በኦሮሚያ ክልል በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 38 ሲቪሎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ገለጹ
newsare.net
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ወረዳ በሚገኙ፣ ቢርቢሳ ጋሌ እና ደረባ በተሰኙ ሁለት ቀበሌዎች ውስጥ ረቡዕ ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ምሽት ላይ በታጣቂዎችበኦሮሚያ ክልል በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 38 ሲቪሎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ገለጹ
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ወረዳ በሚገኙ፣ ቢርቢሳ ጋሌ እና ደረባ በተሰኙ ሁለት ቀበሌዎች ውስጥ ረቡዕ ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ምሽት ላይ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ሲቪሎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምጽ ገለጹ። ወላጆቻቸውን በጥቃቱ ያጡ ቤተሰቦችን ጨምሮ ለአሜሪካ ድምጽ ስለጉዳዩ የተናገሩ ስድስት ሰዎች፣ በዕለቱ በተፈፀመው ጥቃት ቢያንስ 38 ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል። ቁጥሩን እስከ አርባ ያደረሱት ነዋሪዎችም አሉ። በወረዳው ቢርቢሳ ጋሌ ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት አቶ አሸናፊ ቦጋለ፤ ለሥራ ጉዳይ ከቤት ውጭ እንደነበሩ ገልጸው፣ በጥቃቱ ነፍሰጡር ባለቤታቸውን ጨምሮ አራት ቤተሰብ እንደተገደለባቸው ተናግረዋል። “እናቴን፣ ልትወልድ ተቃርባ የነበረች ባለቤቲንና ልጄን በአንድ ጊዜ አጣሁ። አንደኛዋ ሴት ልጄ ህይወቷን ለማትረፍ ስትሮጥ በተተኮሰባት ጥይት ተመታ ቆስላለች” ይቺ በሕይወት የተረፈችው ልጃቸው አዳማ ሆስፒታል እንደምትገኝ አቶ አሸናፊ አክለው ገልጸዋል። ሌላው በዱግዳ ወረዳ፣ ቢርቢሳ ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት አቶ ደጀኔ ጥላሁን ፣ የ77 ዓመት አዛውንት አባታቸው በጥቃቱ እንደተገደሉባቸው ገልጸዋል። “በዕለቱ ማታ ቤት ውስጥ ሁለት ወንድሞቼ፣ ሁለት ሠራተኞችና አባቴ ነበርን። እንደ አጋጣሚ እናታችን ቤት አልነበረችም። ታጣቂዎቹ መጀመሪያ አካባቢውን የሚጠብቁ ይለስሉ ነበር። በኋላ “ወሪ ኩን” እያሉ በኦሮመኛ እየጮሁ ወደ ጊቢያችን ገቡ” በወቅቱ እርሻ ውስጥ መደበቃቸውን የሚናገሩት አቶ አሸናፊ፣ ታጣቂዎቹ የሳር ቤቶቹን አቃጥለው ትልቁን ቤት ለማቃጠል ሲሄዱ አባት ለልመና ከተደበቁበት ወተው ወደ ታጣቂዎቹ ማምራታቸውን ተናግረዋል። “እለምናቸዋለሁ ብሎ ሲሄድ ነው የተጎዳው። እናታችን ነች አስክሬኑን ያነሳችው። እጁን በስለት ተወግቷል፣ ደረቱንም በጥይት ተመቷል። ሥርዓተ ቀብሩም፣ ሐሙስ በዱግዳ ወረዳ ቢርቢሳ ጋሌ ቀበሌ መድሃኒያለም ቤተክርስትያን ተፈጽሟል።” ኩሼ ጌታቸው የተባለች ሌላ ጎረቤታቸውም መገደሏን የጠቆሙት አቶ ደጀኔ፣ “ነፍሰጡር እናትና ማየት የማይችሉ አዛውንት ጭምር ተገድለዋል። ጥቃቱ ዘግናኝ ነው። እንዲህ ያለ ዘግናኝ ድርጊት የፈጸሙት የሸኔ ታጣቂዎች ናቸው ይባላል። እኛ ምን እናውቃለን። ግራ የሚያጋባ ነው።” ብለዋል። አቶ ደጀኔ ቀበሌዉ ከሶዶ ወረዳ ጋራ እንደሚዋሰን ገልጸው፣ በጥቃቱ ዋና ዋነኛ ተጎጂዎቹ የጉራጌ እና የአማራ ብሔር ተወላጆች መኾናቸውን ተናግረዋል። ሟች አባታቸው የአማራ ብሔረሰብ ተወላጅ መኾናቸውን ጠቅሳው፣ እናታቸው ደግሞ የጉራጌ የወላጅ መኾናቸውን ተናግረዋል። ጥቃቱ ሲፈፀም ማንም የፀጥታ ኃይል ወደ አካባቢው አለመምጣቱን የተናገሩት አቶ ደጀኔ፣ አኹን የአካባቢው ሰላም አስተማማኝ ባለመኾኑ፣ የአባታቸው ቤተሰብ ቀያቸውን መልቀቃቸውን ገልጸዋል። አቶ ገመቹ አራባ የተባሉ ሌላ የደረባ ቀበሌ ነዋሪ፣ ቤተሰቦቻቸው እንደተገደሉ ተናግረዋል። “የደረሰብን ጥቃት በጣም አስደንጋጭ እና ከባድ አደጋ ነው። ለመግለፅ ቃላት የለኝም። ወንድ አያቴ እና ሁለት የአጎቴ ልጆች ተገድለውብኛል። ቤቶቻችን ተቃጥሎብናል። እንደምንም ብዬ ነው ቤተሰቦቼን ያተረፍኳቸው። የተገደሉትን ቀብረናቸው ተቀምጠናል። አሁን ራሱ ሜዳ ላይ ነው ያለነው።” አቶ ገመቹ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ተፈጸመ ባሉት ጥቃት፣ ከ40 ሰዎች በላይ መገደላቸውን ተናግረዋል። ከአንድ ቤተሰብ አምስት እና ስደስት የተገደለበት አለ። በጣክ አሳዛኝ ጥቃት የተፈፀመው መንግሥትን ትደግፋላችሁ፤ መሳሪያ ታጥቃችኃል በሚል ነው። ጥቃቱን የፈፀሙትም የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ናቸው” ብለዋል። በጥቃቱ ቤታቸው ውስጥ የነበሩ ሕጻናት፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞች ጭምር መጎዳታቸውን የተናገሩት አቶ ገመቹ “አብዛኛው የተገደሉት የሶዶ ጉራጌ ተወላጆች ናቸው። በአከባቢው የኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ቦራ የፀጥታ ኃይሎች በቅርብ ርቀት ቢኖሩም ጥቃቱን ማስቆም አልቻሉም። ከዚህ በፊትም በወረዳው ሰዎች እየታገቱ ገንዘብ እየተከፈለ ይለቀቁ ነበር።” ብለዋል። ጤሮ ተስፋ የተባሉ ሌላ የቢርቢርሳ ቀበሌ ነዋሪ በበኩላቸው በአካባቢ ዘግናኝ ያሉት ጥቃት በተደራጀ ኃይል መፈጸሙን ይናገራሉ። አቶ ጤሮ ስለግድያው ዘግናኝነት በዝርዝር አስረድተዋል። “ማየት የተሳናቸው፣ ሴቶች፣ ሕጻናት፣ ወንዶች በአጠቃላይ ወደ 40 የሚኾኑ ሰዎች ተገድለዋል። ግድያውን የፈጸመው ሸኔ የተባለ ቡድን ነው። ድርጊቱ ለአዕምሮ የሚከብድ ነው። ሰዎችን መለየት አልቻልንም ዝም ብለን አፍሰን ቀብረናቸዋል። በጥቃቱ የተጎዳው አብዛኛው የጉራጌ ማኅበረሰብ ተወላጅ ሲኾን ነዋሪው አኹን ወደ መቂና ጉራጌ እየሸሸ ነው” ብለዋል። የዱግዳ ወረዳ ቢርቢሳ ጋሌ ቀበሌ ነዋሪ የኾኑና ለደኅንነታቸው ስለሚሰጉ ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ ነዋሪ በዕለቱ ዝናብ እየዘነበ እንደነበር ገልጸው ምሽት አካባቢ ጩኸት መስማታቸውን ይናገራሉ። “ከዚያ ቤት ሲቃጠል ነው የተመለከትነዉ፣ ጥቃቱ የጀመረው ማታ አንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ ሲኾን እየጎላ የመጣው ግን ወደ ሁለት ሰዓት ነው። እናም እስከ ምሽቱ ስድስት ሰዓት ድረስ ግድያው ቀጠለ። ጥቃቱን ያደረሱት ኦሮምኛ ይናገራሉ አሉን። እኛ በጊዜው ተደብቀን ነበር። ኦነግ ሸኔ ናቸው የሚል ነገር ነው የተነገረን። በዚህ ጥቃት በሚያሳዝን መልኩ፣ ሕፃናት፣ አዛውንቶች፣ ነፍሰጡር ሴቶች ጭምር ቤት ውስጥ ተቃጥለዋል። በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው የተከሰተው።” በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓት ዱግዳ ወረዳ መፈጸሙን ተናግረዋል። “ የ38 ሟቸው ቀብር ሥነ ሥርዓት ተፈጽሟል። ከደረባ 24፣ ከኩሬ 17፣ ከቢጥሲ ደግሞ ሁለት ነበሩ። የወረዳዉ መንግሥት ባለሥልጣናት ባሉበት ነው ከተቃጠለው ቤት አስክሬን ወጥቶ ኩሬ ስላሴ ቤተክርስትያን የተቀበረው። ፈጣሪ ይርዳን እንጂ አሁን አብሮ ሲኖር የነበረ ሰው እርስ በርሱ በጥርጣሬ ዐይን እየተያየ ነው። መንግሥትም ይህን እንዴት እንደተመለከተው አላውቅም።” ነዋሪው አክለው ጥቃቱ ሲፈጸም የነበረው እስከ እኩለ ለሊት ቢኾንም፣ የፀጥታ አካላት የደረሱት ግን ማለዳ ላይ ነው ብለዋል። በጥቃቱ የኦሮሞ ተወላጅ ማኅበረሰብ አባላትም መጎዳታቸውን ተናግረዋል። “ኦሮሞ ኾኖ ቤቱ የተቃጠለበትና የተገደለም አለ። ለምሳሌ ከደረባ መኮንን የሚባለው ሰው ከተገደሉት አንዱ ነው። እሱ ኦሮሞ ነዉ፣ ሌላ የአያቴ ባል ጎሳዬ የሚባልም ተገድሏል። ነገር ግን በዚህ ጥቃት የተጎዱት አብዛኛው የጉራጌ ተወላጆች ናቸው።” ሲሉ ነዋሪው ኹኔታውን አስረድተዋል። የምስራቅ ጉራጌ ዞን ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ሃላፊ አቶ ተካልኝ ንጉሴ የተፈፀመው ጥቃት ዘግናኝ መኾኑን ተናግረዋል። ነገር ግን ተገደሉ የተባሉ ሰዎችን ቁጥር ማረጋገጥ እንደማይችሉ ገልጸዋል። ሰዎቹ የተገደሉት በመኖሪያ በታቸው እሳት ተለቀቆባቸው እና መሳሪያ ተተኩሶባቸው እንደኾነ አስረድተዋል። ሴቶች፣ አረጋዊያን፣ አቅመ ደካሞች በእሳት ተቃጥለው መሞታቸውን ገልፀዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የክልሎቹ የፀጥታ ሃይሎች አከባቢውን ለማረጋጋት ወደ ስፍራው መግባታቸውን ያስታወቁት አቶ ተካልኝ ተጎጂዎችን ለመርዳት በሁለቱም አስተዳደር በኩል ጥረት መጀመሩን ተናግረዋል። ነዋሪዎቹና የተጎጂ ቤተሰቦች ኦነግ ሸኔ ሲሉ የጠሯቸውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎችን ተጠያቂ አድርገዋል። ኖርዌይና አፍሪካ ውስጥ እንደሚኖሩ የገለጹት የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት አማካሪ መኾናቸውን የተናገሩት፣ አቶ ጅሬና ጉደታ ስለጉዳዩ መስማታቸውን ገልፀው፣ ታጣቂዎቹ ከጥቃቱ ጀርባ እንደሌሉና በመናገር አስተባብለዋል። ታጣቂዎቻቸው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት እንደማይፈጽሙም ገልጸዋል። አቶ ጅሬና ማስተባበላቸውን ገልጸን አስተያያት እንዲሰጡ የጠየቅናቸው የተጎጂ ቤተሰብ አቶ ገመቹ አራባ፣ ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች ታጣቂዎቹ ይታወቁባቸዋል ያሏቸውን መለያዎች መናገራቸውን ገልጸዋል። “ከጥቃቱ የተረፉ እና የቆሰሉ ሰዎችም አይተዋቸዋል። ሌላው ነገር ቢቀር በሹሩባቸው እንለያቸዋለን። ራሳቸው ናቸው ሰላማዊ ሰዎችን የገደሉት። ከዚህ በፊትም ራሳቸው እየመጡ ሦስት አራት ጊዜ ሞክረው አልተሳካላቸውም ነበር።” በጉዳዩ ላይ ከኦሮሚያ ክልል እና ከአካባቢው ባለሥልጣናት መረጃን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። Read more