newsare.net
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2024፣ በታሪክ ታይቶ በማያውቅ መልኩ ከ60 በላይ ሀገሮች ምርጫ ያካሄዱበት ዓመት ነበር። ምርጫዎቹን ተከትሎ ከድምፅ አሰጣጥ እና የምተሰናባቹ የአውሮፓውያን 2024 ሲቃኝ
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2024፣ በታሪክ ታይቶ በማያውቅ መልኩ ከ60 በላይ ሀገሮች ምርጫ ያካሄዱበት ዓመት ነበር። ምርጫዎቹን ተከትሎ ከድምፅ አሰጣጥ እና የምርጫ ውጤት ጋር የተያያዙ ከ160 በላይ ተቃዎሞዎች መቀስቀሳቸውንም ካርኒጅ የተሰኘው ዓለም አቀፍ የተቃውሞ መቆጣጠሪያ ማዕከል አስታውቋል። ከቁጥሩ በላይ ግን ዓመቱን የተለየ የሚያደርገው፣ ከተለመደው ወጣ ባለ መልኩ፣ በስልጣን ላይ የነበሩ በርካታ መሪዎች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ አለመቻላቸው መሆኑን ፒው የተሰኘው የጥናት ተቋም አመልክቷል። የኢትዮጵያ እና የሶማሌላንድ ስምምነት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2024 የጀመረው ባልተለመዱ እና ባልተጠበቁ ፖለቲካዊ ክስተቶች ነው። ከጅምሩ አዲሱን ዓመት ለመቀበል ዓለም ትኩረቱን በበዓሉ ዝግጅት ላይ ባደረገበት እለት፣ ኢትዮጵያ የባህር በር የምታገኝበት የመግባቢያ ሰነድ ከሶማሌላንድ መሪዎች ጋር መፈራረሟን አስታወቀች። በወቅቱ ለ50 ዓመት የሚዘልቅ ሊዝ እና እየታደሰ እንደሚቀጥል የተገለጸው ስምነት፣ ከባህር በር በተጨማሪ ኢትዮጵያ የጦርና የንግድ ሠፈር እንዲኖራት የሚፈቅድ መሆኑ ተገልጾ ነበር። ሶማሌላንድ በበኩሏ በምትኩ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ እውቅና ልትሰጣት መስማማቷን አስታውቃ ነበር። ወዲያውኑ ግን የሶማሌላንድ ግዛት የአስተዳደሯ አካል መሆኑን የምትገልጸው ሶማሊያ «ስምምነቱ ሕጋዊ መሠረት የሌለው እና ሊዓላዊነቷን እንደሚዳፈር» በመግለፅ ተቃውሞዋን አሰማች። በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውን አል-ሻባብ ለመዋጋት በሀገሯ የሚገኙ ወታደሮች ለቀው እንዲወጡ እንደምታደርግም ዛተች። በዚህ ምክንያት 2024 በአፍሪካ ቀንድ የቀውስ ስጋት የፈጠረውን ይህን ውጥረት ለማርገብ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጥረቶች የተካሄዱበት ሆኖ አልፏል። በዓመቱ ማገባደጃ ላይ በቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን አደራዳሪነት፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከሶማሌላንድ ጋር በተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ምክንያት ለአንድ ዓመት ገብተውበት የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ለማቆም ስምምነት ማድረግ ቢችሉም፣ አሁንም ውጥረቱ ሙሉ ለሙሉ አልበረደም። ብሪክስ በ2024 መግቢያ የዓለም ትኩረት የሳበው ሌላው ጉዳይ፣ ኢትዮጵያ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤም ሬትስ በመልማት ላይ ያሉ አገሮች የመሰረቱትን 'ብሪክስ' የተሰኘ ቡድን መቀላቀላቸው ነው። የምዕራባውያን አገሮች፣ እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የዓለም ባንክ የመሳሰሉ ለመንግሥታት ብድር የሚሰጡ ጠቃሚ ዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ ያላቸው ጫና የወለደውን ይኽን ቡድን ኢትዮጵያ የተቀላቀለችውም፣ በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ምክንያት መሆኑን፣ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሞያዎች ማህበር የምርምር እና ፖሊሲ ትንተና ዳይሬክተር እና የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ ዶክተር ደግዬ ጎሹ አመልክተው ነበር። የአባላቱ ቁጥር ዘጠኝ የደረሱት ብሪክስ በዚህ አመት የተለያዩ ጉባዔዎችን ያካሄደ ሲሆን በሀገራቱ መካከል በሚደረጉ የንግድ ልውውጦች ብሄራዊ ገንዘባቸውን እንዲጠቀሙ የሚያስችል አሰራር ለመፍጠር በመሥራት ላይ መሆናቸውንም በዚህ እየተገባደደ ባለው ዓመት አስታውቀዋል። ሱዳን የአውሮፓውያኑ 2024፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶማሊያ እና ኤርትራ በሚገኙበት የአፍሪካ ቀንድ እየተባባሰ ከሄደው ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት በተጨማሪ፣ በሀገር ውስጥ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች የቀጠሉበት እና እና አዳዲስ የእርስ በእርስ ግጭቶችም የተፈጠሩበት አመት ነበር። ከቀጠናው ወጣ ሲል ደግሞ በሰሜን ምስራቅ በምትገኘው ሱዳንም፣ በሀገሪቱ ጦር ሰራዊት እና በፈጥኖ ደራሹ ኃይል መካከል የሚካሄደው ጦርነት በዚህ አመት አንደኛ አመቱን አስቆጥሮ ቀጥሏል። በዋና ከተማዋ ካርቱም ጨምሮ፣ በዳርፉር፣ ኮርዶፋን እና ሌሎች ክልሎች ከባድ ውጊያዎች ተካሂደዋል። ለ20 ወራት በሱዳን የዘለቀው ይህ አስከፊ ጦርነት እስከዛሬ ከተመዘገቡት ሁሉ ትልቁ ሰብዓዊ ቀውስ ሆኖ መመዝገቡን የዓለም ነፍስ አድን ኮሚቴ ያስታወቀ ሲሆን ከ11 ሚሊየን በላይ ዜጎች በሀገር ውስጥ እና በውጪ ሀገራት መፈናቀላቸውን የመንግስታቱ ድርጅት ገልጿል። ‘የረሃብ ክትትል ኮሚቴ’ በሚል የሚታወቀው ተቋም ከሳምንታት በፊት ይፋ ባደረገው ሪፖርት ከበባ ውስጥ ባለችው የሰሜን ዳርፉር መዲና አል ፋሽር ውስጥ በሚገኙ ሁለት መጠለያዎች፣ እንዲሁም በደቡብ ኮርዶፋን ግዛት በሚገኙ ሌሎች ሁለት አካባቢዎች ረሃብ መስፋፋቱንም አስታውቋል። ወደ 26 ሚሊዮን የሚጠጋ የሱዳንን ሕዝብ ለከባድ ረሃብ ያጋለጠውን አስከፊ ቀውስ ለማርገብ የሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳ መሪዎች የሚገኙበት ስብስብ በዚሁ ዓመት ስብሰባ አካሂዶ ነበር። በመስከረም ወር በኒውዮርክ የተካሄደው 79ኛው የዓለም መሪዎች ጉባዔ አጀንዳ ከነበሩ ርዕሶች አንዱም ይኽ የሱዳን ቀውስ ነው። ሆኖም የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት መቋጫ ሳያገኝ አመቱ ተገባዷል። ምዕራብ አፍሪካ 2024 ከሱዳን በተጨማሪ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ቀውሶች፣ ጥቃቶች እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች ተስተናግደውበታል። ለምሳሌ በየካቲት ወር በሰሜናዊ ቡርኪናፋሶ በሚገኙ ሦስት መንደሮች ላይ የእስላማዊ የጽንፈኛ ኃይሎች ባደረሱት ጥቃት ከ170 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። መጋቢት ወር ላይም በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ ታቂዎች በአንድ ትምህርት ቤት ላይ ወረራ አካሂደው 280 ተማሪዎችን አግተው መውሰድ ችለዋል። ይህም እ.አ.አ በ2014 የቦኮ ሃራም ታጣቂዎች ከቺቦክ መንግደር በመቶዎች የሚቆጠሩ ልጃገረዶችን ካገቱበት ጊዜ አንስቶ፣ ከናይጄሪያ ትምህርት ቤቶች የታገቱ ተማሪዎች ብዛት ከ1ሺህ 400 እንዲበልጥ አድርጎታል። የኔዘርላንድ የጥናት ተቋም የሆነው ክሊነንዳል ኢንስቲትዩት አደገኛ የሆኑ ግንኙነቶችን አስመልከቶ ግንቦት ወር ላይ ይፋ አድርጎት በነበረው የጸጥታ ሪፖርት፣ ታጣቂዎች ከሳህል ቀጠና በባህር ዳርቻ ወደሚገኙ የበለጸጉ ሀገራት እየፈለሱ መሆኑን አመላክቷል። የኢኮኖሚ እድሎች እና ከፍተኛ የድህነት ደረጃ፣ ታጣቂዎች በቀጠናው በቀላሉ ሰዎችን እንዲመለምሉ እና እራሳቸውን እንዲያሳድጉ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም ሪፖርቱ ጨምሮ ገልጿል። የሰሃራ በረሃን አብዛኛውን ክፍል የሚሸፍነው የአፍሪካ ሳህል ቀጠና የዓለም አቀፍ አሸባሪዎች ማዕከል መሆኑን የዓለም ሽብርተኝነት መረጃ ጠቋሚ እ.አ.አ በ2023 ያወጣው መረጃ ያሳያል። ከቅርብ አመታት ወዲህ በቀጠናው የተካሄዱት መፈንቅለ መንግሥቶች የአካባቢውን የጸጥታ ሁኔታ እና ለታጣቂዎቹ ይሰጡ የነበሩ ምላሾችን ክፉኛ እንደጎዱት ባለሙያዎች ይናገራሉ። ይህም በ2024 ተባብሶ ቀጥሏል። የአየር ንብረት ለውጥ ከፖለቲካ አለመረጋጋቱ ጎን ለጎን በ2024 ፈታኝ ሆኖ የቀጠለው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች ናቸው። በደቡብ ኢትዮጵያ፣ ጎፋ ዞን ሐምሌ ወር ላይ የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ከ250 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት አስታውቋል። በዓመቱ መግቢያ በዘነበው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት የኮንጎ ወንዝ ባለፉት ስድስት አስርት አመታት ውስጥ ባልታየ ሁኔታ በመሙላቱ፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በኮንጎ ሪፐብሊክ ያስከተለው ጎርፍ ከ300 በላይ ሰዎች ህይወት ሲያጠፋ ከ350 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ የሰብዓዊ እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል። በሚያዚያ ወር በምስራቅ አፍሪካ የጣለው ከፍተኛ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍም በታንዛኒያ ከ155 በላይ ሰዎችን ሲገድል፣ ከ200 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በደቡብ አፍሪካ ባለፉት 40 አመታት ውስጥ አለመታየቱ የተገለጸ ድርቅም በአንጎላ፣ ቦትስዋና፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ ናሚቢያ፣ ዛምቢያ አንድ ማዳጋስካር ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል። እነዚህ ክስተቶች ታዲያ በህዳር ወር አዘርባጃን ዋና ከተማ፣ ባኩ ውስጥ በተካሄደው 29ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባዔ መፍትሄ ይገኝላቸዋል ተብሎ ተጠብቆ ነበር። በአየር ንብረት ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ላሉ ታዳጊ ሀገራት ለመሰጠት ቃል የተገባው የገንዘብ ድጋፍም ወደ 1.3 ትሪሊየን ዶላር ያድጋል የሚል ተስፋ ተጥሎ ነበር። ሆኖም ከበለጸጉት ሀገራት የሚጠበቀው የገንዘብ ድጋፍም ሆነ፣ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንሱ የሚጠበቀው የአየር በካይ ጋዞችን ልቀት አለመሳካት ብዙዎችን አስቆጥቷል። መካከለኛው ምስራቅ ከአፍሪካ አህጉር ወጣ ስንል ደግሞ፣ 2024 በዋናነት በዩክሬን፣ በጋዛ፣ በሊባኖስ እና በቅርቡ ደግሞ በሶሪያ የተደረጉ ጦርነቶች የተሞላ ነበር። በተለይ በአመቱ ማገባደጃ በሶሪያ የተደረገው ውጊያ ሀገሪቱን ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ ላስተዳድረው የአሳድ ቤተሰብ አገዛዝ ውድቀት ሆኗል። እ.አ.አ በጥቅምት 2023 የሐማስ ታጣቂ ቡድን ያደረሰውን ጥቃት ተክትሎ፣ እስራኤል ከአንድ አመት በላይ በጋዛ ባደረገችው ዘመቻ ከ45 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጋዛ ጤና ሚኒስትርን ጠቅሶ ዘግቧል። እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ወች ያሉ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ተቋማትም እስራኤል ጋዛ ውስጥ፣ በፍልስጤም ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት አድራጎት ፈፅማለች ሲሉ በጦር ወንጀል እና በሰው ልጆች ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎች ከሰዋታል። በ2024 መጀመሪያ ጥር ወር ላይ ደቡብ አፍሪካ ተመሳሳይ ወንጀሎችን ጠቅሳ እስራኤልን በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ከሳ ነበር። ክሱን የተቀበለው ፍርድቤቱም፣ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ፣ የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትራቸው ዮአቭ ጋላንት እና የሐማስ ባለስልጣናትን በጦር ወንጀለኦች በመምክሰስ የእስር ማዘዣ አውጥቶባቸዋል። እስራኤል በጋዛ ላይ የጀመረችውን ጥቃት አጠናቅራ በመካከለኛው ምስራቅ ወዳሉ ሌሎች ሀገራት ፊቷን ያዞረችውም በዚሁ አመት ነው። ሊባኖስ በሚገኘው የሂዝቦላህ ታጣቂዎች ላይ ባደረሰችው ጥቃትም ከ3ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ከእነዚህ ውስጥ በዋና ከተማዋ ቤይሩት ጨምሮ፣ በሊባኖስ የተለያዩ ከተሞች በቤት ሰራተኝነት የሚተዳደሩ በሺዎች የሚቅጠሩ ኢትዮጵያውያንም ይገኙበታል። በዚህ ምክንያት በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ያመለከቱት በቤይሩት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያኖች የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ሀገራቸው እንዲመልሳቸው ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን እያቀረቡ ይገኛሉ። የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የሚካሄደው ጦርነት ያላሸናፊ እና ያለተሸናፊ በ2024ም ቀጥሏል። በላቁ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ፣ ሩሲያ ወደፊት ለመግፋት የምታደርጋቸው ሙከራዎች እና የዩክሬን መልሶ የማጥቃት ዘመቻዎች በንፁሃን ዜጎች እና በሲቪል ተቋማት ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ቀጥለዋል። አንዳቸውም ግን የማሸነፍ ወይም ወደ ሰላም ድርድር የመምጣት ምልክት አላሳዩም። ይልቁኑም ሁለቱም ሀገራት በ2024 በነበራቸው የውጊያ ሂደት የሰው አልባ አውሮፕላን አጠቃቀማቸው በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ እስካሁን 1.5 ሚሊየን ድሮኖችን መግዛታቸው ተመልክቷል። ስፖርት 2024 በአብዛኛው ጦርነቶች፣ መፈናቀሎች፣ ረሃብ፣ እና በአየር ንብረት ቀውስ በደቀኗቸው ፈተናዎች የተሞላ ይሁን እንጂ፣ ሙሉ ለሙሉ ግን የጨለመ አልነበረም። በየካቲት ወር አንድ ወር ለተጠጋ ጊዜ የተካሄደው የአፍሪካ ሀገራት የእግር ኳስ ዋንጫ ፍልሚያ የብዙ ኳስ አፍቃሪያንን ቀልብ የሳበ ሆኖ አልፏል። ውድድሩንም አዘጋጇ ሀገር ኳትዲቯር ተፎካካሪዋን ናይጄሪያን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ፣ በአሸናፊነት አጠናቃለች። ከ60ሺ በላይ ህዝብ በሚያስተናግደው አላሳን ዋተራ (ኢቤምፒ) ስታዲየም የተከናወነውን የፍጻሜ ጨዋታ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ አፍሪካዊያን በቀጥታ ስርጭት የተከታተሉት ሲሆን የዘንድሮውን የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ ለማዘጋጀት ኳትዲቯር 1 በሊየን ዶላር ገደማ እንዳወጣች ተመልክቷል። ሐምሌ ላይ በፓሪስ የተካሄደው የበጋ ኦሎምፒክስ ፉክክርም ዓለምን ያስደመሙ አስደናቂ የአትሌቲክስ ትዕይንቶች የታዩበት ሆኖ የተጠናቀቀው በተሰናባቹ 2024 ነበር። በመክፈቻው ስነስርዓት ፓሪስ፣ የሴይን’ን ወንዝ ተከትሎ ባለው ሥፍራ፣ እጅግ ያማረ፣ በከዋክብት የደመቀ እና ታሪካዊ የውበት እና የለውጥ መፍለቂያ ስሟን ያንጸባረቀ ልዩ የመክፈቻ ዝግጅት ያሳየች ሲሆን፣ በዓለም ዙሪያ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ከሚጫወቱ ድምጻውያን ከፍተኛ ተደማጭነት ያላት ማሊያዊ-ፈረንሳዊቷ የፖፕ ሙዚቃ ኮከብ አቀንቃኝ አያ ናካሙራ፣ በወርቃማ ቀለም የተንቆጠቆጠ ልብስ ለብሳ፣ በዳንሰኞቿ እና በፈረንሳይ ብሄራዊ የክብር ዘብ ባንድ ታጅባ ተወዳጁን «ጃጃ» የተሰኘ ሙዚቃዋን ተጫውታለች። Read more