newsare.net
የዩናይትድ ስቴትስ ተመራጩ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፈረንሳይ ፓሪስ ከዩክሬንና ፈረንሳይ ፕሬዘዳንቶች ጋር ካደረጉት አጭር ስብሰባ በኋላ ከአንድ ሽህ ቀናትራምፕ ከዘለንስኪ ጋር ከነበራቸው ውይይት በኋላ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ
የዩናይትድ ስቴትስ ተመራጩ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፈረንሳይ ፓሪስ ከዩክሬንና ፈረንሳይ ፕሬዘዳንቶች ጋር ካደረጉት አጭር ስብሰባ በኋላ ከአንድ ሽህ ቀናት በላይ የሆነውን ጦርነት ለማቆም ኪየቭ “ስምምነት ማድረግ ትፈልጋለች” በማለት በዩክሬን አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ዛሬ እሁድ አሳስበዋል፡፡ ትሩዝ ሶሻል በተባለው የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባወጡት ጽሁፍ መጀመርያም መከሰት አልነበረበትም ባሉት ጦርነት ኬቭና ሞስኮ በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ ወታደሮቻቸውን ማጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ግጭቱን ለማቆም እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ ባደረጉበት በዚህ መልዕክታቸው «አፋጣኝ የተኩስ ማቆም እና ድርድር መጀመር አለበት፣ ብዙ ህይወት ያለ ምክንያት እየጠፋ ነው ፣ ብዙ ቤተሰቦችንም አጥፍቷል» ብለዋል። የትራምፕ አስተያየት የመጣው ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ እና ከፈረንሳዩ አቻቸው ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ቅዳሜ ተገናኝተው ዘለንስኪ “ገንቢ” ያሉትን ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው፡፡ በእለቱ ዘለንስኪ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ማንኛውም የሰላም ስምምነት ለዩክሬናውያን “ፍትሃዊ መሆን አለበት” ሩሲያ እና ፑቲን ወይም ሌሎች ወራሪዎች የመመለስ እድል ሊኖራቸውም አይገባም ብለዋል፡፡ ዘለንስኪ ዛሬ በማህበራዊ ሚድያ ባጋሩት መረጃ ደግሞ የሞስኮ ወረራ ከጀመረበት እአአ የካቲት 24፣ 2022 እስካሁ ድረስ ሃገራቸው 43ሽ ወታደሮችን ማጣቷንና 370ሽ የሚሆኑት መቁሰላቸውን አስታውቀዋል፡፡ ሁለቱም ሩሲያ እና ዩክሬን የሟቾችን ቁጥር ይፋ ለማድረግ ፈቃደኞች አልነበሩም፣ ነገር ግን የምዕራባውያን ባለስልጣናት ባለፉት ጥቂት ወራት በምስራቅ ዩክሬን ውስጥ የተካሄደው የጦርነት በሁለቱም ወገኖች ላይ ከፍተኛውን ኪሳራ ያስከተለ ሲሆን በየወሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሚሞቱና እንደሚቆስሉ ይናገራሉ፡፡ Read more