እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2024፣ በታሪክ ታይቶ በማያውቅ መልኩ ከ60 በላይ ሀገሮች ምርጫ ያካሄዱበት ዓመት ነበር። ምርጫዎቹን ተከትሎ ከድምፅ አሰጣጥ እና የምርጫ ውጤት ጋር የተያያዙ ከ160 በላይ ተቃዎሞዎች መቀስቀሳቸውንም ካርኒጅ የተሰኘው ዓለም አቀፍ የተቃውሞ መቆጣጠሪያ ማዕከል አስታውቋል። ከቁጥሩ በላይ ግን ዓመቱን የተለየ የሚያደርገው፣ ከተለመደው ወጣ ባለ መልኩ፣ በስልጣን ላይ የነበሩ በርካታ መሪዎች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ አለመቻላቸው መሆኑን ፒው የተሰኘው የጥናት ተቋም አመልክቷል። የኢትዮጵያ እና የሶማሌላንድ ስምምነት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2024 የጀመረው ባልተለመዱ እና ባልተጠበቁ ፖለቲካዊ ክስተቶች ነው። ከጅምሩ አዲሱን ዓመት ለመቀበል ዓለም ትኩረቱን በበዓሉ ዝግጅት ላይ ባደረገበት እለት፣ ኢትዮጵያ የባህር በር የምታገኝበት የመግባቢያ ሰነድ ከሶማሌላንድ መሪዎች ጋር መፈራረሟን አስታወቀች። በወቅቱ ለ50 ዓመት የሚዘልቅ ሊዝ እና እየታደሰ እንደሚቀጥል የተገለጸው ስምነት፣ ከባህር በር በተጨማሪ ኢትዮጵያ የጦርና የንግድ ሠፈር እንዲኖራት የሚፈቅድ መሆኑ ተገልጾ ነበር። ሶማሌላንድ በበኩሏ በምትኩ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ እውቅና ልትሰጣት መስማማቷን አስታውቃ ነበር። ወዲያውኑ ግን የሶማሌላንድ ግዛት የአስተዳደሯ አካል መሆኑን የምትገልጸው ሶማሊያ «ስምምነቱ ሕጋዊ መሠረት የሌለው እና ሊዓላዊነቷን እንደሚዳፈር» በመግለፅ ተቃውሞዋን አሰማች። በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውን አል-ሻባብ ለመዋጋት በሀገሯ የሚገኙ ወታደሮች ለቀው እንዲወጡ እንደምታደርግም ዛተች። በዚህ ምክንያት 2024 በአፍሪካ ቀንድ የቀውስ ስጋት የፈጠረውን ይህን ውጥረት ለማርገብ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጥረቶች የተካሄዱበት ሆኖ አልፏል። በዓመቱ ማገባደጃ ላይ በቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን አደራዳሪነት፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከሶማሌላንድ ጋር በተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ምክንያት ለአንድ ዓመት ገብተውበት የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ለማቆም ስምምነት ማድረግ ቢችሉም፣ አሁንም ውጥረቱ ሙሉ ለሙሉ አልበረደም። ብሪክስ በ2024 መግቢያ የዓለም ትኩረት የሳበው ሌላው ጉዳይ፣ ኢትዮጵያ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤም ሬትስ በመልማት ላይ ያሉ አገሮች የመሰረቱትን 'ብሪክስ' የተሰኘ ቡድን መቀላቀላቸው ነው። የምዕራባውያን አገሮች፣ እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የዓለም ባንክ የመሳሰሉ ለመንግሥታት ብድር የሚሰጡ ጠቃሚ ዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ ያላቸው ጫና የወለደውን ይኽን ቡድን ኢትዮጵያ የተቀላቀለችውም፣ በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ምክንያት መሆኑን፣ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሞያዎች ማህበር የምርምር እና ፖሊሲ ትንተና ዳይሬክተር እና የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ ዶክተር ደግዬ ጎሹ አመልክተው ነበር። የአባላቱ ቁጥር ዘጠኝ የደረሱት ብሪክስ በዚህ አመት የተለያዩ ጉባዔዎችን ያካሄደ ሲሆን በሀገራቱ መካከል በሚደረጉ የንግድ ልውውጦች ብሄራዊ ገንዘባቸውን እንዲጠቀሙ የሚያስችል አሰራር ለመፍጠር በመሥራት ላይ መሆናቸውንም በዚህ እየተገባደደ ባለው ዓመት አስታውቀዋል። ሱዳን የአውሮፓውያኑ 2024፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶማሊያ እና ኤርትራ በሚገኙበት የአፍሪካ ቀንድ እየተባባሰ ከሄደው ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት በተጨማሪ፣ በሀገር ውስጥ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች የቀጠሉበት እና እና አዳዲስ የእርስ በእርስ ግጭቶችም የተፈጠሩበት አመት ነበር። ከቀጠናው ወጣ ሲል ደግሞ በሰሜን ምስራቅ በምትገኘው ሱዳንም፣ በሀገሪቱ ጦር ሰራዊት እና በፈጥኖ ደራሹ ኃይል መካከል የሚካሄደው ጦርነት በዚህ አመት አንደኛ አመቱን አስቆጥሮ ቀጥሏል። በዋና ከተማዋ ካርቱም ጨምሮ፣ በዳርፉር፣ ኮርዶፋን እና ሌሎች ክልሎች ከባድ ውጊያዎች ተካሂደዋል። ለ20 ወራት በሱዳን የዘለቀው ይህ አስከፊ ጦርነት እስከዛሬ ከተመዘገቡት ሁሉ ትልቁ ሰብዓዊ ቀውስ ሆኖ መመዝገቡን የዓለም ነፍስ አድን ኮሚቴ ያስታወቀ ሲሆን ከ11 ሚሊየን በላይ ዜጎች በሀገር ውስጥ እና በውጪ ሀገራት መፈናቀላቸውን የመንግስታቱ ድርጅት ገልጿል። ‘የረሃብ ክትትል ኮሚቴ’ በሚል የሚታወቀው ተቋም ከሳምንታት በፊት ይፋ ባደረገው ሪፖርት ከበባ ውስጥ ባለችው የሰሜን ዳርፉር መዲና አል ፋሽር ውስጥ በሚገኙ ሁለት መጠለያዎች፣ እንዲሁም በደቡብ ኮርዶፋን ግዛት በሚገኙ ሌሎች ሁለት አካባቢዎች ረሃብ መስፋፋቱንም አስታውቋል። ወደ 26 ሚሊዮን የሚጠጋ የሱዳንን ሕዝብ ለከባድ ረሃብ ያጋለጠውን አስከፊ ቀውስ ለማርገብ የሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳ መሪዎች የሚገኙበት ስብስብ በዚሁ ዓመት ስብሰባ አካሂዶ ነበር። በመስከረም ወር በኒውዮርክ የተካሄደው 79ኛው የዓለም መሪዎች ጉባዔ አጀንዳ ከነበሩ ርዕሶች አንዱም ይኽ የሱዳን ቀውስ ነው። ሆኖም የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት መቋጫ ሳያገኝ አመቱ ተገባዷል። ምዕራብ አፍሪካ 2024 ከሱዳን በተጨማሪ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ቀውሶች፣ ጥቃቶች እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች ተስተናግደውበታል። ለምሳሌ በየካቲት ወር በሰሜናዊ ቡርኪናፋሶ በሚገኙ ሦስት መንደሮች ላይ የእስላማዊ የጽንፈኛ ኃይሎች ባደረሱት ጥቃት ከ170 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። መጋቢት ወር ላይም በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ ታቂዎች በአንድ ትምህርት ቤት ላይ ወረራ አካሂደው 280 ተማሪዎችን አግተው መውሰድ ችለዋል። ይህም እ.አ.አ በ2014 የቦኮ ሃራም ታጣቂዎች ከቺቦክ መንግደር በመቶዎች የሚቆጠሩ ልጃገረዶችን ካገቱበት ጊዜ አንስቶ፣ ከናይጄሪያ ትምህርት ቤቶች የታገቱ ተማሪዎች ብዛት ከ1ሺህ 400 እንዲበልጥ አድርጎታል። የኔዘርላንድ የጥናት ተቋም የሆነው ክሊነንዳል ኢንስቲትዩት አደገኛ የሆኑ ግንኙነቶችን አስመልከቶ ግንቦት ወር ላይ ይፋ አድርጎት በነበረው የጸጥታ ሪፖርት፣ ታጣቂዎች ከሳህል ቀጠና በባህር ዳርቻ ወደሚገኙ የበለጸጉ ሀገራት እየፈለሱ መሆኑን አመላክቷል። የኢኮኖሚ እድሎች እና ከፍተኛ የድህነት ደረጃ፣ ታጣቂዎች በቀጠናው በቀላሉ ሰዎችን እንዲመለምሉ እና እራሳቸውን እንዲያሳድጉ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም ሪፖርቱ ጨምሮ ገልጿል። የሰሃራ በረሃን አብዛኛውን ክፍል የሚሸፍነው የአፍሪካ ሳህል ቀጠና የዓለም አቀፍ አሸባሪዎች ማዕከል መሆኑን የዓለም ሽብርተኝነት መረጃ ጠቋሚ እ.አ.አ በ2023 ያወጣው መረጃ ያሳያል። ከቅርብ አመታት ወዲህ በቀጠናው የተካሄዱት መፈንቅለ መንግሥቶች የአካባቢውን የጸጥታ ሁኔታ እና ለታጣቂዎቹ ይሰጡ የነበሩ ምላሾችን ክፉኛ እንደጎዱት ባለሙያዎች ይናገራሉ። ይህም በ2024 ተባብሶ ቀጥሏል። የአየር ንብረት ለውጥ ከፖለቲካ አለመረጋጋቱ ጎን ለጎን በ2024 ፈታኝ ሆኖ የቀጠለው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች ናቸው። በደቡብ ኢትዮጵያ፣ ጎፋ ዞን ሐምሌ ወር ላይ የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ከ250 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት አስታውቋል። በዓመቱ መግቢያ በዘነበው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት የኮንጎ ወንዝ ባለፉት ስድስት አስርት አመታት ውስጥ ባልታየ ሁኔታ በመሙላቱ፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በኮንጎ ሪፐብሊክ ያስከተለው ጎርፍ ከ300 በላይ ሰዎች ህይወት ሲያጠፋ ከ350 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ የሰብዓዊ እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል። በሚያዚያ ወር በምስራቅ አፍሪካ የጣለው ከፍተኛ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍም በታንዛኒያ ከ155 በላይ ሰዎችን ሲገድል፣ ከ200 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በደቡብ አፍሪካ ባለፉት 40 አመታት ውስጥ አለመታየቱ የተገለጸ ድርቅም በአንጎላ፣ ቦትስዋና፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ ናሚቢያ፣ ዛምቢያ አንድ ማዳጋስካር ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል። እነዚህ ክስተቶች ታዲያ በህዳር ወር አዘርባጃን ዋና ከተማ፣ ባኩ ውስጥ በተካሄደው 29ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባዔ መፍትሄ ይገኝላቸዋል ተብሎ ተጠብቆ ነበር። በአየር ንብረት ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ላሉ ታዳጊ ሀገራት ለመሰጠት ቃል የተገባው የገንዘብ ድጋፍም ወደ 1.3 ትሪሊየን ዶላር ያድጋል የሚል ተስፋ ተጥሎ ነበር። ሆኖም ከበለጸጉት ሀገራት የሚጠበቀው የገንዘብ ድጋፍም ሆነ፣ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንሱ የሚጠበቀው የአየር በካይ ጋዞችን ልቀት አለመሳካት ብዙዎችን አስቆጥቷል። መካከለኛው ምስራቅ ከአፍሪካ አህጉር ወጣ ስንል ደግሞ፣ 2024 በዋናነት በዩክሬን፣ በጋዛ፣ በሊባኖስ እና በቅርቡ ደግሞ በሶሪያ የተደረጉ ጦርነቶች የተሞላ ነበር። በተለይ በአመቱ ማገባደጃ በሶሪያ የተደረገው ውጊያ ሀገሪቱን ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ ላስተዳድረው የአሳድ ቤተሰብ አገዛዝ ውድቀት ሆኗል። እ.አ.አ በጥቅምት 2023 የሐማስ ታጣቂ ቡድን ያደረሰውን ጥቃት ተክትሎ፣ እስራኤል ከአንድ አመት በላይ በጋዛ ባደረገችው ዘመቻ ከ45 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጋዛ ጤና ሚኒስትርን ጠቅሶ ዘግቧል። እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ወች ያሉ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ተቋማትም እስራኤል ጋዛ ውስጥ፣ በፍልስጤም ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት አድራጎት ፈፅማለች ሲሉ በጦር ወንጀል እና በሰው ልጆች ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎች ከሰዋታል። በ2024 መጀመሪያ ጥር ወር ላይ ደቡብ አፍሪካ ተመሳሳይ ወንጀሎችን ጠቅሳ እስራኤልን በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ከሳ ነበር። ክሱን የተቀበለው ፍርድቤቱም፣ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ፣ የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትራቸው ዮአቭ ጋላንት እና የሐማስ ባለስልጣናትን በጦር ወንጀለኦች በመምክሰስ የእስር ማዘዣ አውጥቶባቸዋል። እስራኤል በጋዛ ላይ የጀመረችውን ጥቃት አጠናቅራ በመካከለኛው ምስራቅ ወዳሉ ሌሎች ሀገራት ፊቷን ያዞረችውም በዚሁ አመት ነው። ሊባኖስ በሚገኘው የሂዝቦላህ ታጣቂዎች ላይ ባደረሰችው ጥቃትም ከ3ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ከእነዚህ ውስጥ በዋና ከተማዋ ቤይሩት ጨምሮ፣ በሊባኖስ የተለያዩ ከተሞች በቤት ሰራተኝነት የሚተዳደሩ በሺዎች የሚቅጠሩ ኢትዮጵያውያንም ይገኙበታል። በዚህ ምክንያት በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ያመለከቱት በቤይሩት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያኖች የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ሀገራቸው እንዲመልሳቸው ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን እያቀረቡ ይገኛሉ። የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የሚካሄደው ጦርነት ያላሸናፊ እና ያለተሸናፊ በ2024ም ቀጥሏል። በላቁ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ፣ ሩሲያ ወደፊት ለመግፋት የምታደርጋቸው ሙከራዎች እና የዩክሬን መልሶ የማጥቃት ዘመቻዎች በንፁሃን ዜጎች እና በሲቪል ተቋማት ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ቀጥለዋል። አንዳቸውም ግን የማሸነፍ ወይም ወደ ሰላም ድርድር የመምጣት ምልክት አላሳዩም። ይልቁኑም ሁለቱም ሀገራት በ2024 በነበራቸው የውጊያ ሂደት የሰው አልባ አውሮፕላን አጠቃቀማቸው በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ እስካሁን 1.5 ሚሊየን ድሮኖችን መግዛታቸው ተመልክቷል። ስፖርት 2024 በአብዛኛው ጦርነቶች፣ መፈናቀሎች፣ ረሃብ፣ እና በአየር ንብረት ቀውስ በደቀኗቸው ፈተናዎች የተሞላ ይሁን እንጂ፣ ሙሉ ለሙሉ ግን የጨለመ አልነበረም። በየካቲት ወር አንድ ወር ለተጠጋ ጊዜ የተካሄደው የአፍሪካ ሀገራት የእግር ኳስ ዋንጫ ፍልሚያ የብዙ ኳስ አፍቃሪያንን ቀልብ የሳበ ሆኖ አልፏል። ውድድሩንም አዘጋጇ ሀገር ኳትዲቯር ተፎካካሪዋን ናይጄሪያን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ፣ በአሸናፊነት አጠናቃለች። ከ60ሺ በላይ ህዝብ በሚያስተናግደው አላሳን ዋተራ (ኢቤምፒ) ስታዲየም የተከናወነውን የፍጻሜ ጨዋታ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ አፍሪካዊያን በቀጥታ ስርጭት የተከታተሉት ሲሆን የዘንድሮውን የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ ለማዘጋጀት ኳትዲቯር 1 በሊየን ዶላር ገደማ እንዳወጣች ተመልክቷል። ሐምሌ ላይ በፓሪስ የተካሄደው የበጋ ኦሎምፒክስ ፉክክርም ዓለምን ያስደመሙ አስደናቂ የአትሌቲክስ ትዕይንቶች የታዩበት ሆኖ የተጠናቀቀው በተሰናባቹ 2024 ነበር። በመክፈቻው ስነስርዓት ፓሪስ፣ የሴይን’ን ወንዝ ተከትሎ ባለው ሥፍራ፣ እጅግ ያማረ፣ በከዋክብት የደመቀ እና ታሪካዊ የውበት እና የለውጥ መፍለቂያ ስሟን ያንጸባረቀ ልዩ የመክፈቻ ዝግጅት ያሳየች ሲሆን፣ በዓለም ዙሪያ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ከሚጫወቱ ድምጻውያን ከፍተኛ ተደማጭነት ያላት ማሊያዊ-ፈረንሳዊቷ የፖፕ ሙዚቃ ኮከብ አቀንቃኝ አያ ናካሙራ፣ በወርቃማ ቀለም የተንቆጠቆጠ ልብስ ለብሳ፣ በዳንሰኞቿ እና በፈረንሳይ ብሄራዊ የክብር ዘብ ባንድ ታጅባ ተወዳጁን «ጃጃ» የተሰኘ ሙዚቃዋን ተጫውታለች።
በደቡባዊ የዩናይትድ ስቴትስ ክፍል በሚገኙ ግዛቶች በተነሳ አውሎንፋስ የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ባለሥልጣናት አስታወቁ። የደረሰው የጉዳት መጠን ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል። በቴክሳስ፣ ሉዊዚያና፣ ሚሲሲፒ፣ አላባማ እና ጆርጂያ ውስጥ በአውሎንፋስ ምክንያት የደረሱ ቢያንስ 45 ጉዳቶች ሪፖርት መደረጋቸውን፣ በብሔራዊ አየር ሁኔታ አገልግሎት የአየር ትንበያ ማዕከል ውስጥ የሚሰሩ ባለሞያዎች አስታውቀዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለበዓል በሚጓጓዙበት ወቅት የተነሳው አውሎነፋስ በአየር ማርፊያዎች መዘግየት እና የመንገድ መዘጋጋት የፈጠረ ሲሆን፣ በደቡባዊ ጆርጂያ ግዛት በሚገኘው የአትላንታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ብቻ ከ600 በላይ በረራዎች ላይ መዘግየት እንደፈጠረ አንድ የበረራ መከታተያ ተቋም አመልክቷል። የኤሌክትሪክ አገልግሎት መከታተያ ድህረ ገጽ በበኩሉ በሚሲሲፒ፣ ቴክሳስ፣ አላባማ፣ ሰሜን ካሮላይና እና ጆርጂያ የሚኖሩ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደተቋረጠባቸው አመልክቷል።
በኬንያ መንግሥት ላይ ትችት የሚሰነዝሩ ወጣቶች ላይ ያነጣጠረው አፈና እንዲቆም በሚጠይቁ የጎዳና ላይ ሰልፎች ላይ የተሳተፉ ተቃዋሚዎች እና አንድ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ሰኞ ዕለት መታሰራቸው ተገለጸ። የኬንያ ምክር ቤት አባል የሆኑት ሴናተር ኦኪያ ኦምታታህ፣ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ ተቃውሞ ያካሄዱ እና ፖሊስ በዚህ ወር ያገታቸውን ሰባት ሰዎች እንዲለቅ የሚጠይቁ መፈክሮችን ያሰሙ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ተቀላቅለዋል። ፖሊስ ተቃዋሚዎቹን ለመበተን አስለቃሽ ጋዝ የተጠቀመ ቢሆን፣ ሴናተሩን ጨምሮ በርካታ ሰዎች እጅ ለእጅ ተቆላልፈው ከቦታው ለመነሳት ፈቃደኛ ባለመኾናቸው ለእስር መዳረጋቸው ተዘግቧል። የኬንያ ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባለፈው ሐሙስ በአወጣው መግለጫ በመንግሥት ተቺዎች ላይ እየተፈፀመ ነው የተባለው አፈና እየጨመረ መሄድ እንዳሳሰበው ገልጾ ነበር። በሰኔ ወር ከተካሄደው የመንግሥት ተቃውሞ ሰልፍ ወዲህ 82 ተመሳሳይ ውንጀላዎች እንደደረሱትም አመልክቷል። ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በበኩላቸው ወጣቶች በሰላም እንዲኖሩ መንግሥት አፈናውን እንደሚያስቆም ቅዳሜ ዕለት ገልጸው ነበር። የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ከአፈናዎቹ ጀርባ ያለው የሀገሪቱ ፖሊስ መሆኑን በመግለፅ ክስ ቢያቀርቡም፣ ፖሊስ እጁ እንደሌለበት እና ደብዛቸው የጠፉ ሰዎች ጉዳይ ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጿል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ጂሚ ካርተር በ100 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ካርተር ከፕሬዚደንትነታቸው በፊት በለውዝ ግብርና ስራ እንዲሁም በጆርጂያ ግዛት አስተዳዳሪነት ሀገራቸውን አገልግለዋል። ካርተር በአውሮፓዊያኑ አቆጣጣር ፣ ጥር 20 ቀን 1977 የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ሆነው ቃለ መሃላ ሲፈጽሙ «እንደ ሀገሪቱ ህዝብ ሁሉ መልካም መንግስት» እንደሚመሰርቱ ቃል ገብተው ነበር። አራት ዓመት የስልጣን ዘመናቸው ግን ርጋታ የራቀው ነበር።ያሻቀበ የዋጋ ንረት እና የስራ አጥነት ቁጥር መጨመር አስተዳደራቸው ቅድሚያ ሊሰጣቸው ያቀዳቸውን ጉዳዮች አስተጓጉሏል። በግብፅ እና በእስራኤል መካከል የሰላም ስምምነት እንዲደረስ በማድረግ እና የፓናማ ካናል ስምምነትን እውን በማድረግ በውጭ ፖሊሲ መስክ ድሎችን አስመዝግበዋል። ኢራን ውስጥ የነበረው የአጋች ታጋች ቀውስ መዘዝ በኋይት ሀውስ የነበራቸውን ቆይታ የመጨረሻዎቹን ዓመታት ተቆጣጥሮ በ1980ው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ እንዲሸነፉ አድርጓቸዋል። ጂሚ ካርተር ዋይት ኃውስን መናገሻ ካደረጉ የአሜሪካ ፕሬዚደንቶች ሁሉ ዕድሜ ጠገቡ የነበሩ ሲሆን ፣ ከባለቤታቸው ሮሳሊን ጋር ያሳለፉት 76 ዓመት የትዳር ዘመንም ከትኛውም አሜሪካ ፕሬዚደንት ትዳር ዘመን ጋር ሲነጻጸር ረጅሙ ሆኖ ተመዝግቧል ።
በሲዳማ ብሔራዊ ክልል ፣ ምስራቃዊ ሲዳማ ዞን በተከሰተ የመኪና አደጋ 71 ሰዎች መሞታቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ። የዞኑ አስተዳዳሪ ማቴ መንገሻ (ዶ/ር) አደጋው የተከሰተው ከሀዋሳ 125 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቦና ወረዳ- ገላና ወንዝ ተብሎ በሚጠራዉ አከባቢ መሆኑን ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል ። 68 ወንዶች እና 3 ሴቶች በአጠቃላይ 71 ሰዎች ወድያወኑ መሞታቸው መረጋገጡን አስታውቀዋል። የቦና ሆስፒታል ስራ አስኪያጂ አቶ አሸናፊ ብልሶ ከሟቾች በተጨማሪ ፣ 4 ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታሉ መጥተው ህክምና እያገኙ መኾናቸውን ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል። አንድ ተጎጂ ደግሞ ከፍ ላለ ህክምና ወደ ሀዋሳ ሪፌራል ሆስፒታል መላካቸውም ተገልጿል። የዞኑ አስተዳዳሪ ማቴ መንገሻ (ዶ/ር) ተሳፋሪዎችን ጭኖ ሲጓዝ የነበረ ኤፍ ኤስ አር አይሱዙ የተባለ የጭነት መኪና መንገዱንን ስቶ ፣ በገላና ወንዝ ላይ ከሚገኘው መሻገሪያ ድልድይ ወደ ወንዙ በመውርወሩ ምክንያት አደጋው እንደተከሰተ አብራርተዋል። የአደጋው ሰለባ የኾኑት ከአንድ የሰርግ ስነስርዓት እና በቡና ሳይት ስራ ላይ ቆይተዉ ሲመለሱ የነበሩ የአንድ አከባቢ ወጣቶች መሆናቸውን አስተዳዳሪው አክለው ተናግረዋል ።
በትግራይ ክልል ፣የመንግስታዊው ትግራይ ቴሌቭዥን ጋዜጠኞች ቡድን አባላት ከሰዓታት «እስር » በኃላ በዛሬው ዕለት መለቀቃቸው ተሰምቷል። የክልሉ መንግስት ንብረት የሆነው ቴሌቭዥን ጣቢያ ጋዜጠኞች ቡድን አባላት ፣ ለእስር በተዳረጉበት ወቅት በሰሜን ምዕራብ ትግራይ በሚገኝ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ላይ የምርመራ ዘገባ እየሰሩ እንደነበር ታውቋል። ቴሌቭዥን ጣቢያው ጋዜጠኞቹ በአስገደ ወረዳ ፣ በሚይሊ ቀበሌ ተገኝተው ለወርቅ ማዕድን ማውጣት አገልግሎት ላይ የሚውሉ ኬሚካሎች የፈጠሩትን ጉዳት በተመለከተ ምርመራ እያደረጉ እንደነበረ አረጋግጧል። ለደህንነት ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የጣቢያው የቅርብ ምንጮች ለቪኦኤ እንደገለፁት አንድ ጋዜጠኛ፣ አንድ የካሜራ ባለሙያ እና ሾፌራቸው ለእስር ተዳርገዋል። ቆየት ብሎ ከቴሌቭዥን ጣቢያው የወጣው መግለጫ የጋዜጠኛ ቡድኑ አባላት መፈታታቸውን አረጋግጧል። ከታሰሩት ጋዜጠኞች መካከል አንዱ የሆነው እና «ከ 7 ሰዓታት» እስር በኃላ እንደተለቀቀ የተናገረው ተስፋዝጊ ዓስበይ ፣ የደንብ ልብስ ያልለበሱ ሰዎች በቁጥጥር ስር እንዳዋሏቸው እና ሚይሊ ውስጥ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ያሰሯቸው አካላት የአካባቢው የጸጥታ ኃይሎች መሆናቸውን ቆይቶ መረዳቱን ለአሜሪካ ድምጽ ተናግሯል። ተስፋዝጊ የአካባቢው ባለስልጣናት እሱ እና ባልደረቦቹን እንዳስፈቷቸውንም አክሎ ገልጿል። የሰሜን ምዕራብ ትግራይ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተስፋይ አባዲ በአካባቢው የነበሩ የጸጥታ አካላት ጋዜጠኞችን በቁጥጥር ስር ያዋሏቸው « በአካባቢው ቀረፃ ለማካሔድ የሚያስችል የፍቃድ ደብዳቤ ስላልያዙ ነው » ፣ ሲሉ ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል።
ደቡብ ኮሪያ ውስጥ ፣ አንድ የመንገደኞች አውሮፕላን የማኮብኮቢያ ረድፉን ጥሶ ከኮንክሪት አጥር ጋር በመጋጨቱ በትንሹ 179 ሰዎች በእሳት ጋይተው መሞታቸውን ባለስልጣናት ተናገሩ። የጄጁ ኤር ንብረት የሆነው መንገደኛ ጫኝ አውሮፕላን ሙዐን በተባለችው ፣ ከመናገሻዋ ከተማ ሲዮል በስተደቡብ በምትገኝ ከተማ ለማረፍ በሚሞክርበት ቅጽበት ነው አደጋው የተከሰተው። 181 ሰዎችን አሳፍሮ የነበረው አውሮፕላን ከታይላንድ ባንኮክ እየተመለሰ ነበር።አደጋው በሀገሪቱ የበረራ ታሪክ እጅግ አስከፊ ከሆኑት አንዱ እንደሆነ ተነግሯል ። የድንገተኛ አደጋ መከላከል ሰራተኞች ሁለት የአውሮፕላኑን ሰራተኞች ማዳናቸውም ተሰምቷል ። ሁለቱም ሰዎች ለህይወት አስጊ አደጋ እንዳልገጠማቸው ባለስልጣናት ተናግረዋል። ተሳፋሪዎቹ በብዛት ደቡብ ኮሪያውያን ሲሆኑ ፣ ሁለቱ የታይላንድ ዜጎች ነበሩ። የትራንስፖርት ሚኒስቴር ባለስልጣናት ቀደም ብለው ባደረጉት የግንኙነት መሳሪያዎች ግምገማ ፣ የአውሮፕላን ማረፊያው መቆጣጠሪያ ማማ ሰራተኞች ፣ አውሮፕላኑ ለማረፍ ከማቀዱ ጥቂት ቀደም ብሎ አዕዋፍት ከአውሮፕላኑ ጋር ሊጋጩ ይችላሉ የሚል የስጋት ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን እና አብራሪው ሌላ ቦታ እንዲያርፍ መፍቀዳቸውን ያሳያል። የታይላንድ አየር ማረፊያዎች ኃላፊ ኬራቲ ኪጅማናዋት በሰጡት መግለጫ የጄጁ ፣ በረራ 7C 2216 አውሮፕላን ፣ ከሱቫርናብሁሚ አየር ማረፊያ ሲነሳ ፣ ምንም የተለየ ሁኔታ እንዳልተመዘገበበት አረጋግጠዋል። ጄጁ ኤር በሰጠው መግለጫ ለአደጋው ጥልቅ ይቅርታ ከጠየቀ በኃላ ፣ የድህረ አደጋ ሁኔታዎችን ለመቆጣጠር የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ አስታውቋል። በቴሌቭዥን በተላለፈው የጋዜጠኞች ማስገንዘቢያ ላይ የጄጁ ኤር ፕሬዝዳንት ኪም ኢ-ባ ከሌሎች የኩባንያው ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በመሆን በይቅርታ ደንብ እጅ በመንሳት የሟቾችን ቤተሰቦች ይቅርታ ጠይቀው ፣ ለክስተቱ “ሙሉ ሀላፊነት” እንደሚሰማቸው ተናግረዋል። ኪም አየር መንገዱ በወቅቱ ባደረገው ምርመራ በአውሮፕላኑ ላይ ምንም ዓይነት የሜካኒካል ችግር አለመኖሩን እና የአደጋውን መንስኤ በተመለከተ የመንግስት የምርመራ ውጤቶችን እንደሚጠባበቅ ተናግረዋል። (ዘገባው የአሶሼትድ ፕረስ ነው)
በሶማሊያ የሚሰማሩ የብሩንዲ ወታደሮች ቁጥርን በተመለከተ በሶማሊያ እና ብሩንዲ ሀገራት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ወደ አፍሪካ ህብረት የሰላም ተልዕኮ ማምራቱን ተከትሎ በሰላም ተልዕኮው ሽግግር ላይ ስጋት ደቅኗል ። ሶማሊያ በተልዕኮው ውስጥ 1041 የብሩንዲ ወታደሮች እንዲሳተፉ የደለደለች ቢሆንም ብሩንዲ ግን ቁጥር በቂ ያልሆነ እና የወታደሮቿን ድጋፍ እና ስምሪት ደህንነት ለአደጋ የሚያጋልጥ መሆኑን ተናግራለች። ብሩንዲ በትንሹ 2000 ወታደሮችን ለማሰማራት እንደምትሻ ዲፕሎማቶች ተናግረዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ፣ አዲስ ለተቋቋመውን የአፍሪካ ህብረት ፣ የሶማሊያ ድጋፍ እና መረጋጋት ተልዕኮ (ኤዩሶም) ድጋፍ ሰጥቷል ።ተልዕኮው በስራ ላይ የቆየውን የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ (አትሚስ) ከአውሮፓዊያኑ ጥር 1.2025 ጀምሮ ይተካል ።አዲሱ ተልዕኮ በሀገሪቱ ውስጥ ለ12 ወራት ይሰማራ ዘንድ ጸድቆለታል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፣ የአፍሪካ ህብረት 1,040 ፖሊሶችን ጨምሮ እስከ 12,626 መለዮ ለባሾችን እስከ ሰኔ 30 ፥ 2025 በሚዘልቀው የተልዕኮው የመጀመሪያ ምዕራፍ የስራ ዘመን እንዲያሰማራ ስልጣን ሰጥቶቷል።የሶማሊያ ባለስልጣናት እስካሁን ድረስ ከሶስት ሀገራት -ማለትም ከዮጋንዳ ፣ ጅቡቲ እና ኬንያ 11000 ወታደሮችን ማካተታቸውን አስታውቀዋል። በአውሮፓዊያን ታህሳስ 26 በሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አብዱልቃድር ሞሐመድ ኑር የተጻፈው ደብዳቤ ፣የሚሰማሩ ብሩንዲ ወታደሮችን ቁጥር በተመለከተ ስምምነት ላይ አለመደረሱን ጠቁሟል ። አንድ የብሩንዲ ዲፕሎማት ፣ የወታደሮችን ቁጥር በተመለከተ ልዩነት መኖሩን አረጋግጠዋል። “የሶማሊያ ባለስልጣናት ወታደሮቻችንን ለአደጋ የሚያጋልጥ ቁጥር በመመደብ ክብራችንን ዝቅ አድርገዋል።ውለታን በመዘንጋት ፣ብሩንዲያውያን ለሶማሊያውያን ያላቸውን ጥልቅ ስሜት በቅጡ መገንዘብ አልቻሉም «፣ ሲሉ አንድ የብሩንዲ ባለስልጣን ለቪኦኤ አፍሪቃ ቀንድ አገልግሎት በዋትሳፕ መገናኛ በኩል መልዕክት ሰደዋል። “በዛሬ እና በታህሳስ 31(እ ኤ አ) መካከል አንዳች ለውጥ ካልተፈጠረ ወደ ሀገራችን እንመለሳለን ።ለመቆየት አንጓጓም ። ክብራችን ተነክቷል ፣ ስለሆነም ይቅርታን እንሻለን » ሲሉም ዲፕሎማቱ አክለዋል ። ለወታደሮች ቅነሳ ብሎም በታህሳስ 2024 ሶማሊያን ለቆ ለመውጣት የሚያስችል የጊዜ ተመን ለመበየን የሚያስችል የስራ መዋቅር ተፈጻሚ ከሆነ በኃላ የቀድሞው የሶማሊያ የሰላም ተልዕኮ በምሕጻሩ «አሚሶም» ከአውሮፓዊያኑ 2022 በኃላ በ አትሚስ ተተክቷል። የወታደሮቹ የመልቀቂያ ጊዜ እየተቀራበ በመጣበት በአሁኑ ጊዜ ፣ የአፍሪካ ህብረት ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፣ እና የሶማሊያ መንግስት -አልሸባብ አሁንም አደጋ በመጣል ፣ የተገኙ ድሎችን እንዳይቀለብስ ስጋት አድሮባቸዋል። በዚህም ምክንያት የሶማሊያ መንግስት ወታደሮቹን ለማዘጋጀት ተጨማሪ ጊዜ የሚሰጠውን አዲሱን የአፍሪካ ህብረት ፣ የሶማሊያ ድጋፍ እና መረጋጋት ተልዕኮ (ኤዩሶም) ማቋቋም አስፈልጓል። ከዚህ በተጨማሪ በአዲሱ የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ውስጥ ኢትዮጵያ የሚኖራት ሚናም አለየም ። የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በተልዕኮው ውስጥ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ቢናገሩም ፣ አንዳንድ ባለስልጣናት ግን የኢትዮጵያን ሚና ይጠራጠሩታል።
የናይጄሪያ ባለሥልጣናት በሰሜን ምዕራቧ ክፍለ ግዛት ሶኮታ ውስጥ በፈረንጆች ገና ዕለት ቢያንስ አስር ሰዎች በተገደሉበት የአየር ጥቃት ጉዳይ ምርመራ ጀምረናል ብለዋል፡፡ የጦር ኅይሉ በበኩሉ የአየር ጥቃቱ በአካባቢው የሚንቀሳቀስ አዲስ ታጣቂ ቡድንን እንጂ ሲቪሎችን ዒላማ ያደረገ አልነበረም ብሏል፡፡ ቲመቲ ኦቢዬዙ ከአቡጃ ያስተላለፈውን ዘገባ ቆንጅት ታየ ወደ አማርኛ መልሳዋለች፡፡
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የድሬዳዋ ምድብ ችሎት የጂጂጋ ተዘዋዋሪ ችሎት በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በ4 መዝገቦች የተከሰሱ 88 የአልሸባብ አባላት ናቸው የተባሉ ተከሳሾች ላይ እስከ 20 ዓመት የሚደርስ እሥራት ፍርድ አስተላልፏል። ተከሳሾቹ በ2014 ዓም እና በ2015 ዓ/ም የጸጥታ አካላትና ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት በማድረስ፣ ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ንብረት በመዝረፍና በማውደም እንዲሁም መንግሥታዊ መረጃዎችን ለአልሸባብ የሽብር ቡድን አሳልፈው በመስጠት የተከሰሱ መሆናቸው ታውቋል፡፡
በዛምቢያ የሚዲያ ነጻነት ጥቃት እየደረሰበት እንደሆነ አዲስ የወጣ ጥናት አመለከተ፡፡ በጥናቱ ላይ አስተያየታቸውን በመስጠት ከተሳተፉት መካከል ስድሳ በመቶ የሚሆኑት በጋዜጠኞች እና ፀሃፊዎች ላይ በሚደርሱ ተዳጋጋሚ ትንኮሳና ማስፈራራት ምክንያት ሚድያዎች በነጻነት ስራቸውን እየሰሩ ነው ብለው እንደማያስቡ ተናግረዋል፡፡ በካቲ ሾርት የተዘጋጀውን ዘገባ አስማማው አየነው ወደ አማርኛ መልሶታል፡፡
ኮሚሽኑ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ቀድሞ የታገዱ ድርጅቶቹ አቤቱታ እንደደረሰው ገልጾ ጉዳዩን እየተከታተለ ባለበት ወቅት “ተመሳሳይ ይዘት ባለው እና ተቋማቱ የፈጸሟቸውን ከባድ የሕግ ጥሰቶች በዝርዝር ባላስቀመጠ ደብዳቤ“ ተጨማሪ ሁለት ድርጅቶች መታገዳቸውን አሳሳቢ ሆኖ እንዳገኘው ገልጿል፡፡ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ በተደጋጋሚ የሚተላለፉ እገዳዎች የሲቪክ ምኅዳሩን በማጥበብ እና በማኅበር የመደራጀት መብት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳይፈጥሩ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ሲልም አሳስቧል፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በአሁኑ ወቅት በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የሚሠሩትን የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማእከል፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ እና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከልን ከማንኛውም እንቅስቃሴ አግዷል፡፡ ባለሥልጣኑ፣ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶችን ያገደው “ገለልተኛ አይደላችሁም፣ ከዓላማ ውጭም ተንቀሳቅሳችኋል” በሚል እና ተያያዥ ምክንያቶች መኾኑን በጻፈላቸው ደብዳቤ አመልክቷል፡፡ የታገዱ ድርጅቶች ኅላፊዎችም የቀረበበባቸውን ውንጀላ ለአሜሪካ ድምጽ በሰጧቸው አስተያየቶች ማስተባበላቸው ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም “ባለሥልጣኑ የድርጅቶቹን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ የምርመራ ሥራዎቹን በተቻለ ፍጥነት አጠናቆ ወደ ሥራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ እንዲያመቻች” በመግለጫው ጠይቋል፡፡
የጀርመኑ ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ዛሬ ዓርብ የሃገሪቱን ፓርላማ በትነው በሚቀጥለው ወር ምርጫ እንዲደረግ አዘዋል። ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ ከሳምንት በፊት መተማመኛ ድምጽ በማጣታቸውና ባለፈው ወር የገንዘብ ምኒስትራቸውን ማባረራቸውን ተከትሉ፣ በሶስት ፓርቲዎች ጥምር ያቋቋሙት መንግስት ፈርሷል። የዋና ዋና ፓርቲ መሪዎች እአአ በመጪው የካቲት 23 የፓርላማ ምርጫ እንዲደረግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ምርጫው የሚካሄደው ቀድሞ ከታቀደው ሰባት ወራት ቀደም ብሉ ነው። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የወጣው የጀርመን ሕገ መንግሥት፣ ‘ቡንደስታግ’ ወይም የሃገሪቱ ሸንጎ ራሱን መበተን ስለማይችል፣ ውሳኔውን የመስጠት ሃላፊነቱ ፕሬዝደንቱ ላይ ወድቋል። በዚህም መሠረት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ፓርላማውን በትነው ምርጫ እንዲደረግ አዘዋል። የምርጫ ዘመቻው ግን ፓርላማው ከመበተኑ በፊትም በመካሄድ ላይ ነበር። በሕዝብ አስተያየት መለኪያ መሠረት ወግ አጥባቂው የተቃዋሚዎች ስብስብ በመምራት ላይ ሲሆን፣ የኦላፍ ሾልዝ ፓርቲ ደግሞ ይከተላል። በምርጫው ቁልፍ ጉዳዮች የሆኑት ፍልሰት፣ የተዳከመው ኢኮኖሚ እና ለዩክሬን የሚሰጥ ድጋፍ ናቸው።
ካዛክስታን ውስጥ የተከሰከሰውና 38 ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡበትን የአውሮፕላን አደጋ መንስኤ በተመለከተ ሩሲያ እና ሌሎች ወገኖች ጣት በመጠቋቆም ላይ ናቸው። በአደጋው 29 ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል። ስድሳ ሰባት መንገደኞችን ይዞ ሲጓዝ የነበረው የአዘርባጃን አየር መንገድ አውሮፕላን ካዛክስታን ውስጥ በተከሰከሰበት ወቅት በቼችንያ ክልል ውስጥ በዩክሬን የድሮን ጥቃት በመፈጸም ላይ እንደነበር የሩሲያ ሲቪል አቪዬሽን ኅላፊ ዲሚትሪ ያድሮቭ ሲናገሩ፣ አንድ የአዘርባይጃን ምክር ቤት አባል እና በርካታ የአቪዬሽን ባለሙያዎች ደግሞ አውሮፕላኑ የተከሰከሰው በሩሲያ በተተኮሰ የአየር መቃወሚያ መሆኑን ይገልጻሉ። አውሮፕላኑ ከአዘርባጃን መዲና ባኩ ወደ ሩሲያዋ የቼችንያ መዲና ግሮዝኒ በማምራት ላይ እንደነበር ታውቋል። አውሮፕላኑ አቅጣጫውን በመቀየር በካዛክስታኗ አክታ ከተማ በድንገት ለማረፍ በመሞከር ላይ ሳለ ተከስክሷል። የአዘርባጃን፣ ካዛክስታን እና የሩሲያ ባለሥልጣናት የአደጋውን መንስኤ በተመለከተ ከመናገር ተቆጥበው የነበረ ቢሆንም፣ ራሲም ሙሳቤኮቭ የተባሉ የአዘርባጃን ምክር ቤት አባል፣ አውሮፕላኑ በግሮዝኒ ሰማይ ላይ ሳለ ተመትቶ እንደወደቀ ለሃገሪቱ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል። “ሩሲያ ይቅርታ ትጠይቅ” ሲሉም አክለዋል። የፓርላማ አባሉን መግለጫ በተመለከተ የተጠየቁት የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ፣ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበው፣ «የአደጋውን መንስኤ የሚወስኑት መርማሪዎች ናቸው» ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል የጸጥታ ኃይሎች እና በክልሉ ዳአዋሌ መንደር የሚንቀሳቀሱ የጎሣ ታጣቂዎች መካከል ለሦስተኛ ጊዜ በተቀሰቀሰ ግጭት በርካታ ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ። የመጀመሪያዎቹ ሁለት ውጊያዎች የተካሄዱት ባለፈው ሳምንት ረቡዕ እና አርብ ሲሆን፣ ከሁለቱም ወገኖች ሰዎች መሞታቸው እና ትላንት ረቡዕ በተካሄደው ውጊያ ቁጥራቸው የበዛ ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ዘጋቢ ሃሩን ማሩፍ ያደረሰን ያደረሰን ዘገባ ነው፡፡
ዓለም በሚቀጥለው ወር የተመራጩን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ወደ ዋይት ሀውስ መመለስ በሚጠባበቅበት በዚህ ወቅት፣ ታይዋን እየተባባሰ ካለው የቻይና ጠብ አጫሪነትና ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በሚኖራት በውል ባልታወቀው ግንኙነት መካከል ተይዛለች፡፡ የቪኦኤ ዘጋቢ ዊሊያም ያንግ ከታይፔ ተከታዩን ዘግቧል፡፡ ደረጀ ደስታ ያቀርበዋል ወደ አማርኛ መልሶታል፡፡
በየመን ሰነአ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የደረሰውን የአየር ጥቃት ተከትሎ፣ በወቅቱ በሥፍራው የነበሩት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዲሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ከጥቃቱ መትረፋቸውን አስታውቀዋል። ዶ/ር ቴድሮስ በX ማኅበራዊ መድረክ ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፣ በየመን የተገኙት በሃገሪቱ ታግተው የሚገኙ የተመድ ሠራተኞችን ለማስለቀቅ ድርድር ለማድረግ እንደነበር አመልክተዋል። “ሰነአ ላይ ወደ አውሮፕላን ልንገባ ስንል አየር ማረፊያው ላይ ድብደባ ደርሷል። አንድ የበረራ ባልደረባችን በጥቃቱ ተጎድቷል፣ እንዲሁም ሁለት ሰዎች እንደሞቱ ሪፖርት ተደርጓል” ሲሉ ዶ/ር ቴድሮስ በመልዕክታቸው አስታውቀዋል። “እኔም ሆንኩ የተመድ እና የዓለም ጤና ድርጅት ባልደረቦቼ ተርፈናል” ሲሉም አክለዋል። በእስራኤልና በሁቲ አማጺያን መካለከል ውጥረት ማየሉን ተከትሉ በአየር ማረፊያውና አማጺያኑ በሚገኙባቸው አካባቢዎች ባሉ ወታደራዊ መሠረቶች እና የኃይል ማመንጫዎች ላይ የአየር ጥቃቶች በመደረግ ላይ ናቸው። የእስራኤሉ ጠቅላይ ምኒስትር ቤንጃሚን ኔታያሁ “ሥራው እሰከሚጠናቀቅ ድረስ ድብደባው ይቀጥላል” ብለዋል። የሁቲ አማጺያን ባለፉት ሁለት ቀናት ሁለት ጊዜ ወደ እስራኤል ሚሳኤል ተኩሰው እንደነበር ሲታወስ፣ ዛሬ በሰነአ የደረስውን የአየር ጥቃት “ጽዮናውያን በየመን ሕዝብ ላይ የፈጸሙት ወንጀል ነው” ሲሉ የሁቲ ቃል አቀባይ ሞሃመድ አብዱልሰላም ተናግረዋል። የእስራኤል ሠራዊት በበኩሉ“ ተዋጊ አውሮፕላኖቹ በሁቲ አማጺያን ሥር ባሉ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ድብደባ መፈጸማቸውን አስታውቋል። በጋዛ ጦርነቱ ከፈነዳ ወዲህ የሁቲ አማጺያን ከፍልስጤማውያን ጋራ አጋራነታቸውን ለማሳየት በሚል በርካታ ሚሳዬሎችንና እና ድሮኖችን ወደ እስራኤል ሲያስወነጭፉ ቆይተዋል።
ፕሮፌሰር ገብሬ ይንቲሶ የቀድሞ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና በአሁኑ ወቅት የአካታች ሰላምና ልማት በአፍሪካ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅትን በስራአሲያጅነት ይመራሉ፡፡ ሚያዝያ14 ቀን 2016 ዓ.ም የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች ተባባሪ አካላት ጋር ባዘጋጁት መድረክ "በሰላም ግንባታ የወጣቶች ሚና'' በተመለከተ የመወያያ ጽሁፍ አቅርበው ነበር፡፡ የአሜሪካ ድምጽ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስም በኢትዮጵያ ወጣቶች ከግጭትና ጦርነት ወጥተው ወደ ሰላም እንዲመጡ የሚያስችሉ የሰላም ግንባታ ስራዎች በበቂ ሁኔታ እየተሰራ አይደለም ብለዋል፡፡ ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ
ፕሮፌሰር ገብሬ ይንቲሶ የቀድሞ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና በአሁኑ ወቅት የአካታች ሰላምና ልማት በአፍሪካ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅትን በስራአሲያጅነት ይመራሉ፡፡ ሚያዝያ14 ቀን 2016 ዓ.ም የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች ተባባሪ አካላት ጋር ባዘጋጁት መድረክ "በሰላም ግንባታ የወጣቶች ሚና'' በተመለከተ የመወያያ ጽሁፍ አቅርበው ነበር፡፡ የአሜሪካ ድምጽ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስም በኢትዮጵያ ወጣቶች ከግጭትና ጦርነት ወጥተው ወደ ሰላም እንዲመጡ የሚያስችሉ የሰላም ግንባታ ስራዎች በበቂ ሁኔታ እየተሰራ አይደለም ብለዋል፡፡ ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ
ዩኒቨርሰሲቲዎች ውጤታማ ሥራ ካላከናወኑ፣ ህልውናቸው ላይቀጥል እንደሚችል የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ አስጠነቀቁ፡፡ በሀገሪቱ ያሉት ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋራ ዛሬ የአፈፃፀም ኮትራት የፈረሙ ሲሆን፣ ሥራዎቻቸውም፣ በዚሁ ኮንትራት መሰረት እንደሚለካ ተገልፆዋል፡፡ ወደፊት ለዩኒቨርሲቲዎች የሚመደበው በጀት፣ የሥራ አፈፃፀማቸውን መሰረት ያደረገ እንደሚሆን የገለፁት ሚኒስትሩ፣ ከዛም አልፎ ዩኒቨርሲቲዎቹ፣ ውጤታማ ካልሆኑ ወደ ቴክኒክ ማሰልጠኛነት የሚቀየሩበት ኹኔታ ይኖራል ብለዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች በበኩላቸው፣ እርምጃው ውጤትን ለመመዘን ስለሚያስችል ተቋማቱን ያነቃቃቸዋል በማለት ገልፀዋል፡፡
በቅርቡ የቀዶ ሕክምና የተደረገላቸው የምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና አቶ ክርስቲያን ታደለ ወደ ሌላ እስር ቤት መዛወራቸውን ቤተሰቦቻቸው እና ጠበቃቸው ገልፀዋል፡፡ ሁለቱ ታሳሪዎች “ከፍተኛ ሕመም እየተሰማቸው ነው ወደ ቂሊንጦ የተዛወሩት” ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ በተለይ አቶ ዮሐንስ የሚገኙበት ማቆያ ሥፍራ ለጤንነታቸው የሚያሰጋቸው እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ ይህ ሁኔታ እንዲቀየር ለፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረባቸውን ጠበቃቸው አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ገልፀዋል፡፡ የቂሊንጦ ቀጠሮ ማረፊያ ማዕከል ዳይሬክተር ኮማንደር ዓለምሰገድ፣ ውንጀላውን አስተባብለዋል፡፡
በሞዛምቢክ የሕገ መንግሥቱ ም/ቤት ገዢው ፓርቲ ባለፈው መስከረም መጨረሻ ላይ የተደረገውን ምርጫ እንዳነሸነፈ ማወጁን ተከትሎ ባለፉት 24 ሠዓታት ውስጥ በተደረገ ተቃውሞ ሁለት ፖሊሶችን ጨምሮ ቢያንስ 21 ሰዎች መገደላቸው ታውቋል። አጨቃጫቂውን የምርጫ ውጤት ተከትሎ የሃገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ም/ቤት ገዢው ፍሬሊሞ ፓርቲ ማሸነፉን እንዳስታወቀ የተቃዋሚው መሪ ቬናሲዮ ሞንድላኔ ተቃውሞ እንዲደረግ ትላንት ጥሪ አድርገው ነበር። ከእአአ 1975 ጀምሮ ላለፉት አምሳ ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆየው የፍሬሊሞ ፓርቲ ባለፈው መስከረም መጀመሪያ ላይ በተደረገው ምርጫ አሸናፊ መሆኑ ከታወጀ ወዲህ በሃገሪቱ ለሳምንታት በርካታ ሕይወት የቀጠፈ ተቃውሞ ተደርጓል። እስከ አሁን 150 ሰዎች ከምርጫው ጋራ በተያያዘ ሁከት ህይወታቸው አልፏል። የገዢው ፓርቲ እጩ ዳንኤል ቻፖ አሸናፊ እንደሆኑ ቢነገርም፣ በአብዛኛው ወጣቶች የሆኑ የተቃዋሚው ቬናሲዮ ሞንድላኔ ደጋፊዎች ወደ አደባባይ በመውጣት ተቃውሞ አድርገዋል። በውጤቱ ቻፖ 65 በመቶውን ድምጽ እንዳገኙ ሲነገር፣ ሞንድላኔ ደግሞ 24 በመቶ እንዳገኙ ታውቋል። ባለፉት 24 ሰዓታት 236 የሚሆኑ ጥቃቶች ተፈፅመው ሁለት ፖሊሶችን ጨምሮ የ21 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ 13 ሲቪሎችና 12 ፖሊሶች ደግሞ መጎዳታቸውን የሃገሪቱ ፖሊስ አስታውቋል። በመዲናዋ ማፑቶ ሱቆች ሲዘረፉና ሲቃጠሉ የሚያሳዩ ምስሎች በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ታይተዋል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን የነዳጅ እና ሌሎችም የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ተከታታይ የሚሳዬል ጥቃት መፈጸሟንና በርካቶች በዛሬው ገና ዕለት ካለ ኤሌክቲሪክ ኅይል መቅረታቸውን የዩክሬን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። በጥቃቱ 78 የአየር እና የምድር ተወንጫፊ ሚሳዬሎች እንዲሁም 106 ሻሂድ እና ሌሎች ዓይነት ድሮኖች ጥቅም ላይ መዋላቸው ታውቋል። በርካታ ዩክሬናውን በገና ዕለት በምድር ውስጥ የባቡር ጣቢያዎች ለመጠለል ተገደዋል። በጥቃቱ ቢያንስ አንድ ሰው ሳይሞት እንዳልቅረ ተነግሯል። በተለይም በካርኪቭ ክልል በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በቀዝቃዛው ወቅት ሙቀት ማግኘት እንዳልቻሉም ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። በሌላ በኩል ሩሲያ ውስጥ አንድ ድሮን በአየር ላይ ተመቶ ፍርስራሹ ሲወድቅ የአንዲት ሴትን ሕይወት ሲያጠፋ ሦስት ሰዎች ደግሞ ተጎድተዋል። “ፑቲን ሆን ብለው በገና ዕለት ጥቃቱን ፈጽመዋል። ከዚህ በላይ ኢሰብአዊነት አለን?” ሲሉ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ በ X ማኅበራዊ መድረክ ላይ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። “ሩሲያ በመላው ዩክሬን ኅይል እንዲቋረጥ በማጥቃት ላይ ነች” ሲሉም አክለዋል። አንድ ሚሳዬል የሞልዶቫንና የሮማንያን የአየር ክልል አልፎ እንደመጣ የዩክሬኑ የውጪ ጉዳይ ምኒስትር አንድሪል ሲቢሃ አስታውቀዋል። ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጥቃት የጀመረችው ከሁለት ዓመታት በፊት በገና ዋዜማ መሆኑ ይታወሳል።
የየመን አማፂያን ወደ ቴል አቪቭ፣ እስራኤል ዛሬ ረቡዕ ሚሳዬል ማስወንጨፋቸውን አስታውቀዋል። ጥቃቱ የአደጋ ማስጠንቀቂያ እንዲደወል ሲያደርግ፣ ጉዳት ግን አላደረሰም ተብሏል። የእስራኤል ሠራዊት በበኩሉ ሚሳዬሉ ድንበር ከማቋረጡ በፊት መመታቱን አስታውቋል። ሁቲዎች ሚሳዬል ሲያስወነጭፉ በሁለት ቀናት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። በጋዝ ሰርጥ እስራኤል በምታካሂደው ጦርነት ከፍልስጤማውያን ጋራ ያላቸውን አንድነት ለማሳየት እንደሆነ የሁቲ አማጺያን አስታውቀዋል። በእስራኤል ላይ ሚሳዬል ከማስወንጨፍ በተጨማሪ፣ ሁቲዎች በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ በሚተላለፉ መርከቦች ላይ ጥቃት በመፈጸማቸው ቁልፍ የሆነው የንግድ መርከቦች መተላለፊያ ተስተጓጉሏል። የእስራኤል ባለሥልጣናት በበኩላቸው በኢራን በሚደገፉት ሁቲዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ በመዛት ላይ ናቸው። በሌላ በኩል የእስራኤል ሠራዊት ባደረገው ምርመራ፣ ሠራዊቱ በጋዛ በመገኘቱ ምክንያት ባለፈው ነሐሴ ስድስት ታጋቾች መሞታቸውን ትላንት አስታውቋል። እንደ ምርመራው ውጤት ከሆነ፣ ሠራዊቱ መግባቱን ተከትሎ፣ ሐማስ አንድ ትውልደ እስራኤል የሆነ አሜሪካዊን ጨምሮ ስድስት ታጋቾችን ለ330 ቀናት ከያዙ በኋላ ገድለዋል። እስራኤል በጋዛ በምታካሂደው ጦርነት እስከ አሁን 45 ሺሕ ሰዎች እንደተገደሉ የፍልስጤማውያኑ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያስታውቃል።
በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል አንካራ ላይ ሥምምነት ከተፈፀመ ወዲህ የሶማሊያው ፕሬዝደንት በቀጠናው ጉብኝት ሲያደርጉ የመጀመሪያው ነው። ሃሳን ሼክ ሞሃሙድ አሥመራ ሲደርሱ በኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ሁለቱ መሪዎች በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን ግንኙነት በሚያሳድጉበትና በዓለም አቀፍና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ የኤርትራው የማስታወቂያ ምኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በX ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል። የፕሬዝደንት ሃሳን ጉብኝት የመጣው ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ በመካከላቸው ያለውን ውጥረት ለማርገብ ከሁለት ሳምንታት በፊት አንካራ ላይ ሥምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ነው። ሁለቱ ሀገራት አንዱ የሌላውን ሉአላዊነት፣ እንዲሁም የግዛት አንድነት እንደሚያከብር በፈጸሙት ሥምምነት አስታውቀዋል። ሁለቱ ወገኖች በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለንግድ ጠቀሜታ የባሕር አቅርቦት እንዲኖራት ውይይት እንደሚያደርጉ ተስማምተዋል። አሥመራ ባለፈው ጥቅምት የግብጽ እና የሶማሊያን መሪዎች ለሦስትዮሽ ውይይት ጋብዛ አስተናግዳለች። በውይይቱ የሦስቱ ሃገራት መሪዎች የሶማሊያን ተቋማት ለማጠናከርና ከውስጥና ከውጪ የገጠሟትን ተግዳሮቶች ለመጋፈጥ ተስማምተዋል። በተጨማሪም የሶማሊያ ፌዴራል ሠራዊት ሽብርን እንዲጋፈጥና የሃገሪቱን ሉአላዊ ግዛት እንዲከላከል ለማስቻል ተስማምተዋል። የሶማሊያው ፕሬዝደንት ከሁለት ዓመታት በፊት ከተመረጡ ወዲህ አሥመራን ሲጎበኙ ለስምንተኛ ጊዜ ነው። ኤርትራ በርካታ የሶማሊያ ጦር ዓባላትን በማሠልጠን ላይ ስትሆን፣ የተወሰኑት ሥልጠናቸውን አጠናቀው ተመልሰዋል። ሶማሊያ፣ ግብጽ በአፍሪካ ኅብረት ልዑክ ውስጥ ተሳትፎ ለማድረግ መወሰኗን በመልካም እንደምትቀበል አስታውቃለች፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የጆንስ ሆፕኪንስ ማዕከል የጤና ባለሞያዎች 'የወንዶች ስንፈተ ወሲብ' በአብዛኛው ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ እንደሚከሰት ጠቁመዋል። የስኳር በሽታ፣ የልብ ህመም እና ቅጥ ያጣ እና ከመጠን ያለፈ ውፍረት መንስኤ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስታውቀዋል። /የዚህ ሳምንት ኑሮ በጤንነት ችግሩን እና መፍትሄዎቹን ይቃኛል/
ቡናቸውን በቀጥታ ለዓለም አቀፍ ገበያ ያቀረቡ የሲዳማ አርሶ አደሮች የቡና ምርታቸውን በከፍተኛ ዋጋ መሸጣቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ተናገሩ። በዓለም አቀፍ ደረጃ የልዩ ጣዕም ቡና ባለቤቶችን በየዓመቱ እያወዳደረ የሚሸልመው ካፕ ኦፍ ኤክሰሌንሲ (COE) የተባለ ዓለም አቀፍ ድርጀት የኢትዮጵያ ፕሮጀከት ማናጀር አቶ እንዳለ አስፋው ከኢትዮጵያ የ600 አርሶ አደሮች ቡና ተወዳድሮ የ40ዎቹ ቡና አሸናፊ መኾኑን አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዲሬክተር ዶ.ር አዱኛ ደበላ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም በከፍተኛ ዋጋ መሸጡን ተናግረዋል። የCOE ዕውቅና መርኃ ግብር የአርሶ አደሮች በጥራት እንዲያመርቱ አነሳስቷቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የላቀ ብዛት ያላቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የሚኒስትር ቦታዎች እና የፍትህ አካላት ሃላፊነት ላይ ያሉ ሴት አባላት እንዳሏት አሃዞች ያሳያሉ። ነገር ግን በፖለቲካውም ሆነ በተለያዩ ማኅበራዊ ዘርፎች ላይ የሚሳተፉት ሴቶች በቂ እና አጥጋቢ የሆነ የውሳኔ አቅም እንዲኖራቸው የሚያደርግ ምህዳር እንደሌለ በሴቶች ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማት ይናገራሉ። ኤደን ገረመው በትምራን የሲቪክ ማኅበር የመርኃግብር አስተባባሪ የሆነችውን ወጣት ቤተልሔም አለምን እና የኤውብ የሴት አመራሮች ማኅበር አጋር አመስራች እና ዳይሬክተር ወ/ሮ ናሁሰናይ ግርማን አነጋግራ ያሰናዳችው ዘገባ በመቀጠል ይቀርባል።
ተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው በሰሜን ኮሪያ ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን በማጥበቅ የኒውክሊየር የጦር መሣሪያ መርሃ ግብሯን እንድትሰርዝ ሊያስገድዷት ሞክረው ነበር። በሁለተኛው የአስተዳደር ዘመናቸው ትረምፕ ከሰሜን ኮሪያ ምን መጠበቅ እንደሚኖርባቸው የሚቃኝ ዘገባ የአሜሪካ ድምጹ ያንግ ጋዮ ኪም አጠናቅሯል። ቆንጅት ታየ ወደ አማርኛ መልሳዋለች፡፡
የኬንያ መንግሥት ካለፈው ዓመት መስከረም ወር አንስቶ ባለው ጊዜ ከ7 ሺህ በላይ ወሲባዊ እና ጾታዊ ጥቃት መመዝገቡን አስታውቋል። ከነዚህ ውስጥ 100 የሚሆኑት ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እና ልጃገረዶች የተመዘገቡት ደግሞ በዚህ ዓመት፣ ከነሐሴ ወር ወዲህ ባለው ጊዜ ነው። ይህን ተከትሎ የኬንያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የሴቶችን እና ልጃገረዶችን ጥቃት የሚከላከል ልዩ የጸጥታ ቡድን ማቋቋሙን አስታውቋል። መሐመድ ዩሱፍ በዚህ ዙሪያ ያደረሰንን ዘገባ፣ ስመኝሽ የቆየ ወደ አማርኛ መልሳዋለች።
በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ ተደጋግሞ በሚደርሰው ርዕደ መሬት ምክንያት ሥጋት ውስጥ መውደቃቸውን የአካባቢው ኗሪዎች አስታወቁ፡፡ ትናንት እና ከትናንት በስቲያ ምሽት አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ ተፈጠረ በተባለው ርዕደ መሬት የፈንታሌ ተራራ አናት ላይ የጭስ ምልክት ታይቷል፣ የከባድ ፍንዳታ ድምጽ ተሰምቷል፣ የድንጋይ ናዳም ተስተውሏል ሲሉ ኗሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ ርዕደ መሬቱ የተፈጠረበት በአፋር ክልል ዞን ሦስት አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ወሃና ፍሳሽ አገልግሎት የመሬት መንቀጥቀጡንና ንዝረቱን ተከትሎ ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቁ የአርብቶ አደሮች ፍየሎችና ግመሎች በድንጋጤ በርግገው መጥፋታቸውን ጠቁሟል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊሲክስ ህዋ ሳይንስ እና አስትሮኖሚ ተቋም በበኩሉ ላለፉት ስድስት ቀናት የመሬት መንቀጥቀጡ መከሰቱን አረጋግጦ የትናንቱ በሬክተር ስኬል 4.9 እንደሚለካ አመልክቷል፡፡
በጦርነት ትርምስ ውስጥ ባለችው ሱዳን ረሃብ በአምስት አካባቢዎች መስፋፋቱና ወደ ሌሎች ተጨማሪ አምስት አካባቢዎችም ሊስፋፋ እንደሚችል አንድ በዓለም ደረጃ ረሃብን የሚከታተል ተቋም አስታውቋል። በጦርነቱ የሚሳተፉ ወገኖች፣ በዓለም ትልቁ የረሃብ ቀውስ እንደሆነ ለሚነገረው የሱዳን ቸነፈር ተጠቂዎች ሰብአዊ ርዳታን ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት ማስተጓጎል መቀጠላቸውን ተቋሙ ጨምሮ አስታውቋል። ‘የረሃብ ክትትል ኮሚቴ’ በሚል የሚታወቀው ተቋም ጨምሮ እንደገልጸው፣ ከበባ ውስጥ ባለችው የሰሜን ዳርፉር መዲና አል ፋሽር ውስጥ በሚገኙ ሁለት መጠለያዎች፣ እንዲሁም በደቡብ ኮርዶፋን ግዛት በሚገኙ ሌሎች ሁለት አካባቢዎች ረሃብ ተስፋፍቷል። ባለፈው ነሐሴ በሰሜን ዳርፉር ዛምዛም መጠለያ የተከሰተው ረሃብ መቀጠሉንም ኮሚቴው አስታውቋል። የረሃብን ሁኔታ የሚያረጋግጠውና ደረጃ የሚያወጣው ተቋም እንዳስታወቀው፣ በሰሜን ዳርፉር ባሉ ሌሎች አምስት አካባቢዎችም ረሃቡ እንደሚስፋፋ ግምቱን አስቀምጧል። በመላ ሱዳን የሚገኙ አስራ ሰባት አካባቢዎች ደግሞ ለረሃብ ተጋላጭ መሆናቸውም ታውቋል። በሱዳን 24፡6 ሚሊዮን የሚሆነው ወይም ከአጠቃላይ ሕዝቡ ግማሽ የሚሆነው እስከሚቀጥለው ወር ድረስ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚሻ ኮሚቴው አስታውቋል። ኮሚቴው በሱዳን የሚያደርገውን የምግብ ዋስትና ጥናት መንግስት እያስተጓጎለበት እንደሆነ ገልጿል። የሱዳን መንግሥትም የኮሚቲው ሪፖርት “ተአማኒ አይደለም” በሚል በጥናቱ መሳተፉን እንዳቆመ አስውቋል።