ህወሓት ከተፈናቃዮች «በግዳጅ የገንዘብ መዋጮ በመሰብሰብ» አቤቱታ ቀረበበት
newsare.net
- «ከተፈናቃዮች በፈቃዳቸው የሚያዋጡ እንጂ በዕቅድ የሚሰበሰብ የፓርቲ ገንዘብ የለም፤» /ህወሓት/ህወሓት ከተፈናቃዮች «በግዳጅ የገንዘብ መዋጮ በመሰብሰብ» አቤቱታ ቀረበበት
- «ከተፈናቃዮች በፈቃዳቸው የሚያዋጡ እንጂ በዕቅድ የሚሰበሰብ የፓርቲ ገንዘብ የለም፤» /ህወሓት/ Read more
- «ከተፈናቃዮች በፈቃዳቸው የሚያዋጡ እንጂ በዕቅድ የሚሰበሰብ የፓርቲ ገንዘብ የለም፤» /ህወሓት/ Read more
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ሦስት ዓመት የተጠጋውን የዩክሬን ጦርነት ለማስቆም የታለመውን የዲፕሎማሲ ዘመቻቸውን ትላንት ረቡዕ ከፍተዋል፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን ለምታደርግላት ድጋፍ በምላሹ የሚጠብቁባት የሚመስሉትን ሁኔታዎችም ዘርዝረዋል፡፡ ትረምፕ በኋይት ሃውስ ኦቫል ኦፊስ ጽሕፈት ቤታቸው እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር በ2022 ሩስያ በከፈተችው ወረራ የተቀሰቀሰውን የዩክሬን ጦርነት በሚመለከት ጋዜጠኞች ላቀረቡላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ «ለምንሰጠው ገንዘብ በምላሹ ጸጥታ እንዲኖር እንፈልጋለን» ብለዋል፡፡ የቀድሞውን ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ለኪቭ የሚሰጡትን ድጋፍ በሚመለከት « ገንዘባችንን ስንሰጥ በምላሹ በብድር መልክ አለያም በጸጥታ ወይም ደግሞ በነዳጃቸው ወይም በጋዛቸውም ቢሆን አንድ ነገር መጠየቅ አለብን ብያቸው ነበር» ብለዋል፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ከ2022 ጀምሮ ለዩክሬን ወደ183 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወታደራዊ እና ወታደራዊ ያልሆነ ርዳታ መፍቀዱን ትላንት ለምክር ቤቱ የቀረበው የቁጥጥር ሪፖርት አመልክቷል፡፡ ከተፈቀደው ርዳታ እስካሁን ለዩክሬን ያልተላከው 40 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ ቀደም ሲልም ማክሰኞ ምሽት ፕሬዝደንት ትረምፕ ከሩስያ እስር ቤት የተለቀቁትን አሜሪካዊ መምህር ማርክ ፎግል በኋይት ሀውስ ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡ ከዚያም በማስከተል ትላንት ዕኩለ ቀን ላይ ከሩስያ ፕሬዝደንት ቭላዲሚር ፑቲን ጋራ በስልክ መነጋገራቸውን እና ጦርነቱን ለማስቆም በአስቸኳይ ከዩክሬን ፕሬዝደንት ዜሌንስኪ ጋራ ድርድር ለመጀመር መስማማታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ቀጥለውም ምክትል ፕሬዝደንታቸውን ጄ ዲ ቫንስን እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማርኮ ሩቢዮን ከዜሌንስኪ ጋራ እንዲነጋገሩ ወደሚዩኒክ ልከዋቸዋል፡፡
አክራሪው ሃማስ ከእስራኤል ጋራ የተደረሰውን የተኩስ አቁም ውል እንደሚያከብር ዛሬ ሐሙስ ቃል ገብቷል፡፡ ይህ የሆነው ተኩስ አቁሙን ጥሷል በማለት አንዱ ሌላኛውን ወገን እየወነጀሉ ባሉበት እና ጦርነቱ ሊያገረሽ ይችላል የሚል ስጋት በሚሰማበት በዚህ ወቅት ነው፡፡ የሃማስ ቃል አቀባይ አብደል ላቲፍ አል ካኑዋ “የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈርስ አንፈልግም፡፡ ስለዚህም አፈጻጸሙ በጥንቃቄ ሥራ ላይ እንዲውል ብርቱ ፍላጎት አለን” ያሉ ሲሆን «ወራሪዋ እስራኤልም ይሄን እንድታረጋግጥ» ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ካኑዋ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ እና ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሚሰነዘር “የማስፈራራት እና የዛቻ ቋንቋ” የተኩስ አቁም ስምምነቱን አፈጻጸም አያግዝም ብለዋል፡፡ ሃማስ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ እስራኤል በጋዛ የአየር ድብደባ በመፈጸም እና ርዳታ እንዳይገባ በመገደብ ስምምነቱን ጥሳለች ሲል የከሰሰ ሲሆን፤ ቡድኑ የሚለቀቁት ታጋቾች ለሌላ ጊዜ እንደሚያስተላልፍም ተናግሯል። ትላንት ረቡዕ እስራኤል ወታደራዊ ተጠባባቂዎቿን ከጠራች በኋላ፤ የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ የትረምፕን ማስጠንቀቂያ ደግመዋል። ካትዝ “ሃማስ ታጋቾቹን መልቀቅ ካቆመ የተኩስ አቁሙ አይኖርም፤ ጦርነት ይሆናል ማለት ነው።” ያሉ ሲሆን ጦርነቱ የበለጠ ጠንካራ እንደሚሆን እና “ትራምፕ ለጋዛ ያላቸውን ራዕይ እውን ለማድረግ የሚያስችል ይሆናል” በማለት አክለዋል። የተኩስ አቁም ስምምነቱ ባለፈው ወር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፤ በዩናይትድ ስቴትስ በአሸባሪነት የተፈረጀው ሃማስ 21 ታጋቾችን ሲለቅ በአንጻሩ እስራኤል ከ730 በላይ እስረኞችን መልቀቋ ይታወሳል። የፊታችን ቅዳሜ በሚካሄደው የታጋቾች ልውውጥ በእስራኤል በመቶዎች በሚቆጠሩ የፍልስጤም እስረኞች ለውጥ ተጨማሪ ሶስት እስራኤላውያን እንዲፈቱ ተጠይቋል። የጋዛ ጦርነት የተቀሰቀሰው በጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 2023 ሃማስ በእስራኤል ላይ ባደረሰው የሽብር ጥቃት 1200 ሰዎችን ገድሎ፤ 250 ሰዎችን ማገቱን ተከትሎ ነው ። እስራኤል በፈጸመችው የአጸፋ ጥቃት ከ48 ሺህ 200 በላይ ፍልስጤማውያንን የተገደሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውን የአካባቢው የጤና ባለሥልጣናት አስታውቀዋል፡፡ እስራኤል በበኩሏ ከተገደሉት ወስጥ 17 ሺህ የሚሆኑት ታጣቂዎች ናቸው ብላለች፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ወደ ኋይት ሃውስ በተመለሱበት የሥልጣን ዘመናቸው መጀመሪያ ቀን ከፈረሟቸው ፕሬዝዳንታዊ የሥራ ማስፈጸሚያ ትእዛዞች መካከል ስደተኞችን የተመለከተው አንዱ ነው፡፡ ትእዛዙን ተከትሎ፣ በአሜሪካ በሕገ ወጥ መንገድ የሚኖሩና በወንጀል አድራጎት ውስጥ የተሳተፉትን ወደ አገራቸው የመመለስ ሥራ ተጀምሯል፡፡ ለመኾኑ፣ ይኸው ፕሬዘዳንታዊ ትእዛዝ በውስጡ ያካተታቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው? ከዚኹ ጋራ በተያያዘስ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ሊያውቋቸው የሚገቡ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?አስማማው አየነው፣ በካሊፎርኒያ ሎስ ኤንጀለስ አካባቢ የኢምግሬሽን ጉዳዮች ጠበቃ ከኾኑት ወ/ሮ ሙሉ እመቤት ዓለማየሁ ያደረገው ቆይታ ምላሹን ይዟል። ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ ኹኔታ፣ ጋዜጠኞች፥ በነጻነት ዘገባዎችን እንዳይሠሩ አዳጋች እየኾነ መምጣቱን፣ በልዩ ልዩ ብዙኀን መገናኛዎች ላይ የሚሠሩ ባለሞያዎች እና የሞያው ማኅበራት ይናገራሉ። እስር፣ የመረጃ ዕጦት እና አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ኹኔታም ከሚገጠሟቸው ፈተናዎች መካከል መኾናቸውንም ገልጸዋል። አስተያየት ሰጪዎቹ፣ መንግሥት ብዙኀን መገናኛን በተመለከተ የወጡትን ሕጎች ተግባራዊ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡ በዚኽ ጉዳይ ላይ፣ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ሓላፊዎች ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
የዩናይትድ ስቴትስ፣ የብሪታንያ፣ የጀርመን፣ የጣልያን፣ የፈረንሳይ እና የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደሮች እና ተወካዮች ከትግራይ ክልል ጊዝያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ እና ከህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ጋራ ተወያዩ። በኢትዮጵያ የዩናትድ ስቴትስ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ፣ ማክሰኞ የካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም የዩናይትድ ስቴትስ፣ የታላቋ ብሪታንያ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ፈረንሳይ እና አውሮፓ ኅብረት አምባሳደሮች እና ተወካዮች በፕሪቶሪያ የተፈረመው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት አስመልከቶ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ እና ከህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ጋራ ተገናኝተው እንደተወያዩ አስታውቋል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በወይይቱ ወቅት «የፕሪቶርያው ስምምነት በምልዓት ባለመተግበሩ ተፈናቃዮችን ለመመለስ አልተቻለም፣ የትግራይን ችግርም ለመፍታትም አልተቻለም» ሲሉ ለልዑካኑ ተናግረዋል። “በፕሪቶሪያ የተፈረመው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ትግበራ ላይ ያሉት ለውጦች እና በትግበራው የሚያጋጥሙ እንቅፋቶችን አስመልክቶ ከአሁን በፊት ያካሄደነው ውይይት ተከታይ ነው። በዚህ ውይይትም የሚያጋጥሙን ችግሮች መፍትሄ ለማስገኘት ያግዛል። የስምምነቱ አንኳር የሆነው ተፈናቃዮች ወደ ቀየ መመለስ አለመፈፀም አሁን የገጠመን ችግር ነው። በትግራይ በአሁኑ ግዜ ያለው ፖለቲካዊ ቀውስ መነሻውም ይህ አለመፈፀሙ ነው።” ብለዋል አቶ ጌታቸው። ልዑካኑን የመሩት በኢትዮጵያ የብሪታኒያ አምባሳደር ዳረን ዊልች በበኩላቸው፣ «የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች በብዛት ሆነው ወደ መቐለ የተጓዙት የፕሪቶሪያው ሰምምነት በምልዓት እንዲተገበር ባላቸው ፍላጎት ነው» በማለት አስረድተዋል። «መምጣታችን ግጭትን በዘላቂነት ለማቆም የተደረሰው ስምምነት በተሻለ መልኩ እንዲተገበር ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ እንደሚፈልግ ማሳያ ነው። ስምምነቱ እንደግፋለን። የስምምነቱ ትግበራ ብዙዎች እንደሚሹት በፍጥነት እየተተገበረ እንዳልሆነ እንረዳለን። ይህ ውይይታችን ስለሁኔታው በተሻለ ለመረዳት ያግዘናል፣ እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ስምምነቱን ለመፈፀም የሚጠበቅበትን እገዛም እንድንመለከት ያግዛል” ብለዋል አምባሳደሩ። ልዑካኑ ከህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረሚካኤል ጋራም እንደተወያዩ ፓርቲው በፌስቡክ ገፁ አስታውቋል። ዶክተር ደብረፅዮን በውይይቱ የፕሪቶርያ ስምምነት በምልዓት ባለመተግበሩ የክልሉ ህዝብ ስቃይ፣ መከራ እና እንግልት ቀጥሏል። ተፈናቃዮች በመጠለያ ካምፕ እየተንገላቱ ይገኛሉ» በማለት ለልዑካኑ ገልፀውላቸዋል። የስምምነቱ መተግበር ለዘላቂ ሰላም ትልቅ ሚና እንዳለውም አስረድተዋል። የትግራይ የወሰን አስተዳደር ወደ ቅደመ ጦርነት እንዲመለስ፣ ተፈናቃዮች እንዲመለሱ እና የክልሉ የመልሶ ግንባታ ሥራ እንዲጀመር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና እንዲያሳድር ጠይቀዋል። ልዑካኑ በመቐለ ሰብዓ ካሬ ተብሎ የሚያወቀውን የተፈናቃኖች ካምፕ ጎብኝተዋል።
ዓለም አቀፉ የጸረ ሙስና ድርጅት ‘ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል’ በያዝነው ሳምንት ይፋ ባደረገው የሀገራት የሙስና ይዞታ ዓመታዊ ሪፖርቱ እንዳመለከተው፡ 72 ነጥብ ያስመዘገበችው ሲሼልስ ከአፍሪካ ሀገራት በሙሉ በሙስና ዝቅተኝነት ቀዳሚዋ ሀገር ስትሆን፤ ካቦ ቨርዲ በ62፣ ቦትስዋና በ57፣ ሩዋንዳ ደግሞ በ57 ነጥቦች በደረጃው ሰንጠረዥ ተከታታዩን እርከኖች ተቆናጠዋል። በሪፖርቱ መሰረት ክፉኛ በሙስና የተዘፈቁት የአፍሪካ ሀገራት ተርታ 8 ነጥብ ያስመዘገበችው ሶማሊያ 9 ነጥብ ያስመዘገበችው ደቡብ ሱዳን፡ እንዲሁም በተመሳሳይ 13 ነጥቦች ያስመዘገቡት ሊቢያ፣ ኤርትራ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ ይገኙባቸዋል። ከሁለት ዓመት በፊት እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2023 ከወጣው መረጃ ጋራ ሲነጻጸር ኤርትራ በ8 ነጥብ ዝቅ በማለት ከቀድሞውም በከፋ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በ99ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ዘንድሮም እንዳለፈው ዓመት 37 ነጥብ ነው ያስመዘገበችው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ዴንማርክ በ90 ነጥብ በሙስና ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ ፊንላንድ በ88 ነጥብ፣ ሲንጋፖር ደግሞ በ84 በሁለተኛ እና በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ዩናይትድ ስቴትስ በአንጻሩ በ65 ነጥብ 28 ላይ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ በብረታ ብረት እና አሉሚነም ላይ ትላንት ሰኞ የ25 ከመቶ ቀረጥ ጥለዋል። በቀረጡ በጣም የሚጎዱት ለአሜሪካ ዋናዎቹ የብረታ ብረት እና አሉሚነም አቅራቢዎች የሆኑት ካናዳ እና ሜክሲኮ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተመልክቷል። ትረምፕ ንግድን በሚመለከት እየወሰዱ ያሉት ርምጃ ከዋናዋ የዩናይትድ ስቴትስ ተቀናቃኝ ከቻይና በኩል የበረታ ነቀፌታ አስከትሏል። የአሜሪካ ድምጽ የኋይት ሐውስ ዘጋቢ አኒታ ፓወል ያጠናቀረችው ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
ጦርነት፣ ግጭት አለመረጋጋት እና ሰላም ማጣት በወጣቶች ህይወት ላይ ምን ዐይነት ተፅዕኖ እንደፈጠረ የወጣቶችን አስተያየት ጠይቀናል። ምላሻቸውን ከተያያዘው ፋይል ማግኘት ትችላላችኹ። በሌላ በኩል እናንተም አስተያየታችኹን አጋሩን፣ በአካባቢያችሁ ያለው የሰላም ሁኔታ በኑሮአችኹ ላይ ያስከተለው ጫና ምን ይመስላል? የማኅበረሰቡን ችግር ለምቅረፍም ኾነ በሰላም ዙሪያ ለማገዝ የወጣቶች ተሳትፎ ምን ሊኾን ይገባል ትላላችኹ? አስተያየታችኹን አጋሩን።
መንግሥት፣ በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚታዩትን አለመረጋጋቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ወጣቶች ጥሪ አቀረቡ፡፡ ባለፈው ሣምንት አዲስ አበባ ላይ በተካሔደ ሀገር አቀፍ የወጣቶች መድረክ ላይ የተሳተፉ ወጣቶች፣ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት አስተያየት፣ በሀገሪቱ የሚታዩት ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ወጣቱ በነፃነት እንዳይሠራ እያደረጉት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ወጣቶቹ፣ መንግሥት ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ እንዲሰጥ እና የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተቃሚነት እንዲያረጋግጥም ጠይቀዋል፡፡ ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
ከልጅነቱ ጀምሮ አንድ እግሩ አልታዘዝ ያለው መለስ እዮብ፣ አካል ጉዳተኛ መኾኑ ሌሎች መደገፊያ ያጡ አካል ጉዳተኛ ኢትዮጵያውያን ከመርዳት አላገደውም። ከብዙ ዓመታት በፊት አንድ መንግሥታዊ ያልኾነ ድርጅት በሰጠው ክራንች ድጋፍ ያደገው መለስ፣ አንድ ቀን ድጋፉ በመሰበሩ ወድቆ ዳግም ተጎድቶ እንደነበር ያስታውሳል። በወቅቱ የነበረው ሁኔታም ለሌሎች በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ለሚያልፉ ሰዎች ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል አዲስ ነገር ማቋቋም እንዳለበት እንደወሰነ ገልጿል። ሆስፒታል ተቀጥሮ በመሥራት ያገኘውን ገንዘብ አጠራቅሞና፣ ከጓደኞቹ ያገኘውን ጨምሮ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ድጋፍ መስጠት መጀመሩን አስታውቋል። ] በዚህ ዙሪያ የተሰናዳውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
ዓመታዊው የአውሮፓ ፊልም ፌስቲቫል ጥር 23 በአዲስ አበባ ከተማ ተከፍቶ፣ በዛ ያሉ ፊልሞች ታይተዋል። በዝነኛው የቼክ ሪፓብሊክ አትሌት ኤሚል ዛቶፔክ ሕይወት ላይ ያተኮረው ዛቶፔክ ፊልም በመክፈቻው ዕለት ለዕይታ ሲበቃ፣ በአጠቃላይ ሁለት ተጋባዥ የኢትዮጵያ ፊልሞችን ጨምሮ 28 ፊልሞች ለእይታ እንደሚበቁ ታውቋል፡፡ ፊልሞች “ሰዎች እርስ በርስ እንዲተዋወቁ የማድረግ አቅም አላቸው” ያሉት በአፍሪካ ኅብረት የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሃቪየር ኒኞ ፔሬዝ፣ የፌስቲቫሉ ዓላማም ሰዎችን ይበልጥ በማቀራረብ መተባበርን ማጎልበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዙሪያ የተሰናዳውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
በአፍሪካ የማዕድን ዘርፍ ላይ ያተኮረ ጉባኤ ባለፈው ሳምንት ደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ኬፕ ታውን ውስጥ ተካሂዷል። ለአራት ቀናት የተካሄደው ጉባኤ በአመዛኙ ያተኮረው የትረምፕ አስተዳደር የውጭ ርዳታ ፖሊሲ በውል ባልለየበት ሁኒታ አሜሪካ በአፍሪካ የማዕድን ዘርፍ ምን ዓይነት ተሳትፎ ታደርጋለች በሚለው ላይ ነበር፡፡ በስፍራው ተገኝታ ጉባኤውን የተከታተለችው ቪኪ ስታርክ ያጠናቀረችውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
ደራሲ ሳልማን ሩሽዲን ኒው ዮርክ ውስጥ በተካሄደ በአንድ ትምህርታዊ ስብሰባ ላይ ሳለ በቢላ ወግቶ ለመግደል የሞከረው ግለሰብ የፍርድ ቤት ሂደት ዛሬ ሲጀመር፣ የከሳሽ ጠበቆች የመክፈቻ ክርክራቸውን ማሰማት ጀምረዋል። ሩሽዲ በፍርድ ቤቱ እንዲመሰክር የሚጠበቅ ሲሆን፣ በመግደል ሙከራ ከተከሰሰው ሃዲ ማታር ጋራ ከጥቃቱ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ይገናኛል ተብሏል። ከሁለት ዓመታት በፊት በኒው ዮርክ በተዘጋጀና ደራሲያን ደኅንነታቸውን እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸው ባተኮረ ስብሰባ ላይ በመናገር ላይ ሳለ ነበር ሃዲ ማታር ወደ መድረኩ በመሄድ ሩሽዲን ከ12 ጊዜ በላይ በበርካታ የሰውነቱ ክፍሎች ላይ በቢላ የወጋው። ጥቃቱ ሩሽዲን በከፊል ማያት የተሳነው እንዲኾን ሲያደርግ አንድ እጁ ላይም ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። ትውልዱ ከህንድ የሆነውና የአሜሪካና የእንግሊዝ ጥምር ዜግነት ያለው ሩሽዲ፣ በጥቃቱ ላይ ያተኮረ ግለ ታሪክ መጽሓፍ ባለፈው ዓመት አሳትሟል። ሩሽዲ በእ.አ.አ 1989 ያሳተመውና “ሳታኒክ ቨርስስ” የተሰኘው መጽሐፍ እስልምናን የሚያንቋሽሽ ነው በሚል በበርካታ የሃይማኖቱ ተከታዮች ይወገዛል። የኢራኑ አያቶላ ኾሚኒም ሩሽዲ እንዲገደል ፋትዋ አውጥተው ነበር። ኢራን ትዕዛዙን እንደማትፈጽም መግለጿን ተከትሎ ለረጅም ጊዜ ተደብቆ የነበረው ሩሽዲ እንደልብ መዘዋወር ጀምሮ ነበር።
ጥር ወር ደቡባዊ ኢትዮጵያ ለሚገኙ የጌዴኦ ብሔረሰብ አባላት የመኸር ምርታቸውን የሚሰበስቡበትና፣ አሮጌ ያሉትን ዓመት “አዲስ” ብለው የሚቀበሉበት ዓመታዊ በዓላቸውን ነው። ይኽን ጊዜ የመረጡትና የሰየሙትም በአካባቢው ደምቃ በምትወጣው “ደራሮ” አበባ ምክኒያት ነው። ቅዳሜ ዕለት በዲላ ከተማ የተከበረው በዓል ይዘት ምን እንደሚመስል ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
የፊላደልፊያ ኢግልስ ቡድን የካንሳስ ቺፍስ ቡድን ላይ የበላይነትን በመቀዳጀት የዘንድሮው የአሜሪካ እግር ኳስ ሊጎች የፍጻሜ ጨዋታ «ሱፐር ቦል» አሸናፊ ኾነ። አሸናፊው ቡድን ያለፈው ዓመት ቻምፒዮንተ ፎካካሪውን የረታው 40-22 በኾነ ውጤት ነው። የካንሳስ ቺፍ ቡድን ለሦስተኛ ተከታታይ ዓመት የአሜሪካ ብሔራዊ ሊግ አሸናፊ ይሆናል በሚል ተስፋ ከተፎካካሪው ቡድን በመጠኑ የላቀ ግምት ተሰጥቶት ነበር። ይሁንና ኒው ኦርሌየንስ ከተማ ሲዛርስ ሱፐርደም ውስጥ በተካሄደው ጨዋታ የፊላደልፊያ ኤግልስ ተጫዎቾች 34 ነጥቦችን እስካስቆጠሩበት ሦስተኛው የጨዋታው ምዕራፍ ድረስ የካንሳስ ቺፍስ ተጫዎቾች አንድም ነጥብ እንዳያስቆጥሩ ማድረግ ችለዋል። የፊላደልፊያ ኤግልስ አጥቂ መስመር ተጨዋች ጄለን ኸርትስ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተሰይሟል። ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጨዋታውን በአካል ተገኝተው የተመለከቱ ሲኾን ፣ በሥልጣን ዘመኑ «ሱፐር ቦል» ጨዋታን በስፍራው ተገኝቶ የተመለከተ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነዋል። ከጨዋታው በፊት ፕሬዝደንቱ ባሰራጩት የፕሬስ መግለጫ ላይ «እግር ኳስ የአሜሪካ እጅግ ተወዳጅ ስፖርት ነው። ለዚህም መልካም ምክንያቶች አሉ። የብሔራዊ አንድነት ስሜትን ያጎለብታል፣ ቤተሰቦችን፣ ጓደኞችን እና ደጋፊዎችን አንድ ላይ በማሰባሰብ ማኅበረሰቦችን ያጠናክራል» ብለዋል። «ይህ ዓመታዊ ልማድ ልዩነቶቻችንን የሚሻገር እና ወታደራዊ አገልግሎት ጓዶቻችን፣ ሕግ አስከባሪ መኮንኖች እና ቅድሚያ ምላሽ ሰጪዎች በጀግንነት የሚጠብቁትን የቤተሰብ፣ የእምነት እና የነጻነት የጋራ አርበኛ እሴቶቻችንን ያሳያል» ሲሉም አክለዋል። «ሱፐር ቦል» በሚል የሚጠራው የአሜሪካ እግር ኳስ ሊግ የውድድር ዘመን የፍጻሜ ምሽት ከ120 ሚሊየን ሰዎች እንደተመለከቱት የተገመተ ሲሆን ፣ በዚህ ጨዋታ ወቅት የ30 ሴኮንድ ርዝመት ያለው ማስታወቂያ ለማስነገር የሚከፈለው 8 ሚሊየን ዶላር በክብረ ወሰንነት ተመዝግቧል። ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት፣ በአውሮፓዊያኑ አዲስ ዓመት ኒው ኦርሊንስ በሚገኘው በርበን ጎዳና ላይ በተፈጸመ የሽብር ጥቃት፣ በከባድ መኪና ተዳምጠው ለተገደሉት እና ለቆሰሉ ዜጎች እንዲሁም የመጀመሪያ ምላሽ ሰጪዎች የመታሰቢያ ሥነ ስርዐት ተከናውኗል።
በሊቢያ ደቡብ ምሥራቅ ኩፍራ በተባለ አውራጃ የ28 ፍለሰተኞች አስከሬን በአንድ ሥፍራ ተቀብሮ መገኘቱን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። ሥፍራው ፍልሰተኞቹ ታግተው ሰቆቃ ሲፈጸምባቸው የነበረ መሆኑም ተመልክቷል። ፍልሰተኞቹ ከሰሃራ በታች ካሉ ሃገራት የሄዱ እንደኾነም ታውቋል። የሃገሪቱ የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቢሮ እንዳስታወቀው የመቃብር ሥፍራው የተገኘው የሕገ ወጥ ዝውውር ሰለባ የሆኑ ፍልሰተኞች ታግተው ሰቆቃ የሚፈጸምባቸው ሥፍራዎች ላይ ባደረጉት አሰሳ ነው። ከሰሃራ በታች ካሉ ሃገራት የሄዱና ታግተው ሰቆቃ ሲፈጸምባቸው የነበሩ ሰባ ስድስት ፍልሰተኞችን ነጻ ማውጣታቸውንም ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። አንድ ሊቢያዊና ሁለት የሌሎች ሃገራት ዜጎች መያዛቸውም ተመልክቷል። የሃገሪቱ የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ካወጣው መግለጫ ጋራ የተያያዘው ፎቶግራፍ፣ ነጻ የውጡት ፍልሰተኞች ገርጥተው፣ በፊታቸውና በሌሎችም የሰውነት ክፍሎቻቸው ላይ ጠባሳ እንዳለባቸው አሳይቷል። በእ.አ.አ 2011 በሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ሀገራት ደጋፊነት በተነሳው አመጽ፣ የረጅም ጊዜ መሪው ሞአመር ጋዳፊ ከሥልጣን ከተወገዱ ወዲህ ሊቢያ ከሁከት አልተለየችም።
ዩናይትድ ስቴትስ አብዛኛው የውጭ ርዳታ ለሦስት ወራት እንዲቋረጥ ያደረገችውን ውሳኔ ተከትሎ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ኤች አይ ቪ በደማቸው ያሉ ሰዎችን የሚረዱ ድርጅቶች ምን እንደሚያደርጉ ግራ ተጋብተዋል። የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር «ነፍስ አድን» የርዳታ ሥራዎች እንደሚቀጥሉ አስታውቋል። ይሁን እንጂ ቀደም ብለው ሥራቸውን ያቆሙ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በመቀጠል ምን ማድረግ እንዳለባቸው በግልጽ እንደማያውቁ ይናገራሉ። በዓመታት የተመዘገቡ ክንዋኔዎች ሊቀለበሱ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳላቸውም ይገልጻሉ። ኬት ባርትሌት ከጆሀንስበርግ ያጠናቀረችው ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ ውድመት የደረሰበት የጋዛ ክልል የሚተዳደርበትን አስመልክቶ ያቀረቡትን ሐሳብ ተከትሎ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ፍልስጤማውያን ከጋዛ ሰርጥ እንዲወጡ የሚያስችል እቅድ እንዲያወጣ ሰራዊቱን አዟል። የመከላከያ ሚንስቴር እስራኤል ካትስ ትላንት ሃሙስ ሲናገሩ፡ «የእስራኤል መከላከያ ኃይሎች የጋዛ ነዋሪዎች በፈቃዳቸው አካባቢውን ለቀው መሄድ የሚያስችላቸው እቅድ እንዲያዘጋጅ መመሪያ ሰጥቻለሁ» ብለዋል። ካትዝ እቅዱ «የመውጫ መንገድ እና የየብስ ማቋረጫ፤ እንዲሁም በባህር እና በአየር ለመጓጓዝ የሚያስችሉ አማራጮች ዝግጅት ያካትታል» ብለዋል። የመከላከያ ሚንስትሩ አክለውም፤ የጋዛ ነዋሪዎች በጦርነቱ ወቅት በሃማስ ታጣቂዎች ላይ በተነጣጠሩት የእስራኤል የምድር ጦር እና የአየር ድብደባዎች የተጎዳውን አካባቢ ለቀው እንዲወጡ ትረምፕ የያዙት “ቆራጥ እቅድ” ያሉትን በደስታ መቀበላቸውን ተናግረዋል። ትረምፕ በበኩላቸው ትላንት ሃሙስ በሰጡት አስተያየት እስራኤል ከሃማስ ጋር ያካሄደችው ጦርነት ካበቃ በኋላ የጋዛ ሰርጥን ለዩናይትድ ስቴትስ አሳልፋ መስጠት አለባት፤ ምንም አይነት የአሜሪካ ወታደር በዚያ ማሰማራትም አያስፈልግም ብለዋል። የሜዲትራኒያንን ባህር የሚያዋስነው አካባቢ ያለውን ጠባቡን የጋዛ ሰርጥ ዩናይትድ ስቴትስ በባለቤትነት እንድታስተዳድረው ያላቸውን ፍላጎት አስመልክቶ ‘ትሩዝ ሶሻል’ በተባለው የማሕበራዊ ግንኙነት መድረካቸው ላይ ያሰፈሩት ትረምፕ፤ በእርሳቸውም እቅድ መሠረት ቁጥራቸው ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ፍልስጤማውያን “አዳዲስ እና ዘመናዊ ቤቶች ባሉባቸው ለደህንነታቸው አስተማማኝ በሆኑ እና ይበልጥም በተዋቡ፣ በክልሉ በሚገኙ አካባቢዎች ውስጥ ገና ድሮ እንዲሰፍሩ የሚያስችል ነው” ብለዋል። ትረምፕ የሚሉት ሥፍራ እዚያው ጋዛ ውስጥ ይሁን እስካሁን ሃሳቡን ባልተቀበሉ ሆነ ሌሎች ሃገራት ዝርዝር አልሰጡም። «በእርግጥ ደስተኛ የመሆን፣ ደህንነታቸው የመረረጋጋጥ እና ነጻ የመሆን እድል ይኖራቸዋል» ሲሉ ጽፈዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሃማስ በትላንትናው እለት ሁሉም ፍልስጤማውያን አንጃዎች ትረምፕ ጋዛን ለመቆጣጠር ያቀረቡትን ሃሳብ በመቃወም ተባብረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርቧል። “ችግሩን ይበልጥ አያባብሱ” - ጉቴሬዥ ‘ችግሩን አናባብስ’ ሲሉ ያሳሰቡትን የመንግሥታቱን ድርጅት ዋና ጸሐፊ ጨምሮ፣ የትረምፕ የጋዛ ውጥን ከዓለም ዙሪያ መጠነ ሠፊ ነቀፌታ ገጥሞታል። «መፍትሄ ፍለጋ ፍልስጤማውያንን ከጋዛ በማውጣት ችግሩን ይበልጥ ማባባስ የለብንም» ያሉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶንዮ ጉቴሬሽ «ለመሰረታዊው ዓለም አቀፍ ሕጎች ከበሬታ መቆም ያስፈልጋል። ከማንኛውም አይነት የዘር ማጽዳት ድርጊትም መራቅ አስፈላጊ ነው» ብለዋል። አንድን ሕዝብ ከሚኖርበት አካባቢ በኃይል ወደ ሌላ ሥፍራ ማዛወር በዓለም አቀፍ ሕግ በጥብቅ የተከለከለ እና ከዘር ማጽዳት ሊቆጠር የሚችል ድርጊት ነው። የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ዋልተር ሽታይንማየርም ከትላንት በስቲያ ረቡዕ በሰጡት አስተያየት፤ የትራምፕ ዕቅዶች “በአንዳንድ ወገኖች ላይ ጥልቅ ጭንቀት እና አልፎ ተርፎም የመሸበር ስሜት ጭምር ሊቀሰቅሱ የሚችሉ” እናም “በአለም አቀፍ ኅግ ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው” ብለዋል። 22 አባላት ያሉት የአረብ ሊግ በበኩሉ የትራምፕ እቅድ «አለመረጋጋት ሊያስከትል የሚችል» እና ‘የፍልስጤምን ሀገር የመሆን እድልም የማያቃና” ብሎታል። የብሪታንያው ጠቅላይ ሚንስትር ኪር ስታርመርም በተመሳሳይ፤ ፍልስጤማውያን “ወደ ቤታቸው መመለስ ይችሉ ዘንድ መፈቀድ አለበት” ብለዋል። ቀያቸውን መልሰው እንዲገነቡ ሊፈቀድላቸው፤ እኛም በመልሶ ግንባታው እና ‘የሁለት ሃገር መፍትሔ በሚባለው ዕቅድ አብረናቸው ልሆን ይገባል’ ብለዋል። ትረምፕ የጋዛ ባለቤት ስለመሆን የሰነዘሩትን ይህን ሃሳብ ተከትሎም አውስትራሊያ፣ ቻይና፣ ጀርመን፣ አየርላንድ፣ ሩሲያ፣ ሳውዲ አረቢያ እና ስፔን፤ ሁለቱ አገሮች እስራኤል እና ፍልስጤም እንደ ሃገር ጎን ለጎን በሰላም የሚኖሩበትን መንገድ ለመፍጠር የታለመውን ‘የሁለት ሀገራት መፍትሄ’ የተባለ እቅድ መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል። የፍልስጤማውያኑ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስም ‘የመንግስታቱ ድርጅት የፍልስጤምን ህዝብ እና የማይገሰሱ መብቶቹን እንዲያስጠብቅ’ የሚል ጥሪ አሰምተዋል። ትራምፕ ሊያደርጉ ያቀዱት “አለም አቀፍ ህግን በእጅጉ የሚጥስ ነው” ሲሉም ኮንነዋል።
የጅቡቲ መንግሥት በአፋር ክልል ሲያሩ ቀበሌ ነዋሪዎች ላይ በድሮን አድርሶታል ያለውን ጥቃት በጥብቅ እንደሚያወግዙ በአፋር ክልል የሚገኙ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አስታወቁ፡፡ የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር እና የአፋር ለዴሞክራሲ እና ፍትሕ ፓርቲ በአወጡት መግለጫ፣ «ድርጊቱ ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ያደረገ እንዲሁም የሀገር ሉአላዊነትን የተዳፈረ ነው» ሲሉ ወንጅለውታል፡፡ በጥቃቱ ስምንት ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን ዘጠኝ የሚኾኑት ደግሞ ከባድና ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው መግለጫውን ካወጡት ተፎካካሪ ፓርቲዎች አንደኛው ለአሜሪካ ድምጽ አስታውቋል። በሆስፒታሉ ውስጥ በድሮን ጥቃቱ ጉዳት ደርሶባቸው ህክምና በማግኘት ላይ መሆናቸውን የነገሩን የሲያሩ ቀበሌ ነዋሪዋ ወ/ሮ መሬም መሐመድ ጥቃቱ በድንገት መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡ በጥቃቱ የወ/ሮ መሬም እህትን ጨምሮ ሌሎችም መገደላቸውን የተጎጅዋ ቤተሰብ እንደሆኑ የገለጹልን አብደላ መሐመድ ጠቁመዋል፡፡ በአፋር ክልል የሚንቀሳቀሱት የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር እና የአፋር ለዴሞክራሲ እና ፍትሕ ፓርቲ ትናንት ጥር 27 ቀን 2017 ዓ.ም በአወጡት የጋራ መግለጫ የጅቡቲ መንግሥት በአፋር ክልል ኤሊ ደአር ወረዳ ሲያሩ በተባለው ቀበሌ ላይ ፈጽሞታል ያሉትን የድሮን ጥቃት አውግዘዋል፡፡ በአፋር ክልል የሚገኘው የዱብቲ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሁሴን አደን በጥቃቱ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል የመጡና ህክምና በማግኘት ላይ የሚገኙ መኖራቸውን አረጋግጠዋል፡፡ የጅቡቲ የጸጥታ ኃይሎች በበኩላቸው “አሸባሪዎች” ብለው በገለጹት አማጺ ቡድን ላይ በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ ባደረጉት የድሮን ድብደባ ስምንት የቡድኑ አባላትን እና ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቀ ሲቪሎችን መግደላቸውን ባለሥልጣናቱ እሑድ ዕለት አስታውቀዋል። አዶራታ በተባለና ከኢትዮጵያ ድንበር ስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ስፍራ የድሮን ጥቃቱ እንደተፈጸመ የጅቡቲ የመከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ አመልክቷል። “ስምንት አሸባሪዎች ተገድለዋል” ያለው መግለጫ፣ “ነገር ግን የሃገሪቱ ሲቪል ዜጎችም ሕይወታቸውን አጥተዋል” ብሏል።
ከሰባዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ለበርካታ ዕውቅ ድምጻውያን ሥራዎቹን ሰጥቷል። ከኩኩ ሰብስቤ እስከ አስቴር አወቅ እና ጥላሁን ገሰሰ ቁጥራቸው የበዛ ድምጻውያን ድንቅ የሙዚቃ ድርሰቶቹን ተጫውተዋል። ታዋቂው የዘፈን ግጥሞች ደራሲ እና ፕሮዲዩሰር ያየህይራድ አላምረው። ሕይወት እና ሥራውን ለመዘከር የተሰናዳውን ቅንብር ከዚህ ይከታተሉ።
በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት የዲሞክራቲክ ፓርቲ አመራር አባላት፣ የትረምፕ አስተዳደር የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ፕሮግራም መሥሪያ ቤትን (ዩኤስኤአይዲ) በመሳሰሉ የመንግስት መሥሪያ ቤቶች ይዞታ እና አሰራር ላይ እያደረገ ያለውን ለውጥ፣ በመንግሥቱ በጀት ዕቅድ ዙሪያ ከፕሬዝዳንቱ ጋር በሚደረጉ ድርድሮች ወቅት እንደሚጠቀሙበት በመግለጽ አስጠነቀቁ። የአሜሪካ ድምጿ የምክር ቤት ጉዳዮች ዘጋቢ ካትሪን ጂፕሰን ያደረሰችው ዘገባ ነው።
ኢትዮጵያ ከተጋረጠባት የሰላም እጦት እንድትወጣ የሃይማኖት አባቶች የፀሎት እና የሰላም ጥሪ አቅርበዋል። የሃይማኖት አባቶቹ፣ ዛሬ በአዲስ አበባ በተካሔደ ዝግጅት ላይ ለተፋላሚ ሃይሎች የሰላም ጥሪ ያቀረቡ ሲኾን፣ የፀሎት አዋጅም አውጀዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሲቪል እና የሙያ ማኅበራት ኮንግረስ አዘጋጅነት ሐሙስ ጥር 29 ቀን በአድዋ ድል መታሰቢያ አዳራሽ በተካሔደ አገራዊ የፀሎት እና የሰላም ጥሪ ዝግጅት ላይ የተገኙ የልዩ ልዩ ቤተ እምነቶች አባቶች ፀሎት ካደረጉ በኋላ ለምዕመናን እና ለተፋላሚ ወገኖች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለማስቆም አሁንም የተቀናጀ ስራ እንደሚያስፈልግ የገለፀው የኢትዮጵያ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒሰቴር፣ ከተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እና ከሌሎች አጋሮች ጋር በመተባበር ያዘጋጃቸውን ሰነዶች ዛሬ ይፋ አድርጓል ። ጥር 29 ቀን 2017 ዓ/ም ይፋ የተደረጉት ብሔራዊ የዕቅድ ሰነዶች ችግሩን እ.አ. አ. እሰከ 2030 ለመፍታት ያስችላሉ የተባሉ ናቸው። የተፈጥሮ አደጋዎች እና ግጭቶች ታዳጊ ሴቶችን ለተጠቀሱት ችግሮች እያጋለጡ መሆኑን የተናገሩት፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ምኒሰትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ «ትልቁ ነገር ሰላም ላይ መስራት ነው» ብለዋል። ድርጊቶቹ ሰብዓዊ ቀውስ በሌለበት ሁኔታ ውስጥም እየተፈጸሙ ናቸው ያሉት በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተጠባባቂ ተወካይ ማሪኮ ካጎሺማ፣ ሰነዶቹ የግንዛቤ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያግዙ ጠቅሰዋል።
ዛሬ በዓመታዊው ‘ብሔራዊ የፀሎትና የቁርስ ሥነ ሥርዐት’ ላይ የተገኙት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ፣ ከተፈጸመባቸው ሁለት የግድያ ሙከራዎች በኋላ ከሃይማኖት ጋራ ያላቸው ግንኙነት እንደተቀየረ አስታውቀዋል። አሜሪካዊያን “ፈጣሪን መልሠው በሕይወታቸው ውስጥ ያኑሩ” ሲሉ ጥሪ አድርገዋል ትረምፕ። በካፒቶል የሚካሄደውና የሰባ ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠረው ዓመታዊ የፀሎትና የቁርስ ሥነ ሥርዐት የሁለቱም ፓርቲዎች የምክር ቤት ዓባላት የሚሳተፉበት ሃይማኖታዊ ሥነ ስርዓት ነው። “ከሃይማኖት ውጪ፣ ከእምነት ውጪ ደስተኛ መሆን እንደማይቻል አምናለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል ትረምፕ፡፡ ከግድያ ሙከራዎቹ በኋላ ወደ እግዚያብሄር ይበልጥ እንደቀረቡ ያመለከቱት ትረምፕ፣ ጆሯቸውን በጨረፈው ሙከራ ጸጉራቸው እንዳልተነካ ለዚህም ምስጋና ማቅረባቸውን ሲናገሩ ታዳሚውን ፈገግ አሰኝተዋል። ትረምፕና አስተዳደራቸው ከሃይማኖት መሪዎች ጋራ ግጭት ውስጥ ሲገቡ ከዚህ በፊት ተስተውሏል ያለው የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ፣ በባዕለ ሲመታቸው ቀን በተደረገ የቤተ ክርስቲያን ሥነ ሥርዓት ሰባኪው ማሪያን ቡደስ ለስደተኞችና ለተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ርህራሄ እንዲያሳዩ መጠየቃቸውን ትረምፕ ተቃውመው እንደነበር አመልክቷል። የካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆኑት ምክትል ፕሬዝደንት ጄ ዲ ቫንስ ደግሞ የስደተኞችን ጉዳይ በተመለከተ ተመሳሳይ እምነት ካላቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋራ ሳይስማሙ ቀርተዋል።
አሜሪካ የውጪ ርዳታዋን ማቁረጧ በኢትዮጵያ በርካታ የልማት ሥራዎችን፣ በተለይም ደግሞ ከኤችአይቪ ጋራ የሚኖሩ ሰዎችን ለመርዳት የሚደረገውን ጥረት እንደሚጎዳ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤች አይ ቪ ኤድስ ፕሮግራም (ዩኤሴይድስ) አስታውቋል። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከኤችአይቪ ጋራ የሚኖሩ የ503 ሺሕ ሰዎች በ1ሺሕ 400 ጤና ጣቢያዎች በኩል አንቲሪትሮቫይራል የተሰኘው መድኃኒት እንደሚሰጣቸው የተመዱ የኤድስ ፕሮግራም አስታውቃል። በክልሎች የሚገኙ የጤና ባለሥልጣናት በአሜሪካው ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤሴይድ) እና በአሜሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) የገንዘብ ድጋፍ የሚሠሩ የጤና ሠራተኞችን እንዲያሰናብቱ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መመሪያ እንደደረሳቸው ለቪኦኤ አስታውቀዋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከቪኦኤ አስተያየት እንዲሰጥ ተጠይቆ መልስ አልሰጠም። ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ለውጪ ሃገራት የሚሰጥ ርዳት እንዲቋረጥ ማዘዛቸውን ተከትሎ፣ የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ኤችአይቪን ጨምሮ ሌሎችም ሕይወት አድን ፕሮግራሞችን አሜሪካ መደገፍ እንደሚቀጥል አስታውቆ ነበር። የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ምኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ርዳታ እንደሚቀጥል ቀደም ብለው አስታውቀው የነበረ ሲሆን፣ ቆየት ብለው ደግሞ ደግሞ ሕይወት አድን መድሃኒቶችና የሕክምና አገልግሎቶች እንዲሁም የምግብና የመጠለያ ርዳታዎች እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለውጪ ሀገራት የሚሰጡ የገንዘብ ድጋፎችን ለ90 ቀናት ማገዳቸውን ተከትሎ፤ የናይጄሪያ ባለሥልጣናት የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ /ዩ ኤስ ኤ አይ ዲ/ ድጋፍ ይንቀሳቀሱ ለነበሩ የጤና ፕሮግራሞች የሽግግር እና ዘላቂ እቅድ የሚያዘጋጅ ኮሚቴ አቋቁመዋል። የተለያዩ ሚኒስትሮች የተካተቱበት ኮሚቴም ወሳኝ የኾኑ የጤና ፕሮግራሞች አዲስ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል። ቲሞቲ ኦቢየዙ በዚህ ዙሪያ ከአቡጃ ያጠናቀረውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
በስዊድን አንድ ግለሰብ በጎልማሶች ትምህርት ቤት ውስጥ በከፈተው ተኩስ ግለሰቡን ጨምሮ 11 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ ሌሎች አምስት ሰዎች ደግሞ ክፉኛ ተጎድተዋል ተብሏል። ፖሊስ ግለሰቡ ድርጊቱን ለብቻው መፈጸሙን ገልጾ፣ የትምህርት ቤቱ ተማሪ ይሆን እንደሁ ወይም ምን እንዳነሳሳው አላሳወቅም። የጅምላ ግድያው በስዊድን ታሪክ የከፋው እንደሆነ ተነግሯል። ግድያው የተፈጸመው ከስቶክሆልም ወጣ ብሎ በሚገኝና ለጎልማሶች የአንደኛና የሁለተኛ ደርጃ ትምህርት እንዲሁም ለስደተኞችና ለሌሎችም የቋንቋና የሙያ ትምህርት በሚስጥበት ቅጥር ግቢ ውስጥ ነው። ስዊድን ውስጥ በትምህርት ተቋማት በመሣሪያ የሚፈጸም ግድያ እምብዛም አይስተዋልም።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በጦርነት የዳሸቀችውን ጋዛን በባለቤትነት እንድትረከብ እንደሚፈልጉ ተናገሩ። ይህ ሐሳባቸው ታዲያ፤ የጋዛን ነዋሪዎች፣ ዮርዳኖስ እና ግብጽን ጨምሮ በሌሎች ሀገሮች እንዲሰፍሩ ለማድረግ እቅድ አንዳላቸው ከአሁን ቀደም ከተናገሩትም ገፋ ያለ ነው፡፡ ፕሬዝደንት ትረምፕ ይህንን ሐሳባቸውን የገለጹት ትላንት ማክሰኞ ማታ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁን ተቀብለው ባስተናገዱበት ወቅት ነው፡፡ የአሜሪካ ድምጽ የኋይት ሐውስ ዋና ዘጋቢ ፓትሲ ዊዳኩስዋራ ያጠናቀረችውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ አሜሪካ ጋዛን በባለቤትነት መቆጣጠር እንደምትሻ አስታውቀዋል። ከዚህ ቀደም ፕሬዝደንቱ ጦርነት ባፈራረሳት ሰርጥ ውስጥ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ወደ ጎረቤት ጆርዳን እና ግብጽ ሄደው እንዲሰፍሩ ሐሳብ አቅርበው ነበር። የፍልስጤም ራስ ገዝ፣ ግብጽ፣ ሳዑዲ አረቢያና ሌሎችም የአሜሪካ ሸሪኮችም ሆነ ወዳጅ ያልሆኑ ሃገራት የትረምፕን ሃሳብ ተቃውመዋል። “ያነጋገርኳቸው ሰዎች በሙሉ አሜሪካ ጋዛን በባለቤትነት ትያዝ የሚለውን ሐሳብ ወደውታል። ድንቅ የሆነውን ሥፍራ በማልማትም በሺሕ የሚቆጠር የሥራ ዕድል ይፈጠራል” ብለዋል ትረምፕ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ምኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጋራ በመሆን ዋሽንግተን ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ። ኔታንያሁ በበኩላቸው ዋናው ግባቸው ሐማስ በእስራኤል ላይ ስጋት ማረጋገጥ ቢሆንም፣ “ትረምፕ ደግሞ ግቡን ከፍ አድርገውታል” ብለዋል። “ታሪክን የሚቀይር ይመስለኛል፣ ይህን መንገድ መከተል ጠቃሚ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል ኔታንያሁ። በ15 ወራት ጦርነት የፈረሰውን ሥፍራ ለመቆጣጠር ያላቸውን ዕቅድ ዝርዝር ትረምፕ አላሳወቁም። የአሜሪካ ወታደሮችን መላክም ከአማራጮች ዝርዝር ውስጥ አለመውጣቱን ትረምፕ አስታውቀዋል። “አስፈላጊ ከሆነ እናደርገዋለን። ያንን ሥፍራ ይዘን እናለማዋለን” ብለዋል ትረምፕ፡፡
አሜሪካ ለ90 ቀናት የውጪ ርዳታ እንደሚቋረጥ ብታስታወቅም፣ ‘የፕሬዝደንቱ የኤድስ አስቸኳይ ጊዜ ርዳታ’ ወይም ‘ፔፕፋር’ በሚባል የሚታወቀው ፕሮግራም እንደማይቋረጥ ታውቋል። ፔፕፋር በዓለም መሪ የሆነ በኤድስ ላይ የሚሠራ ፕሮግራም ሲሆን፣ ሕይወት አድን ፕሮግራሞች እንዲቀጥሉ በመወሰኑ የ90 ቀናት እገዳው እንደማይመለከተው ታውቋል። ፕሬዝደንት ትረምፕ ሥልጣኑን ደግመው በተረከቡ በሰዓታት ውስጥ ነበር “አሜሪካ ትቅደም” ከሚለው የውጪ ፖሊሲያቸው ጋራ የሚጣጣሙ መሆናቸው እስከሚጣራ ለውጪ ሃገራት የሚሰጡ ዕርዳታዎች ለ90 ቀናት እንዲቆሙ ያዘዙት፡፡ የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ምኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ እንደሚቀጥል ቀደም ብለው አስታውቀው የነበረ ሲሆን፣ ቆየት ብለው ደግሞ ደግሞ ሕይወት አድን መድሃኒቶችና የሕክምና አገልግሎቶች እንዲሁም የምግብና የመጠለያ ዕርዳታዎች እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል። በዓለም በኤች አይ ቪ ከተያዙት ከሁለት ሶስተኛ በላይ ወይም ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የቫይረሱ ተጠቂዎች በፔፕፋር ፕሮግራም በቀጥታ የሚረዱ መሆኑም ታውቋል።
የአሜሪካ የፖስታ አገልግሎት ከቻይና እና ከሆንግ ኮንግ የሚላኩ ጥቅሎችን ለጊዜው መቀበል ማቆሙን ትላንት ማክሰኞ አስታውቆ የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ደግሞ ወደ ደንበኞች የሚላኩ ጥቅሎች መቋረጥ እንዳይከሰት ከጉምሩክና ድንበር ባለሥልጣን ጋራ አዲሱን ታሪፍ ተግባራዊ የሚያደርግበትን መንገድ መላ እንደሚዘይድ አስታውቋል። የፖስታ ቤቱ የማክሰኞ እርምጃ የመጣው እንደ ቴሙ እና ሺኢን የመሰሉ የኢንተርኔት መገበያያዎች አነስተኛ ጥቅሎችን ከቀረጥ ነጻ የሚያስገቡበትን ደንብ ፕሬዝደንት ትረምፕ መሻራቸውን ተከትሎ ነው። ፕሬዝደንቱ በቻይና ላይ የጣሉት ተጨማሪ 10 በመቶ ታሪፍ ከትላንት ማክሰኞ ጀምሮ ተግባራዊ ሆኗል። ቀደም ሲል የነበረው ደንብ አሜሪካውያን ከ$800 ዶላር በታች ከውጪ ለሚገዙት ዕቃ ታሪፍ እንዲከፍሉ አያስገድድም። ፕሬዝደንት ትረምፕ ቻይና 10 በመቶ ተጨማሪ ታሪፍ እንድትከፍል እንዲሁም አነስተኛ ጥቅሎችም ታሪፍ እንዲጣልባቸው ያዘዙት፣ የቻይና ሸቀጥ አቅራቢዎች አጋጣሚውን በመጠቀም ፈንትነል የተሰኘውን አደገኛ መድሃኒት መቀመሚያ ኬሚካሎች በሌሎች ሸቀጦች ስም ወደ አሜሪካ ይልካሉ በሚል ነው። በተጨማሪም ቤጂንግ ወደ አሜሪካ የሚላከውን የፈንትነልን ዝውውር አትቆጣጠርም በሚልም ነው።
የትረምፕ አስተዳደር በመላው ዓለም የሚገኙ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ድርጅት (ዩ ኤስ ኤ አይ ዲ) ሠራተኞች ሥራ እንዲያቆሙ አዟል። ላለፉት ስድሳ ዓመታት በመላው ዓለም ረሃብን በማስወገድ እና ለትምህርት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ በመስጠት የአሜሪካንን ደኅንነት ሲያስጠብቅ የከረመው ድርጅት የመዘጋት ዕጣ ገጥሞታል። የትረምፕ አስተዳደር ለአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ድርጅት ሠራተኞች በኢሜይል በላከውና እና በድርጅቱ ድህረ ገጽ ላይ ባሠፈረው መልዕክት ነው ውሳኔውን ያስታወቀው። የትረምፕ አስተዳደር ባለሥልጣኖች እና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ቁጥር እና ሠራተኞችን ለመቀነስ የተቋቋመውንና ‘ዶጅ’ በመባል የሚታወቀውን ቡድን የሚመሩት ኢላን መስክ የዕርዳታ ድርጅቱ ለውጪ ሃገራት የሚያውለውን ገንዘብ እንደ ብክነት እንደሚቆጥሩት ተመልክቷል። ትዕዛዙ ከዓርብ እኩለ ሌሊት በፊት ተፈጻሚ የሚሆን ሲሆን ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ከሚፈለጉ ሠራተኞች ውጪ በመላው ዓለም የሚገኙ ሌሎች የድርጅቱ ሠራተኞች ወደ አሜሪካ ለመመለስ 30 ቀናት ተሰጥቷቸዋል። ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ከሚፈለጉ ኮንትራክተሮች ውጪ ሥራቸውን እንዲያቆሙ እንደሚነገራቸውም ታውቋል። የተቀረው የድርጅቱ ሥራም በአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር እንዲጠቃለል እንደሚደረግ ታውቋል። ትረምፕ ለውጪ የሚሰጥ ርዳታ እንዲቆም ማድርጋቸውን ተከትሎ፣ በመላው ዓለም የሚገኙ የድርጅቱ የሀገር ውስጥ ተቀጣሪዎች ተባረው ፕሮግራሞቹም እንዲቆሙ ተደርጓል።
የፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ትሬድ ማህበራዊ ሚዲያዎችን የሚያስተዳድረው ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሜታ፤ በማህበራዊ የትስስር ገጾቹ ላይ የሚተላለፉ ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመቀነስ ከሶስተኛ ወገን ተቋማት ጋር በመተባበር ያካሂድ የነበረውን የመረጃ ማጣራት ስራ ማቋረጡ ሀሰተኛ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች በስፋት እንዲሰራጭ ያደርጋል ሲሉ ተቺዎች ተናግረውል። በአሁኑ ወቅት ውሳኔው በአሜሪካ ውስጥ ብቻ ተግባራዊ እንደሚደረግ ለአሜሪካ ድምፅ የገለጸው ፌስቡክ በበኩሉ፣ ከአሜሪካ ውጪ ወዳሉ ሀገራት ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ተቋሙ የሚኖሩበትን ግዴታዎች በጥንቃቄ እንደሚያጠና ገልጿል። (ዝርዝሩን ከተያያዘው የቪዲዮ ዘገባ ያገኛሉ)
አሜሪካ በካናዳ እና ሜክሲኮ ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ ለመጫን መወሰኗ እና ሁለቱ ሃገራትም በምላሹ ተመሳሳይ ርምጃ እንደሚወስዱ ማስታወቃቸው፣ እንዲሁም ቀድሞውንም በቻይና ላይ ተጭኖ የነበረውን 10 በመቶ ታሪፍ ጨምሮ፣ በዓለም የንግድ ጦርነትና የኢኮኖሚ ቀውስ ይከሰታል የሚል ከፍተኛ ስጋት አሳድሮ ነበር። ፕሬዝደንት ትረምፕ አዲሱ ደንብ ተግባራዊ ከመሆኑ አንድ ቀን ቀደም ብሉ፣ ከካናዳ እና ከሜክሲኮ መሪዎች ጋራ መነጋገራቸውን ተከትሎ፣ ነገሮች ወደነበሩበት የተመለሱ መስለዋል። ትረምፕ ከመሪዎቹ ጋራ ከተነጋገሩ በኋላ ሁኔታዎችን ለማጤን ተጨማሪ 30 ቀናት እንደሚወስዱ አስታውቀዋል። ካናዳን በተመለከተ በሰሜኑ የአሜሪካ ድንበር ላይ ቁጥጥር ለማድረግ መስማማቷን፣ በአሜሪካ የበርካቶችን ሕይወት በመቅጠፍ ላይ ያለውና ፈንትነል የተሰኘው ሱስ አሲያዥ መድኃኒት በሕገ ወጥ መንገድ የሚገባበትን ሁኔታ ለማስቆም፣ ለዚህም 1.3 ቢሊዮን ዶላር በመመደብ እንድሚንቀሳቀሱ የካናዳው ጠቅላይ ምኒስትር ጀስቲን ትሩዶ መስማማታቸውን ትረምፕ አስታውቀዋል። በአዲስ ሄሎኮፕተሮች፣ ቲክኖሎጂ እና የሰው ኅይል በመታገዝና ከአሜሪካ ጋራ በመተባበር የፈንትነል ዝውውርን ለመግታት እንደሚሰሩም ተስማምተዋል። 10 ሺሕ የሚሆን የሰው ኃይል እንደምታሰማራና የፈንትነል ጉዳይ አማካሪ በመሾም ለ24 ሰዓታት ድንበሩን እንደምትቆጣጠር እንዲሁም የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎችንም በሽብርተኝነት እንደምትፈርጅ ካናዳ ተስማምታለች ተብሏል፡፡ በተመሳሳይም ከሜክሲኮ ፕሬዝደንት ክላውዲያ ሼይንቦም ጋራ በተደረገው ውይይት፣ 10ሺሕ ወታደሮችን በድንበር ላይ ለማሰማራት ፕሬዝደንቷ መስማማታቸውን እነዚህም ወታደሮች የፈንትለልና የሕገ ወጥ ፍልሰተኞችን ዝውውርን ለመቆጣጠር እንደሚሰሩ ትረምፖ አመልክተዋል። በውይይቶቹም በካናዳ እና ሜክሲኮ ላይ ሊጣል የነበረው 25 በመቶ ታሪፍ፣ እንዲሁም ሃገራቱ በአጸፋው በአሜሪካ ላይ ሊጥሉት የነበረው ተመሳሳይ የታሪፍ መጠን ለጊዜው ለሰላሳ ቀናት ያህል እንዲቆም ስምምነት ላይ ተደርሷል። በቻይና በኩል ያለው የንግድ ውዝግብና የታሪፍ ጭመራ ግን እንደቀጠለ ነው። ቻይና ለፕሬዝደንት ትረምፕ የታሪፍ እርምጃ አጸፋ ሰጥታለች፡፡ የህም ከአሜሪካ በሚገቡ በርካታ ሸቀጦች ላይ የሚጣል ሲሆን፣ በተለይም በተፈጥሮ ጋዝ ውጤቶች ላይ 15 በመቶ፣ በድፍድፍ ነዳጅ ላይ ደግሞ የ10 በመቶ ታሪፍ እንደምትጭን አስታውቃለች፡፡ አዲሱ የታሪፍ እርምጃም ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ቻይና አስታውቃለች። “የአሜሪካ የታሪፍ ጭማሪ ከዓለም ንግድ ድርጅት ደንቦችን የጣሰ እንደሆነ” ያስታወቀችው ቻይና “በአሜሪካ የሚይታዩ የኢኮኖሚ ችግሮችን ለፍታት የማይጠቅም” ብቻ ሳይሆን፣ በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚና የንግድ ትብብር የሚጎዳ እንደሆነ ገልጻለች፡፡ በተጨማሪም የአሜሪካንን የታሪፍ ጭማሪ በተመለከተ በዓለም የንግድ ድርጅት መድረክ ላይ እንደምትሞግት ቻይና አስታውቃለች፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በትግራይ ክልል የፖለቲካ ኃይሎች መካከል በቀጠለው የፖለቲካ ልዩነት ዙሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ አስተያየት ሰጡ። በዛሬው ዕለት በፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ "የትግራይ የፖለቲካ መሪዎች እና ልሂቃን የውስጥ ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ’ ሲሉ ጥሪ ያሰሙት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ፣ ከሌሎች ክልሎች ይሁን ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር የሚነሱ ማናቸውም ልዩነቶች የሃገሪቱ ሕገ መንግሥት በሚያዘው መሠረት ሊፈቱ ይገባል’ ብለዋል። የትግራዩ የፖለቲካ አለመግባባት በቅርቡ አንዳንድ የክልሉ የጦር አዛዦች ድጋፋቸውን ለሕወሐት ሊቀ መንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ከገለጹ በኋላ ከክልሉ ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ጋራ የገቡት ብርቱ የፖለቲካ ውዝግብ ተባብሶ መቀጠሉ ተዘግቧል። የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ የክልሉ ምክር ቤት ከተበተነ ከዓመታት በኋላ በትላንትናው ዕለት አማካሪ ምክር ቤት ተመስርቷል። የአማካሪው ምክር ቤት ፕሬዝዳንቱን ከመሰየም በመለስ የክልል ምክር ቤቱን ሥራ እንደሚሠራ ተገልጿል። እርምጃውን የተቃወሙት የሕወሐት መሪ አማካሪ ጉባኤውን ድርጅታቸውን ለመበተን የታለመ ሲሉ ተከራክረዋል። ዐቢይ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ የትግራይ ሕዝብ “የትላንት ቁስሉ ሳይጠግ፣ አሁንም በፍርሃት እና በተሸበረ ሥሜት እንዳለ ነው” ብለዋል።