newsare.net
በሲቪሎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት እና የአከባቢው አለመረጋጋት አሳሳቢ ነው ያሉ ከ50 በላይ ሀገራት ለእስራኤል የሚደረገው የጦር መሣሪያ ሽያጭ በአስቸኳይ እንዲቆከ50 በላይ ሀገራት ለእስራኤል የመሣሪያ ሽያጭና አቅርቦትን እንዲያስቆም ተመድን ጠየቁ
በሲቪሎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት እና የአከባቢው አለመረጋጋት አሳሳቢ ነው ያሉ ከ50 በላይ ሀገራት ለእስራኤል የሚደረገው የጦር መሣሪያ ሽያጭ በአስቸኳይ እንዲቆም ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ደብዳቤ ልከዋል፡፡ በቱርክ አስተባባሪነት ለሁለት የተባበሩ መንግሥታት ድርጅት አካላት እና ለድርጅቱ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ የተላከውና ትላንት ሰኞ ማምሻው ላይ አሶሴይት ፕሬስ እጅ የገባው የሀገራቱ ደብዳቤ፣ “በጋዛ እና በሌሎች የፍልስጤም ግዛቶች እንዲሁም በሊባኖስ እና በቀሪው የመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄደ ያለው ዓለም አቀፍ ህጉን የጣሰ ነው” ሲል እስራኤልን ከሷል፡፡ ሀገራቱ በደብዳቤያቸው " ዓለም አቀፍ ህግን በመጣስ እስራኤል እየፈፀመች ባለችው ድርጊት ሳቢያ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው አብዛኞቹ ህጻናት እና ሴቶች የሆኑበት አስደንጋጭ የሰላማዊ ሰዎች እልቂት፣ ህሊና የማይቀበለውና የማይታለፍ ነው፡፡” ብለዋል፡፡ በአካባቢ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ከመጠን ያለፈ ሰብአዊ ስቃይ እና ክልላዊ አለመረጋጋት ለማስቆም አፋጣኝ ርምጃ መውሰድ አለብን” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ “የተባበሩት መንግሥታት ይህንን ቀውስ ለማስቆም፣ አስቸኳይ የተኩስ ማቆም ማወጅና፣ የሰላማዊ ሰዎችን ህይወት የሚታደግ ርምጃዎችን መውሰድ፣ ተጠያቂነት ማረጋገጥና ለእስራኤል የሚተላለፈው መሣሪያ እንዲቆም ግልጽ ጥያቄ ማቅረብ አለበት ሲል” የሀገራቱ ደብዳቤ ጠይቋል፡፡ በተባበሩት መንግስታት የእስራኤል አምባሳደር ዳኒ ዳኖን የቱርክን ተሳትፎ ውድቅ በማድረግ “በጥፋት ኃይሎች ድጋፍ ግጭትን ለመቀስቀስ ሙከራ ከምታደርግ ሀገር ምን ልንጠብቅ እንችላለን” ብለዋል፡፡ “የእስራኤል ጥቅሞች ከየትኛው ፖለቲካዊ እና ወታደዊ ጥቃት ለመከላከል መታገላችንን እንቀጥላለን “ሲሉም አምባሳደሩ ሀገራቸው ራሷን ለመከላከል ያላትን አቋም ገልጸዋል። ደብዳቤውን ከፈረሙት መካከል የአረብ ሊግ ፣ የእስላማዊ ኮርፖሬሽን፣ ኖርዌ እና ደቡብ አፍሪካ ይገኙበታል፡፡ ደቡብ አፍሪካ በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ተፈጽሟል ስትል እስራኤልን በመክሰስ ጉዳዩን ከዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ፊት ማቅረቧ ይታወሳል፡፡ በጋዛ የእስራኤል ሀማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ከ43ሺ በላይ ሰዎች መገደላቸውን የፍልስጤም የጤና ባለሥልጣናት አስታውቀዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ሴቶችና ህጻናት መሆናቸውን ባለሥልጣናቱ ገልጸዋል፡፡ ጦርነቱ የተጀመረው እኤአ ጥቅምት 7 2023 ወደ እስራኤል ዘልቀው የገቡ የሃማስ ታጣቂዎች አብዛኞቹ ሰላማዊ የሆኑ 1ሺ200 ሰዎችን ከገደሉና 250 የሚሆኑትን አግተው ከወሰዱ በኋላ ነው፡፡ Read more