newsare.net
በአዘርባጃን ዋና ከተማ፣ ባኩ በተካሄደው 29ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባዔ፣ የበለጸጉ ሀገራት፣ ታዳጊ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውንዓለም አቀፉ የገንዘብ ድጋፍ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ማህበረሰብ እንዴት ይደርሳል?
በአዘርባጃን ዋና ከተማ፣ ባኩ በተካሄደው 29ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባዔ፣ የበለጸጉ ሀገራት፣ ታዳጊ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ጉዳት መቋቋም የሚያስችላቸውን የገንዘብ ድጋፍ እንዲሰጡ ጥረት ተካሂዷል። ለመሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ እየተጎዱ ያሉ ሀገራት ከዚህ የገንዘብ ድጋፍ ምን ያክል ተጠቃሚ ይሆናሉ? በደቡብ ኢትዮጵያ፣ ጎፋ ዞን ሐምሌ ወር ላይ ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ተከታታይ የመሬት መንሸራተት አደጋ ህይወታቸውን ማጣታቸው ከተረጋገጠው 243 ሰዎች መካከል የአቶ ሰለሞን ሶማም ታላቅ እህት እና ሌሎች 13 የቤተሰባቸው አባላት ይገኙበታል። በአደጋው ምክንያት አሁንም ድንጋጤ እና ሐዘን ላይ መሆናቸውን የሚገልጹት አቶ ሰለሞን አርሶ አደር ናቸው። ከአባታቸው በወረሱት ማሳ ባቄላ፣ በቆሎ፣ እና ጤፍም ያመርቱ ነበር። አሁን ግን ተፈናቃይ ናቸው። በእድሜያቸው አይተውት የማያውቁት መሆኑን የሚገልጹት አስደንጋጭ አደጋ የደረሰው፣ በደን ምንጣሬ እና መሬት ያለእረፍት በተደጋጋሚ በመታረሱ ምክንያት የአየር ንብረቱ በመለወጡ ነው ብለውም ያምናሉ። በኦሮሚያ ክልል፣ ቦረና ዞንም እንዲህ ለአምስት ተከታታይ ወቅቶች ዝናብ ባለመዝነቡ በተከሰተው ድርቅ ሰዎች ለረሃብ ተጋልጠዋል፣ የሕዝቡ ዋና መተዳደሪያ የሆኑ ከብቶች በብዛት አልቀዋል፣ ሚሊየኖችም ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። አቶ ሊበን ጎዳና በዞኑ ያቤሎ ከተማ ውስጥ ነዋሪ ሲሆኑ፣ በስድስት እና በሰባት አመት ይከሰት የነበረው ድርቅ አሁን በአመት እና በሁለት አመት የሚመጣ በመሆኑ በነዋሪው ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ያመለክታሉ። አቶ ሊበን አክለው በተደጋጋሚ ለድርቅ እና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭ የሆነው የቦረና ማህበረሰብ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት፣ የማህበረሰቡ የአኗኗር ዘይቤን ከመቀየር አንስቶ በርካታ ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባ ያምናሉ። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርስባቸውን ጉዳት ለመቋቋም የሚያስችል መሠረተ ልማት እንደሌላቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያመለክታል። የገንዘብ ድጋፍ ከተገኘ ግን የሚሊየኖችን ህይወት ለማዳን እና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓቶችን ለመዘርጋት እንደሚቻልም ይገልጻል። በአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ የተካሄደው 29ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ቁልፍ እና አንገብጋቢ ጉዳይም ይህ ነበር። በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳትን እያስተናገዱ ባሉ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገራት እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ እንዲያስችል፣ ቃል የተገባው የገንዘብ ድጋፍ እንዲጨምር እና ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ። ቢኒያም ያዕቆብ በዓለም አቀፉ የአካባቢ እና ልማት ተቋም ከፍተኛ ጥናት አጥኚ ሲሆኑ በጉባዔው ላይ ታዳጊ ሀገራትን ወክለው ይደራደራሉ። የበለጸጉ ሀገራት የታሰበውን የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት ስምምነት ላይ ቢደርሱም፣ ታዳጊ ሀገራት ገንዘቡን ለማግኘት እንደ የዓለም ባንክ ወይም የአየር ንብረት ፈንድ ያሉ ተቋማት ማመልከቻዎች ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ በፊት በታየው ልምድ ግን ብዙዎቹ ታዳጊ ሀገራት ይህ ገንዘብ ለማግኘት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን በሚፈለገው መሥፈርት እና ጊዜ ለማቅረብ እንደሚቸገሩ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ዶክተር ይተብቱ ሞገስ የደን ስነ-ምህዳር ባለሙያ ናቸው። የታዳጊ ሀገራት አቅም ውሱንነት በአዘርባጃን ከተነሱ የድርድር አጀንዳዎች መካከል አንዱ መሆኑን አቶ ቢኒያም ያመለክታሉ። ታዳጊ ሀገራት ካሉባቸው የውስጥ ችግር በተጨማሪ የበለጸጉ ሀገራት ገንዘቡን የሚለቁበት መንገድ ውስብስብ መሆንም ሌላው ችግር ነው። በመሆኑም ዶክተር ይተብቱ ኢትዮጵያ ይህን ውስብስብ አሰራር ተረድተው መረጃዎችን በፍጥነት ማጠናከር የሚችሉ ተቋማት እንዲቋቋሙ ይመክራሉ። የበለጸጉ ሀገራት እንዲሰጡ በሚጠበቀው የገንዘብ ድጋፍ ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረስ ከተቻለ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ታዳጊ ሀገራት በገንዘቡ መጠቀም የሚያስችል ብቅት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። እስከዛው ለአየር ንብረት መዛባት እምብዛም አስተዋፅኦ የሌላቸው የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች በተደጋጋሚ ከሚያጠቃቸው የድርቅ እና የጎርፍ አደጋ ለመላቀቅ በተስፋ ይጠብቃሉ። Read more