ቅዳሜ ለእስራኤል አራት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የተፋጠነ ወታደራዊ እርዳታ ለማድረስ መፈረማቸውን ተናግረዋል። በዚህ ዓመት ጥር ወር ላይ ሥራውን የጀመረው የትራምፕ አስተዳደር እስካሁን ድረስ 12 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ወታደራዊ ሽያጭ፤ ለእስራኤል መፍቀዱን ሩቢዮ በመግለጫቸው አስታውቀዋል። መግለጫው አያይዞም “አሜሪካ ለእስራኤል ደህንነት ያላትን የረዥም ጊዜ ቃልኪዳን ለሟሟላት፤ ስጋቶችን ለመከላከል የሚያስችል ዘዴን ጨምሮ ሁሉንም ያሏትን አማራጮች መጠቀሟን ይቀጥላል” ብሏል። ሩቢዮ ለእስራኤል ወታደራዊ ዕርዳታ ለማድረስ የአስቸኳይ ጊዜ ሥልጣናቸውን መጠቀማቸውን ገልጸዋል። በአሁን ሰዓት እስራኤል እና በዩናይትድ ስቴትስ አሸባሪ ተብሎ የተመዘገበው ሀማስ ድርጅት ጋር በቋፍ ላይ ያለ የተኩስ አቁም ውስጥ ይገኛሉ።
የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮለድሚር ዜለንስኪ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ጋራ የተጋጋለ ኃይለ ቃል ከተለዋወጡ ከአንድ ቀን በኋላ ለንደን ሲደርሱ፣ በእንግሊዝ ጠቅላይ ምኒስትር ኪር ስታርመር ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ሁለቱ ሀገራት የዩክሬን የመከላከያ አቅምን ለመደገፍ የ2.84 ቢሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ይፋ ያደረጉ ሲኾን፤ ብድሩ እንዳይንቀሳቀሱ ከታገዱ የሩሲያ ንብረቶች ሽያጭ ትርፍ ላይ የሚከፈል ነው። ሞስኮ ኪየቭን በወረረችበት ወቅት፣ የአውሮፓ ባለሥልጣናት፣ ከሩስያ ውጭ የሚገኙ ማንኛውንም የሩሲያ ንብረቶችን እንዳይንቀሳቀሱ በማገድ፣ ሞስኮን ለመቅጣት መወሰናቸው ይታወሳል። ዜለንስኪ በዶውኒንግ ጎዳና ከአቻቸው ስታመር ጋራ ፎቶ ለመነሳት ለአፍታ የቆሙ ሲሆን፤ እንግሊዛውያን በጩኸት ድጋፋቸውን አሳይተዋቸዋል። ስታመርም ለዜለንስኪ “በዳውኒንግ ጎዳና ሁሌም እንቀበሎታለን” ብለዋቸዋል። አክለውም፣ «ከቤት ውጭ በጎዳናው ላይ እንደሰሙት፣ በዩናይትድ ኪንግደም ሙሉ ድጋፍ አሎት፣ ምን ዐይነት ጊዜ ቢወስድም ሁሌም ከዩክሬን እና ከእርሶ ጋራ እንቆማለን» ብለዋቸዋል። ሁለቱ መሪዎች 75 ደቂቃ የፈጀ ውይይት ካደረጉ በኋላ ስታመር ዜለንስኪን እስከ መኪናቸው ድረስ ሸኝተዋቸዋል። ምንም እንኳን የትረምፕ እና ዜለንስኪ ውይይት ባለመግባባት ቢጠናቀቅም፣ የትረምፕ ድጋፍ ለዩክሬን በእጅጉ አስፈላጊ መኾኑን ዜለንስኪ ትላንት ቅዳሜ አጽንኦት ሰጥተውበታል።
በዩጋንዳ ሁለተኛው የኢቦላ ታማሚ የአራት ዓመት ህፃን ህይወቱ ማለፉን የአለም ጤና ድርጅት፤ የሀገሪቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን ጠቅሶ ገልጿል። ሁኔታው በዩጋንዳ የተረጋገጠ የኢቦላ ሟቾችን አሃዝ አስር አድርሶታል። በምሥራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር መዲና ካምፓላ ሙላጎ ብሔራዊ ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ የሚያገለግል አንድ ወንድ ነርስ ከሞተ በኋላ፤ ሀገሪቱ ባለፈው ጥር ወር በአደገኛ ሁኔታ ተላላፊ፣ ገዳይ እና ብዙ የደም መፍሰስ የሚያስከትል በሽታ መከሰቱን አስታውቃለች። የዓለም ጤና ድርጅት የዩጋንዳ ጽህፈት ቤት ትላንት ቅዳሜ በኤክስ ማኅበራዊ ድረገጽ ላይ ዘግይቶ እንዳስታወቀው፤ ሚኒስትሩ ባለፈው ማክሰኞ “በሙላጎ ሆስፒታል ውስጥ የአራት ዓመት ተኩል ዓመት ሕፃን በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወቱ አለፏል” ማለቱን ሪፖርት አድርጓል። ሙላንጎ የኢቦላ ህክምና ሪፈራሎች የሚመጡበት በሀገሪቱ ያለ ብቸኛ ብሔራዊ ሆስፒታል ነው። ሚኒስቴሩ በዚህ ዓመት በየካቲት ወር በእንክብካቤ ላይ ያሉ ስምንቱ የኢቦላ ታማሚዎች ታክመው ሲወጡ፤ በተጨማሪም 265 የሚሆኑና ከእነሱ ጋር ንክኪ የነበራቸው ግለሰቦች በካምፓላ እና በሌሎች ሁለት ከተሞች ጥብቅ ማቆያ ውስጥ መቆየታቸውን አስታውቋል። የኢቦላ ምልክቶች ትኩሳት፣ ራስ ምታት እና የጡንቻ ህመም ሲሆኑ፤ ቫይረሱ የሚተላለፈው ከተበከሉ የሰውነት ፈሳሾች እና አካላት ጋር በሚደረግ ንክኪ ነው።
የእስራኤል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፤ በእስራኤል እና ሀማስ መካከል የተደረሰው ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ሊያበቃ የሰዓታት ጊዜ በቀሩት ወቅት፤ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልዑክ የሆኑት ስቲቭ ዊትኮፍ፤ በረመዳን እና በፋሲካ የጾም ወቅት በጋዛ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ያቀረቡትን ሀሳብ ሀገራቸው መቀበሏን እሁድ ማለዳ አስታውቋል። ዊትኮፍ ባቀረቡት ዕቅድ መሰረትም በመጀመሪያው ቀን በጋዛ በህይወትም ያሉት እና ከሞቱትም ታጋቾች ግማሾቹ እንደሚለቀቁ የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት የገለጸ ሲሆን፥ ቀሪዎቹ ታጋቾችም ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ እንደሚለቀቁ ገልጿል። ዊትኮፍ በቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመነጋገር ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልግ በመረዳታቸው፤ አሁን ያለውን የተኩስ አቁም ለማራዘም ሀሳብ አቅርበዋል ሲል የኔታኒያሁ ጽህፈት ቤት አስታውቋል። በዩናይትድ ስቴትስ አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው የሐማስ ቡድን ቃል አቀባይ ሀዜም ቃሴም ከቅዳሜ ዕለት ቀደም ብሎ ቡድኑ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያ ምዕራፍ መራዘሙን ውድቅ ማድረጉን ቢገልጹም የዊትኮፍ እቅድን በግልፅ አልጠቀሱም። እስራኤል በዊትኮፍ እቅድ ላይ ሀማስ ከተስማማ ወዲያውኑ ድርድር ታካሂዳለች ሲል የኔታኒያሁ ቢሮ አስታውቋል። “በስምምነቱ መሰረት እስራኤል ከ42ኛው ቀን በኋላ ድርድሩ ውጤታማ እንዳልሆነ ከተሰማት ወደ ጦርነት መመለስ ትችላለች” በማለት የኔታኒያሁ ጽህፈት ቤት ሀማስ ስምምነቱን ጥሷል ሲል ከሷል። ሁለቱም ወገኖች አንዱ ሌላኛውን ስምምነቱን ጥሷል በሚል ሲከሱ ቆይተዋል። ስለድርድሩ የሚያውቁ ሁለት የፍልስጤም ባለሥልጣናት ለሮይተርስ እንደተናገሩት እስራኤል ወደ ሁለተኛው የስምምነት ምዕራፍ ለመግባትም ሆነ በዚህ ጉዳይ ላይ ድርድር ለመጀመር ፈቃደኛ አልሆነችም ብለዋል። በምትኩ፣ እስራኤል ሳምንታቶቹን በማራዘም ለተራዘመው ለእያንዳንዱ ሳምንት በርካታ ታጋቾችን እና አካላት እንዲለቀቁላት ጠይቃለች። ቅዳሜ ዕለት የሀማስ ታጠቂ ክንፍ የእስራኤል ታጋቾች አሁንም በጋዛ በእስር ላይ እንደሚገኙ የሚያሳይ ቪዲዮ የለጠፈ ሲሆን፤ የተቀሩት ታጋቾች ሊፈቱ የሚችሉት በጎርጎርሳውያኑ ጥር 19 የተጀመረው የተኩስ አቁም ስምምነት ሲጠናቀቅ ብቻ መሆኑን አፅንዖት ሰጥቷል። የተኩስ አቁም ንግግሮች በቅርቡ በካይሮ ቢደረጉም ስምምነት ላይ ሳይደረስ ተጠናቀዋል። በተያያዘ ዜና ዛሬ እሁድ እስራኤል ሀማስ በቋፍ ላይ ያለውን የተኩስ አቁም የማይቀበል ከሆነ ወደ ጋዛ ሰርጥ የሚገቡ ምርቶችና ሸቀጦችን እንደምትገድብ እና “ተጨማሪ መዘዞች” እንደሚከተሉ አስታውቃለች። ሀማስ እስራኤል ጫፍ ላይ ያለውን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማደናቀፍ እየሞከረች ነው በማለት የከሰሰ ሲሆን፤ ዕርዳታውን ለማቆም የወሰነችው ውሳኔም “ርካሽ ዘረፋ፣ የጦር ወንጀል እና ግልጽ ጥቃት” ነው ብሏል።
ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ነጻነት ለማስከበር ለመጀመሪያ ጊዜ “ብሔራዊ ሆነው” የተነሡበትና በኅብረት ተዋግተው ያሸነፉበት፣ 129ኛው የዓድዋ ድል በዓል በትግራይ ክልል በሶሎዳ ተራራ ላይ ዛሬ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም ተከበረ። በበዓሉ አከባበር ላይ የተገኙት፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ምኒስትር ዴኤ'ታ እንደገና አበበ፣ የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ እና ጭቁን ሕዝቦች ዐዲስ ምዕራፍ የከፈተ እንደነበር አስታውሰዋል። በየዓመቱ በአገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት የሚዘከረው የዓድዋ ድል፣ መከበር የጀመረው ጦርነቱ ከተደረገበት 1888 ዓ.ም. ከሰባት ዓመት በኋላ ነው፡፡ ዛሬ በሶሎዳ ተራራ ላይ በተከበረው በዓል ላይ፣ በጦርነቱ ጊዜ ኢትዮጵያውያን በሕብር አድርገውት የነበረውን ተሳትፎ የሚያስታውሱ የኪነጥበብ ሥራዎች ቀርበዋል። የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዘም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አፅብሃ ገብረእግዚአብሄር፣ የዓድዋ ድል በዓል ለሰላም፣ አንድነት እና ብሩህ ተስፋ፣ በሚል መሪ ሐሳብ በመከበር ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ እና የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮለድሚር ዜለንስሊ ውይይት ወደ ተጋጋለ እሰጥ አገባ ከተቀየረ እና ትረምፕ ዜለንስኪን «አክብሮት የጎደለው» ሲሉ ከተናገሯቸው በኋላ በመላ አህጉሪቱ የሚገኙ የአውሮፓ መሪዎች ከዩክሬን ጎን ቆመዋል። የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ካጃ ካላስ ፣ «አኹን ነጻው ዓለም አዲስ መሪ እንደሚያስፈልገው ግልጽ ኾኗል» ብለዋል። በዚኹ በማኅበራዊ ሚዲያ ኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጹሑፍ፣ «ዩክሬን የአውሮፓ ነች፣ ከዩክሬን ጎን እንቆማለን» ብለዋል። የጀርመን ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ «ዩክሬን በጀርመን ላይ መተማመን ትችላለች - በአውሮፓም ላይ እንዲኹ» በማለት ኤክስ ላይ ሲጽፉ፣ የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ደግሞ «ዩክሬን- ስፔን ከጎንሽ ትቆማለች” ብለዋል። የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ቱስክ »ውድ ዜለንስኪ እና ውድ የዩክሬን ጓደኞቻችን ፣ ብቻህን አይደለህም« ሲሉ በኤክስ ላይ ጽፈዋል። የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው ለፖርቹጋል ጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ »አጥቂዋ ሩሲያ ነች። ተጠቂው የዩክሬን ሕዝብ ነው” ብለዋል። የፊንላንድ፣ ኔዘርላንድስ፣ ቼክ ሪፐብሊክ እና ኖርዌይን ጨምሮ ሌሎች የአውሮፓ መሪዎችም ለዩክሬን ድጋፋቸውን ለመስጠት በማኅበራዊ ገጾቻቸው ላይ ጽፈዋል። ኖርዌይም በማኅበራዊ ሚዲያ ለዩክሬን ድጋፏን ገልጻለች። ሆኖም ዩክሬንን የደገፉት ሁሉም የአውሮፓ መሪዎች አይደሉም፣ ለኪቭ የሚሰጠውን ርዳታ ለረዥም ጊዜ ሲቃወሙ የቆዩት የሃንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን፣ ምንም እንኳን ሁኔታውን ለሌሎች ለመቀበል ቢከብዳቸውም ፕሬዝደንት ትረምፕ ለሰላም የቆሙ ናቸው። እናመሰግናለን ፕሬዝደንት!” ብለው ጽፈዋል።
ፖለቲከኛ እና የቀድሞ ጋዜጠኛ የነበሩት ኬሪ ሌክ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለምአቀፍ ሚዲያ ኤጀንሲ (ዩ.ኤስ.ኤ.ጂ.ኤም.) አማካሪ ኾነው መሾማቸውን ተቋሙ ፣ ሐሙስ የካቲት፣ 20 ቀን 2017 ዓ.ም አስታወቀ። ላለፉት 30 ዓመታት በጋዜጠኝነት ያገለገሉት ኬሪ ሌክ፣ በመንግሥት ለሚደገፈውና ዓለም አቀፍ ሥርጭት ላለው አሜሪካ ድምፅ በዲሬክተርነት እንዲሾሙ መታጨታቸውን፣ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ፣ በታኅሣሥ ወር 2017 ዓ.ም አስታውቀው ነበር። ኾኖም የዩናይትድ ስቴትስ ዓለምአቀፍ ሚዲያ ኤጀንሲን (ዩ.ኤስ.ኤ.ጂ.ኤም.) በዋና ሥራ አስፈፃሚነት እንዲመሩ በትረምፕ የተመረጡት፣ ወግ አጥባቂ ሐሳቦች አራማጅ እና ጸሐፊው ኤል ብሬንት ቦዜል ሹመት፤ የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት)ማረጋገጫ በመጠባበቅ ላይ በመኾኑ የኬሪ ሌክ ሹመት አጓቶታል። ሚዲያ ኤጀንሲንው፣ የተለያዩ እህትማማች ተቋማት ኃላፊዎችን መሾም ወይም ማሰናበትን ጨምሮ ከዋና ሥራ አስፈጻሚ ጋራ አብሮ የሚሠራ፣ ከሁለቱ ፓርቲዎች የተዋቀረ ቦርድ እስኪሰየም በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። የኤጀንሲው የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አማንዳ ቤኔት፣ ሥልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኾነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ሮማን ናፖሊ፣ ሌክ በልዩ አማካሪነት መቀላቀላቸውን ለተቋሙ ሠራተኞች በላኩት ኢሜል አስታውቀዋል። “ከሁለት ዐስርት ዓመታት በላይ በታላላቅ ብዙኅን መገናኛ ውስጥ በዘጋቢነት እና ዜና አቅራቢነት ያገለገሉት ሌክ፣ በብሮድካስት ጋዜጠኝነት ውስጥ ብዙ ልምድ አላቸው” በማለት ናፖሊ አክለዋል። ናፖሊ የሌክን ስኬት በማጉላትም፣ ከዚኽ ቀደም ለኹለት የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች ቃለ መጠየቅ ማድረጋቸውን እና በዓለም አቀፍ ዘገባዎች ምክኒያት ሁለት ጊዜ የኤሚ ሽልማት መቀበላቸውን፣ ጠቅሰዋል። «ኬሪ የትረምፕ አስተዳደር ከፍተኛ አማካሪ እንደመኾናቸው፣ የሚዲያ ኤጀንሲውን፣ የእህትማማች ተቋማቱን እና የፈንዱን ሥራ ለማቀላጠፍ፣ የሚያስፈልጉትን ፖሊሲዎች እና ስልቶች ተግባራዊ ለማድረግ ያግዛሉ»ሲሉ ናፖሊ በኢሜል መልዕክታቸው ጠቅሰዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ዓለምአቀፍ ሚዲያ ኤጀንሲ (ዩ.ኤስ.ኤ.ጂ.ኤም.)፣ ከ420 ሚሊዮን በላይ የሚኾኑ ዓለም አቀፍ አድማጮችና ተመልካቾችን ያላቸው፣ በዜና ዘገባ እና ቅድመ ምርመራ ወይም ሳንሱርን በመዋጋት ላይ ትኩረታቸውን አድርገው የሚሠሩ በርካታ ተቋማትን ይቆጣጠራል። በዩ.ኤስ.ኤ.ጂ.ኤም. ሥር የሚገኙ እነዚኽ እህትማማች ድርጅቶች፣ የአሜሪካ ድምፅ፣ የኩባ ብሮድካስቲንግ ቢሮ (Cuba Broadcasting) እና ለትርፍ ያልተቋቋመው የነፃ አውሮፓ ራዲዮ ወይም ራዲዮ ሊበርቲ (Free Europe/Radio Liberty)፣ የነፃ እሥያ ራዲዮ(Radio Free Asia)፣ የመካከለኛው ምሥራቅ ብሮድካስቲንግ መረብ እና የኦፕን ቴክኖሎጂ ፈንድ እና የፍሮንት ላይን ፈንድን ናቸው። የዩናይትድ ስቴትስ ዓለምአቀፍ ሚዲያ ኤጀንሲ (ዩ.ኤስ.ኤ.ጂ.ኤም.)፣ የሕዝብ ጉዳዮች ክፍል የኬሪ ሌክን ሹመት በተመለከተ ለአሜሪካ ድምፅ ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጠም። «ፋየርዎል» በመባል የሚታወቀው የኢዲቶሪያሉ ገለልተኝነት መጠበቂያ፣ ዩ.ኤስ.ኤ.ጂ.ኤም በሚያስተዳድራቸው ብዙኅን መገናኛ የጋዜጠኝነት ሥራ ውጤት ላይ ጣልቃ እንዳይገባ ይከለክላል። ሌክ በዓመታዊው የወግ አጥባቂ አቀንቃኞች የፖለቲካ ጉባኤ ላይ በሰጡት አስተያየት የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ሚዲያ የቀረበበትን ትችት በንግግራቸው ዳሰዋል፡፡ ሌክ ለታዳሚው እንደ ቪኦኤ ዲሬክተር የዜና ተቋሙ “ትክክለኛ እና ታማኝ ዘገባዎችን” ማዘጋጀቱ ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ሌክ አክለው ፣ “የፊታችን ሰኞ 83 ዓመት የሚኾነው ቪኦኤ አሜሪካን ታሪክ ለዓለም ሲያቀርብ ቆይቷል። አንዳንድ ጊዜ በዜና ሽፋኑ አስደናቂ ሲኾን በሌሎች ወቅቶች ደግሞ አሳዛኝ ነበር” ብለዋል፡፡ አያይዘውም “እኛ የምንዋጋው የመረጃ ጦርነት ነው፤ በመሆኑም ከእውነት የተሻለ መሳሪያ የለም፣ እናም ቪኦኤ ይህ መሳሪያ ሊሆን ይችላል ብዬ አምናለሁ” በማለት ተናግረዋል፡፡ የዜና ጣቢያው እንዲዘጋ ከጠየቁት መካከል የትራምፕ ልዩ አማካሪ ኢላን መስክ ይገኙበታል። ይሁን እንጂ ሌክ “የትራምፕ ቴሌቭዥን አንሆንም” በማለት የተናገሩ ሲኾን፤ “ሆኖም ግን ዲጂታል ኬብል ቴሌቭዥን እንደማንኾን ግን እርግጠኛ ነው” ብለዋል፡፡ አክለውም “ትረምፕን ምክኒያታዊ ባልኾነ መልኩ መተቸትን ከሲ.ኤን.ኤን፣ ኤም.ኤስ.ኤም.ቢ.ሲ፣ 60 ደቂቃ፣ ዘ ዋሺንግተን ፖስት እና ከኒውዮርክ ታይምስ ልታገኙ ትችላላቹ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ኬሪ ሌክ በኮቪድ 19 ወረርሽኙ ወቅት የተሳሳተ መረጃ ነው ብለው ባመኑት መረጃ ምክንያት ከአሪዞና የዜና ጣቢያ ሥራቸውን ለቀዋል። በኋላም ለአሪዞና ሀገረ ገዥነት ተወዳድረ ያልተሳካላቸው ሲኾን ሽንፈታቸውን ባለመቀበል ክስ መስርተዋል። በመቀጠልም ለግዛቱ ሴናተርነት ያደረጉት ውድድርም አልተሳካላቸውም።