በኢትዮጵያ እና በኬንያ የድንበር ላይ ግጭትን ተከትሎ ሰዎች መፈናቀላቸው ተገለጸ
newsare.net
በኢትዮጵያ እና በኬንያ ድንበር አካባቢ በተዋሳኞቹ የዳሰነች ወረዳ እና የቱርካና ወረዳ አርብቶ ዐደሮች መካከል የተከሠተውን ግጭት ተከትሎ፣ የዳሰነች ወረዳ አበኢትዮጵያ እና በኬንያ የድንበር ላይ ግጭትን ተከትሎ ሰዎች መፈናቀላቸው ተገለጸ
በኢትዮጵያ እና በኬንያ ድንበር አካባቢ በተዋሳኞቹ የዳሰነች ወረዳ እና የቱርካና ወረዳ አርብቶ ዐደሮች መካከል የተከሠተውን ግጭት ተከትሎ፣ የዳሰነች ወረዳ አርብቶ አደሮች ሲአስ ከሚባል መንደራቸው መፈናቀላቸውን፣ የወረዳው አስተዳደሪ አቶ ታደለ ሀቴ ለአሜሪካ ደምፅ በስልክ አስታውቀዋል። በደኅንነት ሰጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁን በዳሰነች ወረዳ የሲአስ ቀበሌ ነዋሪ፣ በስምንት ቀበሌዎች የሚኖሩ የዳሰነች ማኅበረሰብ ነዋሪዎች እንደተፈናቀሉና በአምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ደብረሞስ ቀበሌ እንደሸሹ፣ በስልክ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል። በግጭቱ የአጎታቸው እና የአክስታቸው ልጅ እንደተገደለባቸው ከዚኽ ቀደም የተናገሩት፣ አሰጪ ሎካሊባ የተባሉ ዐርብቶ አደር፣ እርሳቸውን ጨምሮ የቀበሌያቸው ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን አስረድተዋል። ግጭቱ ካለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ የካቲት 15 ቀን 2017 ዓ.ም. አንሥቶ፣ አንዱ ወገን የሌላውን የዓሣ ማሥገሪያ መረብ በመሰራረቅ መቀስቀሱን ያስታወሱት የዳሰነች ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ታደለ፣ ግጭቱ ሰኞ የካቲት 17 ቀን በመባባሱ ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል። የኬንያ ባለሥልጣናት «ድንበር ተሻጋሪ» ሲሉ በገለጹት ግጭት ከ20 በላይ ለሚደርሱ ኬንያውያን መጥፋታቸውን አስታውቀዋል። የዳሰነች ወረዳ አስተዳዳሪው ከኢትዮጵያ በኩል 13 ሰዎች መሞታቸውንና ሦስት ሰዎች መጎዳታቸውን ተናግረዋል። ተጎራባች የኾኑት አርብቶ ዐደሮቹ፣ ሁለቱ አገሮች የሚዋሰኑበትን ድንበር በሚያቋርጠው ቱርካና ሐይቅ ላይ በጀልባቸው ኾነው የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን የገለጹት የዳሰነች ወረዳ የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ብዙአየኹ ከበደ፣ በኬንያ በኩል ጠፍተዋል የተባሉት ሰዎች በሕይወት ስለመትረፋቸው የታወቀ ነገር እንደሌለ አመልክተዋል። በኢትዮጵያ በኩል ተገድለዋል ከተባሉት 13 አርብቶ ዐደሮች መካከልም፣ የአንድ ሰው አስከሬን ብቻ መገኘቱንና የሌሎቹን መሞት ያረጋገጡት፣ ከቤተሰቦቻቸው በተሰጣቸው መረጃ መሠረት እንደኾነ፣ ሓላፊው ተናግረዋል። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ሓላፊ አቶ ወገነ ብዙነህ፣ ከኹለቱም ወገን ዐርብቶ አደሮቹ መጥፋታቸው ከመገለፁ ውጪ አስክሬን ባለመገኘቱ በቁጥር መናገር እንደሚቸግር ተናገርዋል። ከባለሥልጣናቱ ውይይት በኋላ በተደረገ የሟቾች አስከሬን ፍለጋ፣ ሁለቱ መገኘታቸውን የገለጹት ሓላፊው፣ ከሁለቱም ማኅበረሰቦች በኩል የሰው ሕይወት መጥፋቱን አረጋግጠዋል። የኬንያ የደኅንነት ጉዳይ አዋቂ የኾኑት ሪቻርድ ቱታ፣ በናይሮቢ የአሜሪካ ድምፅ ዘይነብ ሰዒድ ጋራ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ በተፈጥሮ ሀብቶች አጠቃቀም የተነሣ ለሚከሠቱ ግጭቶች ከሥር መሠረታቸው የጋራ መፍትሔ መስጠት፣ እንዲሁም በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እንዲወርድ መሥራት ያስፈልጋል፤ ብለዋል። የደኅንነት ጉዳይ ባለሞያው፣ ሰሞነኛውን የድንበር ላይ ግጭት፣ «አልፎ አልፎ የሚከሠት» ሲሉ ቢገልጹትም፣ በቱርካና እና በዳሰነች ማኅበረሰቦች መካከል፣ ውሱን በኾነው የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ረገድ ያለው ፉክክር፣ ለግጭቱ እያደር ማገርሸት አደጋ እንደሚደቅን አልሸሸጉም፡፡ “አኹን ከኹሉም በላይ የሚያስፈልገው፣ ሁለቱ ተጎራባች ሀገራት የችግሩን ምንጭ ከሥር መሠረቱ መመልከት ይኖርባቸዋል፡፡ የሀብት ውሱንነት እስካለ ድረስ ግጭት ዳግመኛ አይቀሰቀስም እያልኹ አይደለም። በዋናነት ማከናወን የሚያስፈልገው፣ ክፍተቶቹ ምን እንደኾኑ መለየትና ከዚያም የግጭቱን የማገርሸት ዕድል ለመቀነስ የሚረዳ ዕቅድ መተግበር ነው፡፡” ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋራ በምትዋሰንበት ድንበር ላይ ከፍተኛ የጥበቃ ኀይል ማስፈሯን፣ አሶሺዬትድ ፕሬስ የአገሪቱን የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኪፕቹምባ ሙርኮመን ጠቅሶ ዘግቧል። የኬንያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኪፕቹምባ ሙርኮመን፣ የጠፉትን ሰዎች ለማግኘት ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋራ በመተባበር እየሠሩ መኾኑን ገልጸዋል። በኬንያ የቱርካና አውራጃ አስተዳዳሪ ዠርሚያ ሎሞሩካይ በበኩላቸው፣ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ ከኢትዮጵያ የመጡ ያሏቸው ዓሣ አሥጋሪዎች በኦሞ ወንዝ ላይ ከኬንያ የቱርካና ጎሣ አባላት ጋራ እሑድ ዕለት መጋጨታቸውን አውስተው፣ 15 ጀልባዎች ጠፍተዋል፤ ብለዋል። በሁለቱ ተጎራባች ሀገራት ድንበር አካባቢ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ፣ ኬንያ፣ ተጨማሪ የፖሊስ ተጠባባቂዎችን ቀጥራ የነበረ ሲኾን፣ የሀገር ውስጥ ሚኒስትሩ ሙርኮመን፣ ኬንያ ወደ ውስጥ የሚገቡ ሰዎች ሁሉ የሚፈተሹበትን የድንበር ኬላ አቋቋማለች፤ ብለዋል። የዳሰነች ወረዳ አስተዳደሪ አቶ ታደለ፣ ኬንያ ወታደሮቿን በተሽከርካሪዎች እና በሄሊኮፕተሮች እያጓጓዘች ወደ ድንበር ማስጠጋቷንም፣ አቶ ታደለ ገልጸዋል። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ሓላፊ አቶ ወገነ ብዙነህ፣ ከዳሰነች ወረዳ አርብቶ ዐደሮች እና በኬንያ ቱርካና ካውንቲ ባለሥልጣናት ጋራ መወያየታቸውን አስታውቀው፣ በዚኽም የችግሩን መነሻ ለይቶ ዘላቂ መፍትሔ በማፈላለግ፣ የሁለቱን አገሮች አርብቶ ዐደሮች ሰላማዊ ግንኙነት በማስቀጠልና ሰው የመግደል ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች በሕግ በሚጠየቁበት ኹኔታ ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን ዘርዝረዋል። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትም ያለው ኹኔታ ከባድ መኾኑን አልሸሸጉም፡፡ የኬንያ ባለሥልጣናት በድንበሩ ላይ የጸጥታ ጥበቃቸውን አጠናክረዋል፡፡ የጸጥታ ጉዳይ አዋቂው ሪቻርድ ቱታ ታዲያ፣ ለችግሩ መፍትሔ ለማምጣት ሁለቱ ሀገራት፥ የጋራ የሀብት አስተዳደር መርሐ ግብሮችን ሥራ ላይ እንዲያውሉ ይመክራሉ፡፡ ከነዚህም መካከል አንዱ የጋራ የዓሣ ማሥገሪያ ቀጣና ማካለል እንደኾነ ጠቁመዋል። “እነዚኽ የተፈጥሮ ሀብቶች፣ አብዛኞቹ የማኅበረሰቡ አባላት ለኑሯቸው የሚጠቀሙባቸው ናቸው፡፡ ሀብታቱ ደግሞ ድንበር ተሻጋሪ እንጂ በሀገራቱ ወሰን ውስጥ ብቻ ተካለው የሚገኙ አይደሉም፡፡ ስለዚኽም የውኃ ሀብት፣ ለም የግጦሽ መሬት የመሳሰሉትን የተለያዩ ሀገራትን ድንበር የሚሻገሩ ተፈጥሯዊ ሀብቶችን በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል ዘዴን መቀየስ ያስፈልጋል። ምክንያቱም በድንበሮቹ አዋሳኝ አካባቢዎች ባሉት ማኅበረሰቦች መካከል እዚኽም እዚያም የሚከሠቱት አብዛኞቹ ግጭቶች መንሥኤአቸው ከጋራ ሀብቶች አጠቃቀም ጋራ የተያያዙ ናቸው፡፡” የኬንያ ባለሥልጣናት፣ ልዩ ስሙ ቶዶጋኒው በተባለው ስፍራ ለተከሠተው ሰሞነኛ ግጭት፣ ፈጣን ምላሽ አልሰጡም፤ በሚሉ ኬንያውያን በኩል ነቀፋ ተሰንዝሮባቸዋል፡፡ የኬኒያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ለትችቱ በሰጠው ምላሽ፣ ርምጃው የዘገየው ከኢትዮጵያ በኩል በአግባቡ መረጃ ስላልደረሰን ነው፤ ብሏል፡፡ ማይክል ሙቺሪ የኬኒያ ፖሊስ ቃል አቀባይ ናቸው፡፡ “ይህ ሁለቱን አገሮች የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡ በኬንያ የጸጥታ ተቋማት እና በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት መካከል ያለ ነገር ነው፡፡ ግጭቱ ደርሷል በተባለበት ስፍራ ደርሰው ሪፖርታቸውን እስኪያቀርቡልን ድረስ እየተጠባበቅን ነው፡፡” የኬንያ መንግሥት ተጨማሪ የጸጥታ ኀይል በድንበር አካባቢ እያሰፈረ ነው፤ የዐርብቶ አደሮቹ መፈናቀል የተከሰተውም ከስጋት ነው የሚሉ አስተያየቶች ከተፈናቃዮቹ ተሰንዝሯል። ይኽንኑ በተመለከተ የተጠየቁት አቶ ወገነ፣ ኢትዮጵያ እና ኬንያ በጸጥታ እና በጋራ ልማት የሁለትዮሽ እና ስልታዊ ግኑኝነት ያላቸው፣ የወዳጅነት እንጂ የባላንጣነት ታሪክ የሌላቸው በመኾኑ፣ ብዙ የሚያሰጋ ነገር የለም፤ የፌዴራል መንግሥትም ጉዳዩን በቅርበት በመከታተል ላይ ነው፤ ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። የጠፉትን ዓሣ አሥጋሪዎች ለማግኘት፣ እኹንም ፍለጋው እንደቀጠለ መኾኑን፣ የሁለቱም አገሮች ባለሥልጣናት ገልጸዋል። ከግጭቱ በኋላ በስጋት ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸው የገለጹት ዐርብቶ አደሮች ፣ ከረጂ ድርጅቶችም ኾነ ከመንግሥት እስከ አኹን የደረሰ ሰብአዊ ድጋፍ እንደሌለ ተናግረዋል። የተፈናቀሉ ዜጎች ዕለታዊ ቀለብ እያገኙ ያሉት ከተጠለሉበት ቀበሌ ነዋሪዎች እንደኾነ አመልክተዋል። ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ካለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም. አንሥቶ፣ ለሕይወታቸው ሰግተው ሲሸሹ ነበሩ ከተባሉ አርብቶ ዐደሮች ውስጥ፣ ወደ ቀዬአቸው የተመለሱ አለመኖራቸውን ያነሡት አስተያየት ሰጪው፣ ኾኖም ተፈናቃዮቹ የኢትዮጵያ እና የኬንያ ድንበር የመጨረሻ አዋሳኝ ወደ ኾነው ቀበሌያቸው መመለስ እንደሚሹ ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ እና በኬንያ ዓሣ አሥጋሪዎች መካከል፣ በተፈጠረ የድንበር ላይ ግጭት፣ ከኢትዮጵያ በኩል 13፣ ከኬንያ ደግሞ 22 ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁን፣ የአሜሪካ ድምፅ የአካባቢውን ነዋሪዎች እና ባለሥልጣናቱን ዋቢ አድርጎ መዘገቡ ይታወሳል። Read more