የአሜሪካ ፕሬዚደንቶች በዓለ ሲመት ታሪክ
newsare.net
በአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ በዓለ ሲመት ትልቅ ቀን ነው፡፡ የራሱ የኾነ ወግ እና ሥርዐትም አሉት። አንዳንዶቹ ከመጀመሪያው ፕሬዝደንት በዓለ ሲመት ጀምሮ የነበሩ የየአሜሪካ ፕሬዚደንቶች በዓለ ሲመት ታሪክ
በአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ በዓለ ሲመት ትልቅ ቀን ነው፡፡ የራሱ የኾነ ወግ እና ሥርዐትም አሉት። አንዳንዶቹ ከመጀመሪያው ፕሬዝደንት በዓለ ሲመት ጀምሮ የነበሩ የክፍለ ዘመናት ዕድሜ የጠገቡ ወጎች አና ባሕሎች ናቸው፡፡ ታዲያ ሁሉም ፕሬዚደንታዊ በዓላተ ሲመት በሚፈለገው ሥርዓት አና ወግ በታቀደው መሠረት ተከናውነዋል ማለት አይደለም፡፡ እሱም ነው አንዳንዶቹን ከሌሎቹ ይበልጥ አይረሴ የሚያደርጋቸው፡፡ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1789 ዓ.ም የተከናወነው የመጀመሪያው ፕሬዝደንት ጆርጅ ዋሽንግተን በዓለ ሲመት የመጀመሪያው ፕሬዝደንት ጆርጅ ዋሽንግተን ቃለ መሐላቸውን የፈጸሙት ኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ ነበር፡፡ በወቅቱ ኒውዮርክ የአገሪቱ ጊዜያዊ መዲና ስለነበረች ነው፡፡ አሜሪካዊያን ከዚያ በፊት ፕሬዝዳንት ኖሯቸው ስለማያውቅ የምክር ቤት አባላቱ ሥነ ሥርዐቱ እንዴት ቢከናወን ይሻላል በሚል መክረው እስኪወስኑ ጆርጅ ዋሽንግተን አንድ ሳምንት መጠበቅ ነበረባቸው፡፡ ከዚያ በኋላ እ አ አ ሚያዚያ 30 ቀን ላይ ፕሬzደንቱ እና ምክትላቸው እንዲሁም የምክር ቤቱ አባላት የHግ መወሰኛው ምክር ቤት ውስጥ ከተሰባሰቡ በኋላ በረንዳው ላይ ወጥተው ደጅ ለሚጠባበቀው ታዳሚ እጃቸውን በማውለብለብ ሰላምታ ሰጡ፡፡ በመቀጠል ቃለ መሐላውን የሚያስፈጽሟቸው ዳኛ «በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንትነት የተጣለብዎትን ኅላፊነት በታማኝነት ይወጣሉ? ብለው ጠየቋቸው፡፡ ጆርጅ ዋሽንግተን በአዎንታ ቃለ መሐላቸውን ሰጡ፡፡ ይህ ቃለ መሐላ እንዳለ በአሜሪካ ሕገ መንግሥት ውስጥ የተቀመጠ ነው፡፡ ዳኛው ጆርጅ ዋሽንግተን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ምለው ቃል እንዲገቡ ለማድረግ ነበር ያቀዱት፡፡ ነገር ግን የሚከናወንበት ሰዓት ሲቃረብ ዳኛው መጽሐፍ ቅዱስ እንዳላመጡ ባወቁ ጊዜ በጥድፊያ ሰው ተልኮ ከሌላ ቦታ መጽሐፍ ቅዱስ በውሰት መጥቶ ጆርጅ ዋሽንግተን ቃለ መሐላቸው ፈጸሙ፡፡ ዋሽንግተን ቃለ መሐላቸውን ከፈጸሙ በኋላ ያዘጋጁትን ንግግር በሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ አባላት ፊት አነበቡ፡፡ ዊሊያም ማክሌይ የተባሉ ሴኔተር በግል ማስታወሻቸው ላይ ዋሽንግተን ንግግራቸውን ሲያነቡ ተጨናንቀው እጃቸው ይንቀጠቀጥ እንደነበር ማንበብ አስቸግሯቸው እንደነበረም ጽፈዋል፡፡ አዲሱ ፕሬዚደንት ዋሽንግተን ግር ቢላቸውም ሥነ ሥርዓቱ እጥር ጥፍጥ ያለ እንደነበር አክለዋል፡፡ ቶማስ ጀፈርሰን በ1801 ዓ.ም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1801 ዓ.ም የሦስተኛው ፕሬዝደንት የቶማስ ጄፈርሰን በዓለ ሲመት ደግሞ ከጆርጅ ዋሽንግተን በዓለ ሲመት ይበልጥ ቀለል ብሎ የተከናወነ ነበር፡፡ ቶማስ ጄፈርሰን ወደ በዓለ ሲመቱ ሥነ ሥርዐታቸው የሄዱት ከሳቸው በፊት እንደነበሩት ሁለቱ ቀደምቶቻቸው በሠረገላ ሳይሆን በእግራቸው ተጉዘው ነው፡፡ የአሜሪካ ምክር ቤት ካፒቶል ሲደርሱ ብዙ ሕዝብ ሲጠብቃቸው ነበር፡፡ ንግግራቸውንም አዘጋጅተው ነበር፡፡ ነገር ግን ድምጻቸው በጣም ድክም ያለ ስለነበረ ንግግራቸውን ሊሰማ የቻለው በጣም ጥቂት ሰው እንደነበር ታሪክ መዝግቦታል፡፡ ቢሆንም ዛሬ ያ የቶማስ ጄፈርሰን የበዓለ ሲመት ንግግር በአሜሪካዊያን ዘንድ በሚገባ ይታወቃል፡፡ በምርጫ ዘመቻው ወቅት በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የነበረውን አስቀያሚ ጭቅጭቅ ለማርገብ ያደረጉት ንግግር አድናቆት አትርፏል፡፡ ሆኖም የምርጫው ዘመቻው ጭቅጭቅ የተወው አስከፊ ገጽታ ቀጠለ እና ከጄፈርሰን ጋራ የተፎካከሩት ከሳቸው በፊት የነበሩት ፕሬዚደንት ጆን አዳምስ በጄፈርሰን በዓለ ሲመት ላይ ሳይገኙ ቀሩ፡፡ በዓለ ሲመቱ ነገ ሊሆን በዋዜማው ምሽቱ ላይ ጓዛቸውን ጠቅልለው ከዋይት ሐውስ ወጡ እና ወደቦስተን ተመለሱ፡፡ ዊሊያም ሄንሪ ሃሪሰን በ1841 ዓ.ም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1841 የዘጠነኛው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሄንሪ ሃሪሰን የቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓት ታሪክ ሳይወሳ የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች በዓለ ሲመት ታሪክ ተወሳ ለማለት አይቻልም፡፡ ሲመረጡ የ68 ዓመት ሰው የነበሩት ዊሊያም ሃሪሰን በዘመኑ ከነበሩት ፕሬዝደንቶች ሁሉ በዕድሜ ትልቁ ነበሩ፡፡ ታዲያ እንደሚባለው በፕሬዝደንትነት ለማገልገል ጠንካራ መሆናቸውን በጣም ረጅም ንግግር በማድረግ ለማሳየት አስበው ነው ይባላል ኃይለኛ ቅዝቃዜ በነበረበት የበዓለ ሲመታቸው ዕለት ጭንቅላታቸውን በብርድ ቆብ ሳይሸፍኑ ካፖርትም ሳይደርቡ ቆመው ረጅሙን ንግግራቸውን አደረጉ፡፡ ያ በሆነ በወሩ አዲሱ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሃሪሰን ታምመው ሞቱ፡፡ ሥልጣን ላይ ሆነው ሕይወታቸው ያለፈ የመጀመሪያ ፕሬዝደንት ናቸው፡፡ ሐኪማቸው ፕሬዝደንቱን ለሕልፈት የዳረጋቸው የሳምባ ምች ወይም ኒውሞኒያ ነው ብለዋል፡፡፡በተለምዶ ግን ብዙዎች ረጅሙ ንግግራቸው የገደላቸው ፕሬዚደንት ይሏቸዋል፡፡ የሐሪሰን አሟሟት እ አ አ በ2014 ምርምር ተደርጎበት ነበር፡፡ ተመራማሪዎቹ ጄን ሜክሂዩ እና ፊሊፕ ሜክውላክ ሃሪሰን የሞቱት በሳምባ ሕመም ሳይሆን በሌላ ምክንያት ነው ይላሉ፡፡ እነሱ እንደሚሉት ሃሪሰን የታመሙት ከበዓለ ሲመታቸው በኋላ ወዲያውኑ ሳይሆን ቆይተው ከሦስት ሳምንታት በኋላ ነው፡፡ የነበራቸውም የሕመም ስሜት ድካም እና ጭንቀት እንጂ ሳምባቸው ላይ እንዳልነበረ ይናገራሉ፡፡ ተመራማሪዎቹ እንዳሉት ከሆነ በጊዜው ዋሽንግተን ዲሲ ጥሩ የፍሳሽ ማስወገጃ አገልግሎት ስላልነበራት የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽ ከኋይት ሐውስ በቅርብ ርቀት ሜዳ ላይ ይፈስ ስለነበረ ምናልባት በባክቴሪያ የተበከለ ውሃ ጠጥተው ሳይታመሙ አልቀሩም ሲሉ ተመራማሪዎቹ ድምዳሜአቸውን ኒው ዮርክ ታይምስ ላይ አስነብበዋል፡፡ የ30ኛው ፕሬዚደንት ካልቭን ኩሊጅ በ1923 ዓ.ም ስለ ፕሬዝደንቶች በዓለ ሲመት ሲወሳ ታዲያ የሁሉም የቃለ መሐላ ሥነ ሥርዐት አይረሴ ነው ማለት አይደለም፡፡ የ30ኛው ፕሬዚደንት ካልቭን ኩሊጅ በዓለ ሲመት ቀዝቀዝ ባለ ድባብ ከተከናወኑት ውስጥ የሚጠቀስ ነው፡፡ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ኩሊጅ እ አ አ በ1923 ነሃሴ ወር ውስጥ ብዙም የሥራ ኃላፊነት ስላልነበረባቸው ቨርሞንት ወደሚኖሩት ቤተሰቦቻቸው ቤት ለዕረፍት ሄደው ነበር፡፡ አንድ ቀን ሌሊት በተኙበት አባታቸው ይቀሰቅሷቸው እና ቴሌግራም እንደተላከላቸው ይነግሯቸዋል፡፡ ፕሬዚደንቱ ዋረን ሀርዲንግ አርፈዋል የሚል መርዶ የያዘ ቴሌግራም ነበር፡፡ በዚያ ኩሊጅ ፕሬዝደንት ሆኑ፡፡ ኩሊጅ በግል ማስታወሻቸው ላይ ይህንን ባውቅኩ ጊዜ መጀመሪያ ተነስቼ ቆምኩ እና ጸለይኩ፡፡ ከዚያም ከሕገ መንግሥቱ ውስጥ የፕሬዝደንት ቃለ መሐላው ያለበትን አውጥቼ ለአባቴ ያዘው ብዬ ሰጠሁት፡፡ ከዚያም ተመልሼ ጥቅልል ብዬ ተኛሁ ብለው እንደጻፉ ተመልክቷል፡፡ ሊንደን ጆንሰን 1963 ዓ.ም ቀደም ሲል ከተነገረው በተጻራሪ ድንገተኛ ሐዘን የተመላበትን ሊንደን ጆንሰን 36ኛው ፕሬዚደንት ሆነው ቃለ መሓላ የፈጸሙበትን ቀን አይረሴ ነው፡፡ ጆንሰን ቃለ መሃላ የፈጸሙት ፕሬዚደንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ በሰው እጅ በጥይት ከተገደሉ ከአንድ ሰዓት ተኩል በኃላ ነበር፡፡ ጆንሰን በፕሬዝደንታዊው አውሮፕላን ኤር ፎርስ ዋን ውስጥ ቀኝ አጃቸውን ከፍ አድርገው ቃለ መሃላ ሲፈጽሙ የተነሳው ፎቶግራፍ ታሪኩን ይናገራል፡፡ በስተቀኛቸው ባለቤታቸው በስተግራቸው የሟቹ ፕሬዚደንት ባለቤት ጃኪ ኬኔዲ አጅበዋቸው ይታያሉ፡፡ ሊንደን ጆንሰንን ቃለ መሐላውን ያስፈጸሟቸው ሴት ዳኛ ሲሆኑ እስካሁን በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ ፕሬዝደንትን ቃለ መሐላ ያስፈጸሙ ብቸኛዋ ሴት ዳኛ ናቸው፡፡ በፎቶው ላይ ሚስስ ኬኔዲ በባለቤታቸው በሰው እጅ መገደል የነበሩበት ድንጋጤ እና ሐዘን ፊታቸው ላይ ይነበባል፡፡ ጆንሰን ቃለ መሐላ ላይ ሲፈጽሙ ጎናቸው የቆሙትም ባለቤታቸው በጥይት በተገደሉበት ጊዜ ለብሰውት የነበረውን ያንኑ ልብስ እንደለበሱ ነበር፡፡ ምስሉ ፕሬዝደንቱ በሰው እጅ ለተገደሉበት የአሜሪካ ሕዝብ ተተኪ ፕሬዝደንት መሰየሙን በስተቀር ባልተጠበቀ ምስቅልቅል ሁኔታ ውስጥም ቢሆን የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ሥራ እንደሚቀጥል እምነት እንዲያድርበት ያደረገም ነበር፡፡ ታዲያ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ሥራ ሁልጊዜ ያለ እንከን ይከናወናል ማለት አይደለም፡፡ በታቀደላቸው ስርዐት መሠረት ያልተከናወኑ ብዙ በዓለ ሲመቶች አሉ፡፡ በሥነ ሥርዓት ያልተከናወኑ በዓለ ሲመቶች የወፍ ምስል ወደ ጥንት ወደ እ አ እ 1829 ዓም መለስ ብለን የአንድሩው ጃክሰንን በዓለ ታሪክን ብንቃኝ ቃለ መሓላቸውን ከፈጸሙ በኋላ በኋይት በነበረው ድግሥ ላይ የታደሙ ደጋፊዎቻቸው እጃቸውን እየጨበጡ ደስታቸውን ለመግለጽ ጓጉተው ሲረባረቡ አዲሱን ፕሬዝደንት ከግድግዳ ጋር አጣብቀው ሊደፈጥጧቸው ምንም አልቀራቸውም ነበር፡፡ ፕሬዝደንቱ በመስኮት ወጥተው እንዳመለጡ ታሪክ ይናገራል፡፡ በ1865 ደግሞ የፕሬዝደንት አብራሃም ሊንከን ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው የተመረጡት አንድሩ ጆንሰን በቃለ መሐላ ሥነ ስርዐታቸው ላይ በስካር መንፈስ ንግግር ማድረጋቸው ተመዝግቧል፡፡ አሟቸው ስለነበረ ለህመም ማስታገሻ እንዲሆናቸው የወሰዱት ዊስኪ ነው ያሰከራቸው የሚል ምክንያት እንደተሰጠላቸው ተጽፏል፡፡ በ1873 ዩሊሰስ ኤስ ግራንት በበዓለ ሲመታቸው ድግስ ላይ »በድግሱ ቦታ ሰማያዊ ወፎች ቢበሩልኝ እንዴት ደስ ባለኝ ብለው ነበር" እና ሐሳባቸው ይሙላ ተብሎ ወፎች ለትዕይንት እንዲበሩ ተደረገ፡፡ ክፋቱ ብርዱ ነበር እና ወፎቹን ክንፋቸውን እያደረቀ እንዳረገፋቸው ይነገራል፡፡ የወፍ ነገር ከተነሳ እ አ አ በ1973ም ሪቻርድ ኒክሰን ርግቦች የበዓለ ሲመታቸው የሰልፍ ትዕይንት በሚያልፍበት መንገድ እንዳይገኙ ለማባረር ኬሚካል አስረጭተው ነበር እና የበዐሉ ታዳሚዎች የዋሽንግተኑ ፔንሲልቬኒያ አቨኑ ጎዳና ላይ መደዳውን ኬሚካሉ የገደላቸውን ርግቦች ሬሳ እንዳይረግጡ እየዘለሉ ያልፉ እንደነበር በፕሬዝደንታዊ በዓለ ሲመት ታሪክ ተመዝግቧል፡፡ Read more