ኢትዮጵያ በሶማሊያ ከሚሰማራው አዲስ ተልዕኮ ጋራ እንደምትተባበር አስታወቀች
newsare.net
በሶማሊያ አዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ተልዕኮ ከአል ሻባብ ጋራ ለሚያደርገው ፍልሚያ እንደምትተባበር ኢትዮጵያ አስታውቃለች፡፡ በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረኢትዮጵያ በሶማሊያ ከሚሰማራው አዲስ ተልዕኮ ጋራ እንደምትተባበር አስታወቀች
በሶማሊያ አዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ተልዕኮ ከአል ሻባብ ጋራ ለሚያደርገው ፍልሚያ እንደምትተባበር ኢትዮጵያ አስታውቃለች፡፡ በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የድጋፍና የማረጋጋት ተልዕኮ በቅርቡ ወደ ሶማሊያ እንደሚሰማራ በመጠበቅ ላይ ነው። ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋራ የፈጸመቸው የባሕር በር አቅርቦትን የተመለከተ የመግባቢያ ስምምነት በፈጠረው ውጥረት ምክንያት፣ የኢትዮጵያ ወታደሮች ተሳተፎ እንደማይኖራቸው ሶማሊያ ስታስታውቅ ብትሰነብትም፣ቱርክ ላይ በተፈጸመው የሰላም ስምምነት ውጥረቱ ሊረግብ ችሏል። የኢትዮጵያው መከላከያ ሚኒስትር አይሻ ሞሃመድ ትላንት ሐሙስ በሶማሊያ ጉብኝት በማድረግ ከሶማሊያው ፕሬዝደንት ሃሳን ሼኽ ሞሃሙድ ጋራ ተወያይተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተላከ መልዕክት ማድረሳቸውን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአወጣው መግለጫ አስታውቋል። “ውይይቱ በሶማሊያ እና በቀጠናው ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ ሁለቱ ሀገራት በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ደግመው ያረጋገጡበት ነው” ሲል የኢትዮጵያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በአወጣው መግለጫ አስታውቋል። “ሁለቱ ሀገራት የኅብረቱን ተልዕኮ በተመለከተ ትብብር ለማድረግና የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል” ሲል የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በመግለጫው አስፍሯል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው፣ ዛሬ አርብ ታኅሣሥ 25 ቀን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ “በአንካራው ስምምነት መሰረት የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ግንኙነት እንዲታደስ እየሠራን እንገኛለን” ብለዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጉብኝቶችም የዚሁ አካል እንደኾኑ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ የተመራ ልዑክ፣ ትላንት በሞቃዲሾ ከሶማሊያ ባለሥልጣናት ጋራ መወያየቱንም የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ ውይይቱ “ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የኤዩሶምን ተልዕኮ ውጤታማ ለማድረግ በትብብር ለመሥራት የተስማሙበት ነው” ብለዋል፡፡ “ኢትዮጵያ በኤዩሶም ትሳተፋለች ወይስ አትሳተፍም ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “አሁን ባለንበት ደረጃ ውይይቶች እየተካሔዱ ነው” ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ እና በሞቃዲሾ ሰሞኑን ከተደረጉት ውይይቶች በተጨማሪ “በቅርቡም በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ አዲስ አበባ ላይ ተመሳሳይ ውይይት ለማድረግ እና በጉዳዩ ዙሪያ ለመነጋገር ቀጠሮ ተይዟል” ብለዋል፡፡ በሰሞናዊው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ባለሥልጣናት ውይይት ላይ አልሻባብን ለመዋጋት የሚደረጉ ጥረቶችን ለማጠናከር መግባባት መኖሩን ጠቅሰው፣ “ከድህረ-አትሚስ በኋላ የሚኖረው የኃይል ስምሪት፣ ኢትዮጵያ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲሆን ትፈልጋለች” ብለዋል፡፡ የሶማሊያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ በዐዲሱ ተልዕኮ ለመሳተፍ “የኢትዮጵያን ጥያቄ ለመመልከት ፍላጎት አለው” ቢልም፣ ተጨማሪ ዝርዝር አልሰጠም። በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚደረገው ውይይት አስፈላጊ መሆኑን ያመለከተው የሚኒስቴሩ መግለጫ፣ “ለሶማሊያ ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት ክብር መኖሩን በድጋሚ ለማረጋገጥ” ቁልፍ እርምጃ ነው ብሏል። ኢትዮጵያ ከተገንጣይዋ የሶማሊያ ራስ ገዝ አስተዳደር ሶማሊላንድ ጋራ የተፈራረመችውን የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት አምርራ የተቃወመችው ሶማሊያ፣ የመግባቢያ ስምምነቱን እስካልሰረዘች ድረስ ኢትዮጵያ በኤዩሶም ተልዕኮ እንደማትሳተፍ አቋም ይዛ ቆይታለች፡፡ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች፣ በአገሮቻቸው መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ በቅርቡ በአንካራ ከተስማሙ በኋላም ቢኾን፣ በሶማሊያ ሰላም የማስከበር ተልዕኮ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛውን ሚና ስትጫወት የቆየችው ኢትዮጵያ በዚህ ተሳትፎዋ የመቀጠሏ ጉዳይ እልባት አላገኘም፡፡ የሶማሊያ ባለሥልጣናት በኤዩሶም ስር የሚሰለፉ አስፈላጊ 11 ሺሕ ወታደሮችን ከዩጋንዳ፣ ጅቡቲ እና ኬንያ ማግኘታቸውን የገለፁ ሲኾን፣ ከዓባይ ውሃ አጠቃቀም ጋር በተገናኘ ከኢትዮጵያ ጋራ አለመግባባት ውስጥ የምትገኘው ግብፅም፣ በሶማሊያው የአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ ስር ወታደሮቿን እንደምታሳትፍ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ገልጻለች፡፡ አዲሱ የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ - ኤዩሶም ከአውሮፓውያኑ ጥር 1 ቀን 2025 ዓ.ም ጀምሮ በሶማሊያ ኃላፊነቱን መረከቡ፣ በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ድጋፍና ማረጋጋት ተልዕኮ ኃላፊ ሞሀመድ ኤል አሚኒ ሱፍ በእለቱ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። Read more