ዩጋንዳ በደቡብ ሱዳን ልዩ ኃይሏን አሰማራች
newsare.net
በደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር እና በተቀዳሚ ምክትላቸው ሪክ ማቻር መካከል የተፈጠረው አለመግባባት፤ ሀገሪቱን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሊመልሳት ይችላዩጋንዳ በደቡብ ሱዳን ልዩ ኃይሏን አሰማራች
በደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር እና በተቀዳሚ ምክትላቸው ሪክ ማቻር መካከል የተፈጠረው አለመግባባት፤ ሀገሪቱን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሊመልሳት ይችላል የሚለው ስጋት እያየለ መሄዱን ተከትሎ፣ ዩጋንዳ ልዩ ኃይሏን በዋና ከተማዋ ጁባ ማሰማራቷን የኡጋንዳ ጦር አዛዥ ትላንት ማክሰኞ አስታወቁ። ነዳጅ አምራች በኾነችው ደቡቡ ሱዳን የኪር መንግሥት ሁለት ሚኒስትሮችን እና በርካታ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናትን ማሰሩን ተከትሎ ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል። በጁባ የተካሄደው እስር እና በሰሜናዊው ናሲር ከተማ የተቀሰቀሰው ግጭት፣ በኪር እና በማቻር ታማኝ ኃይሎች መካከል የተካሄደውን እና ወደ 400 ሺህ ለሚጠጉ ሰዎች ህልፈት ምክንያት የሆነውን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም እ.አ.አ በ2018 የተፈረመውን የሰላም ስምምነት አደጋ ላይ እንደሚጥል ተገልጿል። የኡጋንዳ የጦር አዛዥ ሙሆዚ ካይኔሩጋባ በኤክስ የማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት «ልዩ ኃይላችን ከሁለት ቀናት በፊት ፀጥታዋን ለማስጠበቅ ጁባ ገብቷል» ብለዋል። በዚሁ መልዕክታቸው አክለውም «የዩጋንዳ ጦር የሚያውቀው አንድ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ብቻ ነው ። እሳቸውም ሳልቫ ኪር ናቸው። እሳቸውን በመቃወም የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ በዩጋንዳ ላይ ጦርነት እንደማወጅ ይቆጠራል» ብለዋል። ሮይተርስ በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር የደቡብ ሱዳን ማስታወቂያ ሚኒስትር ቃል አቀባይ እና የጦሩ ቃል አቀባይ የእጅ ስልክ ላይ በመደወል ያደረገ ሙከራ አልተሳካም ። እ.አ.አ በ2013 በደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ዩጋንዳ ከማቻር ጋራ የሚዋጋውን የኪር ኃይል ለማጠናከር ወታደሮቿን በጁባ አሰማርታ የነበር ሲኾን፣ እ.አ.አ በ2015 ለቀው ወጥተዋል። እ.አ.አ በ2016ም በሁለቱ ወገኖች መካከል ጦርነት በመቀስቀሱ የዩጋንዳ ጦር በድጋሚ ለአጭር ጊዜ ተሰማርቶ ነበር። ኡጋንዳ በሰሜን በኩል በምትዋሰናት ጎርቤቷ በድጋሚ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከፍተኛ የስደተኞች ማዕበል ሊነሳ እና በሀገሯ አለመረጋጋት ሊፈጥር ይችላል ስትል ትሰጋለች። ካይኔሩጋባ፣ ዩጋንዳ ጦሯን በጁባ ያሰፈረችው በኪር መንግሥት ተጠይቆ ይሁን ወይም ወታደሮቹ ለምን ያህል ጊዜ በደቡብ ሱዳን እንደሚቆዩ አልተናገሩም። Read more