የዶር. ደብረ ጽዮን ቡድን የመቐለ ከንቲባ ጽሕፈት ቤትን ተቆጣጠረ፤ አቶ ጌታቸው "በትግራይ መፈንቅለ መንግሥት እየተካሔደ ነው” ብለዋል
newsare.net
ከመቶ ቀናት በላይ በዝግ የቆየው የመቐለ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ በዶር. ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል በሚመራው የህወሓት ቡድን በተሾሙት ከንቲባ ቁየዶር. ደብረ ጽዮን ቡድን የመቐለ ከንቲባ ጽሕፈት ቤትን ተቆጣጠረ፤ አቶ ጌታቸው "በትግራይ መፈንቅለ መንግሥት እየተካሔደ ነው” ብለዋል
ከመቶ ቀናት በላይ በዝግ የቆየው የመቐለ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ በዶር. ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል በሚመራው የህወሓት ቡድን በተሾሙት ከንቲባ ቁጥጥር ሥር ውሏል። በዶር. ደብረ ጽዮን ሊቀ መንበርነት በሚመራው የህወሓት ቡድን በኩል ታጭተው በከተማዋ ምክር ቤት የተሾሙት ዶር. ረዳኢ በርሀ፣ ዛሬ ኀሙስ፣ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በከንቲባ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ገብተው ሥራ መጀመራቸውን ይፋ አድርገዋል። «ወደ ጽሕፈት ቤቱ የገባነው በሰላማዊ መንገድ ነው፤» ያሉት ዶር. ረዳኢ፣ «የከንቲባውን ጽሕፈት ቤት ሲጠብቁ የነበሩ የከተማዋ ዓይደር ክፍለ ከተማ ፖሊሶች፣ በቦታው መቆየታቸው ትክክል እንዳልኾነ አምነው፣ በመነሣታቸው ነው የገባነው፤» ሲሉ አስረድተዋል። ከ100 ቀናት በላይ ተዘግቶ በቆየው ጽሕፈት ቤት፣ ሕዝባዊ አገልግሎቶችን መስጠት እንደሚጀምሩም ዶክተር ረዳኢ ገልጸዋል። በተመሳሳይ፣ የመቐለ 104.4 ኤፍ ኤም ራድዮ ጣቢያ፣ በዶር. ረዳኢ በርሀ በተሾሙት አቶ ዘመንፈስ ቅዱስ ፍሥሓ እና የከተማው አመራሮች ቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገልጿል። የራድዮ ጣቢያውን በታጣቂዎች ታጅበው እንደተቆጣጠሩት፣ አንድ የጣቢያው ሠራተኛ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጿል። በጉዳዩ ላይ፣ ከአቶ ዘመንፈስ ቅዱስ ማብራርያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፣ “መፈንቅለ መንግሥት እየተፈጸመ ነው፤” ብለዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ ዛሬ ኀሙስ፣ በዐዲስ አበባ ሸራተን ዐዲስ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በአኹኑ ሰዓት ትግራይ ውስጥ እየተፈጠረ ያለው፣ “አንድ የሕወሓት አንጃ ደጋፊዎቼ ያላቸውን የተወሰኑ ከፍተኛ መኰንኖችን በመያዝ ማኅተም የመንጠቅና ሥራዎች እንዳይሠሩ የማድረግ ሥራ እየሠራ ነው፤” ብለዋል። “ይህን ሥርዐት ለማስያዝ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ዕድል ተነፍጓል፤” ያሉት አቶ ጌታቸው፣ በዚኽ ሰዓት የፌዴራል መንግሥቱ “አግባብነት ያላቸውን ርምጃዎች መውሰድ አለበት፤” ብለዋል። ይህ ማለት ግን “ጦር አዝምቶ ጦርነት ይቀስቅስ ማለት አይደለም” ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ነገር ግን፣ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋራ በመኾን፣ አሁን በክልሉ ባለው ኹኔታ ምክንያት ጦርነት እንዳይፈጠር የሚያስችሉ ርምጃዎችን መውሰድ የፌዴራል መንግሥት ኃላፊነት ነው፤” ሲሉ አመልክተዋል። “በምክር ቤት ደረጃ ተሰብስበን የፌዴራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ በይፋ ያቀረብነው ጥያቄ የለም፤” ካሉ በኋላ “ጥያቄውም ያስፈልገዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት በጋራ ያቋቋምነውን ጊዜያዊ አስተዳደር መታደግ የፌዴራሉ መንግሥት ሓላፊነት ነው፤” ብለዋል። በክልሉ የሚንቀሳቀሱት ዓረና ትግራይ፣ ባይቶና እና ወድብ ናፅነት ትግራይ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ ወታደራዊ ኀይል በመጠቀም የመንግሥት ሥልጣን ለመቆጣጠር የሚደረግ እንቅስቃሴን እንቃወማለን፤ ብለዋል። ተቀማጭነታቸው በዐዲስ አበባ የኾኑ የዩናይትድ ስቴት ኤምባሲን ጨምሮ የ25 ሀገራት ኤምባሲዎች፣ በሰሜን ኢትዮጵያ እያገረሸ ያለውን ውጥረት እየተከታተሉት እንደኾነ ጠቅሰው፣ የፕሪቶርያው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት፣ የጥይትን ድምፅ ያጠፋ በመኾኑ ገቢራዊነቱን እንደሚደግፉ ገልጸዋል። ዳግመኛ ወደ ግጭት መግባት አይገባም፤ ያሉት ኤምባሲዎቹ፣ ኹሉም ተቀናቃኝ ኀይሎች ውጥረቱን እንዲያረግቡና ወደ ውይይት እንዲገቡ ጠይቀዋል፤ ለዚኽም ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ አስታውቀዋል። Read more