newsare.net
በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ርዕደ መሬት በተከሰተበት ማዕከል አዋሳኝ ከሚገኙት አፋር፣ ኦሮሚያ እና አማራ ክልል አካባቢዎች 80 ሺሕ ነዋሪዎችን ማራቁን መንግሥት አስመንግሥት 80 ሺሕ ነዋሪዎችን ርዕደ መሬት ከተሰተባቸው አካባቢዎች እያራቀ መኾኑን አስታወቀ
በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ርዕደ መሬት በተከሰተበት ማዕከል አዋሳኝ ከሚገኙት አፋር፣ ኦሮሚያ እና አማራ ክልል አካባቢዎች 80 ሺሕ ነዋሪዎችን ማራቁን መንግሥት አስታወቀ። በርዕደ መሬት መለኪያ እስከ 5.8 ሬክተር ስኬል የተመዘገበ መንቀጥቀጥ ዛሬ አርብ ታኅሣሥ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ሌሊት መከሰቱን የኢትዮጵያ የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መሥሪያ ቤት አስታውቀዋል። መሥሪያ ቤቱ በአወጣው መረጃ፣ ቦታው ከኦሮሚያ ክልል አቦምሳ ከተማ 56 ኪሎ ሜትር እና ከአዳማ ከተማ 146 ኪሎ ሜትር ርቀት እንደሚገኝ የዕለት ሁኔታ በሚያወጣበት መረጃ አጋርቷል። ርዕደ መሬቱ በመጠን እና በድግግሞሽ እየጨመረ መምጣቱን የጠቆመው የኮምዩኒኬሽን መስሪያ ቤቱ መግለጫ፣ ዛሬ ቅዳሜ የተመዘገበው 5.8 ሬክተር ስኬል መጠን ከእስካኹኖቹ የጨመረ መኾኑን ያሳያል። ዛሬ ቅዳሜ ውድቅት ሌሊት ላይ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት ከዚኽ ቀደሞቹ ጠንከር ብሎ አዲስ አበባ፣ አዳማ መተሃራ እና ሌሎች ከተሞች መሰማታቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል። ንዝረቱ የተሰማበት መጠን እንደየ አካባቢዎች የተለያየ መኾኑን ከነዋሪዎቹ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስ ሕዋ ሣይንስ እና አስትሮኖሚ ተቋም የሴስሞሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ፣ ፕሮፌሰር አታላይ አየለ ርዕደ መሬቱ አፋር ውስጥ በምስራቅ ሸዋ ፈንታሌ አካባቢ ዶፈን በተባለ ተራራ መሀል ላይ መከሰቱን ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል። አክለውም “ርዕደ መሬቱ የተከሰተው እዛው ሰሞኑን ሲከሰትበት በነበረው አፋር ክልል ውስጥ አዋሽ ፈንታሌ እና ዶፈን ተራራ መሀል ነው። ሌሎቹ አካባቢዎች የተሰማው የርዕደ መሬቱ ንዝረት ነው” ብለዋል። የኢትዮጵያ ከርሰ ምድር ጥናት ተቋም ዛሬ የተከሰተው መጠኑ ከፍ ያለው 5.8 የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ 10 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍን ጠቁሟል። ከዛሬው ክስስተት በኋላ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ለችግሩ ተጋላጭ ናቸው የተባሉ አካባቢዎችን በመለየትም 12 ቀበሌዎች ላይ መንግሥት ከተለያዩ የሞያ ዘርፎች የተውጣጡ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን በቦታው በማሰማራት የጉዳቱን መጠን አሰሳ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል። 80 ሺሕ ነዋሪዎችን ርዕደ መሬት ከተሰተባቸው አካባቢዎች እያራቀ መኾኑን ገልጿል። በተያያዘም የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ዛሬ ታኅሣሥ 26 ቀን 2017 ዓ.ም በአወጣው መግለጫ፣ በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ እና ዱለቻ ወረዳዎች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳ ነዋሪዎች የርዕደ መሬቱ ክስተት ሊያደርሰው ለሚችል አደጋ ተጋላጭ ናቸው ተብለው መለየታቸውን አስታውቋል። ኮሚሽኑ በአፋር ክልል በአዋሽ ፈንታሌና ዱለቻ ወረዳዎች ውስጥ 35 ሺሕ የሚኾኑ ነዋሪዎች ለችግሩ ተጋላጭ መሆናቸውን አመልክቶ፣ በአዋሽ ፈንታሌ ስድስት ቀበሌዎች ውስጥ ከሚገኙ 15 ሺሕ ነዋሪዎች እስከ አሁን 7ሺሕ የሚሆኑት ወደ ሌላ ስፈራ ተጓጉዘዋል ብሏል፡፡ በዱለቻ ወረዳ ካሉት 20ሺሕ ተጋላጭ ነዋሪዎችም፣ እስከ አሁን ከ6ሺሕ በላይ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውን አክሏል። በኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳም ከአምስት ቀበሌዎች 16 ሺሺ 182 ነዋሪዎች ለአደጋው ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቅሷል። እስከ አሁን ድረስ 7 ሺህ 350 ነዋሪዎች ከስፍራው መውጣታቸውን አስታውቋል፡ቀሪዎቹ ነዋሪዎችም በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ከስፍራው እንደሚንቀሳቀሱ የጠቀሰው የኮሚሽኑ መግለጫ፣ በአጠቃላይ ለ70 ሺሕ ነዋሪዎች ድጋፍ እየተደረገ መኾኑን አክሏል። ንዝረቱ የተሰማቸው ነዋሪዎች የአቦምሳ ከተማ ነዋሪ የኾነችው ዙምራ ማሞ፣ አርብ ሌሊት ለቅዳሜ አጥቢያ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጡን ንዝረት መስማቷን ለአሜሪካ ድምጽ ገልጻለች። “ልጄ አልተኛ ስላለኝ ይዤው መሬት ላይ ተኝቼ ነበር፣ ከዚያ መሬቱ ተንቀጠቀጠ፣ የቤቴ መስታዎት አኹን ረግፏል” ስትል ገልፃለች። ዙመራ ክስተቱ ለደቂቃ መቆየቱን ገልጻ ከዚህ ቀደም ከተነገረው የጠነከረ እንደነበር ተናግራለች። ሌላው በፈንታሌ ወረዳ ነዋሪ የኾነው አቶ አባይኔ ኡርጎ፣ የተሰማው ንዝረት ከዚኽ ቀደሞቹ ከፍ ያለ እንደነበር ተናግሯል። አቶ አባይነህ የሌሊቱ ንዝረት ለአንድ ደቂቃ ያህል መቆየቱን ገልጸው፣ ኃይሉም ከዚኽ ቀደሞቹ ጠንከር ያለ እንደነበር ጠቁመዋል። ክስተቱ በአፋር ክልልና በፈንታሌ አካባቢዎች በተደጋጋሚ እንደሚከሰት አቶ አባይነህ ጠቅሰው፣ የአካባቢው ነዋሪዎች በፍራቻ ከቤታቸው እያደሩ እንደኾነም ተናግረዋል። ሌላው ንዝረቱ የተሰማበት አዲስ አበባ ከተማ ሲኾን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ከዚኽ ቀደሞቹ ኹሉ ጠንከር ያለ ያለና ዘለግ ላለ ሰከንዶች የቆየ መኾኑን ገልጸውልናል። አዲስ አበባ ከተማ ኮተቤ አካባቢ ነዋሪ የኾነው አዲስ ወንድሙ፣ ሕምፃ ላይ አራተኛ ፎቅ እንደሚኖር ገልጾ፣ በሰዓቱ ወንበር ላይ ተቀምጦ የጹሑፍ ሥራ እየሠራ እንደነበር ገልጾልናል። “ድንገት ነው የተከሰተው እንደ መወዝወዝ ነው የምቆጥረው። ለጥቂት ሰከንዶች ሕንፃው ቦታውን የለቀቀ ነገር መሰለኝ። ልክ እንደ ፔንዱለም ዐይነት ነገር ነው የተሰማኝ። ከዚኽ ቀደሞቹ የአኹኑ ትንሽ ጠንከር ያለ ነው። እንቅልፍ ላይ የነበረችው ባለቤቴም በንዝረቱ ነቅታ ወደ እኔ መጣች” ብሎናል። ኤፍሬም ዋቅጅራ የተባለ በአዲስ አበባ መካኒሳ አካባቢ ነዋሪ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረቱ ላለፉት አምስት ቀናት በተለያየ ጊዜ ሲሰማው እንደነበር ገልጾ፣ የትላንት ምሽቱ ግን “ከእንቅልፌ የቀሰቀሰኝ ከባድ ነበር” ሲል ጠቅሷል። በአፋር ክልል ርዕደ መሬቱ ሲከሰት የመጀመሪያ አይደለም። እስካኹን በነዋሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የሚያሳዩ ሪፖርቶች አልወጡም። ኾኖም በአፋር ክልል በዐሥሮች የተቆጠሩ ቤቶች መፍረሳቸው ተዘግቧል። ከዚኹ ጋራ በተያያዘም፣ በኢትዮጵያ አፋር ክልል፣ አዋሽ ፈንታሌ የእሳተ ገሞራ መፈንዳት ምልክቶችን እንዳሳየ የኢትዮጵያ ከርሰ ምድር ጥናት ተቋም ዛሬ ትላንት በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ከአጭር ቪዲዮ ጋራ ባጋራው መረጃ አስታወቀ። ተቋሙ በአዋሽ ፈንታሌ ጭስ ሲወጣ ከሚያሳየው የቪዲዮ ምስል ጋራ ባጋራው መረጃም፣ «ሰሞኑን ሲጠበቅ የነበረው አዋሽ ፈንታሌ በአሁኑ ሰዓት በአፋር ክልል ዱላቻ ወረዳ ዶፋን ተራራ ላይ የታመቀ ውሃ እና እንፋሎት ተከሰተ» ብሏል። በዚህም ምክኒያት ባለሥልጣናት ነዋሪዎችን ወደ ጊዜያዊ መጠለያ እንዲያዘዋውሩ ማድረጋቸውን የሀገር ውስጥ ብዙኅን መገናኛ ዘግበዋል። በመንግሥት የሚደገፈው ፋና ብሮድ ካስቲንግ በአፋር ክልል የጋቢ ረሱ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አብዱ ዓሊ ጠቅሶ በአወጣው ዘገባ፣ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ነዋሪዎችን ወደ ጊዜያዊ መጠለያ የማጓጓዝ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ጠቅሷል። «ፍንዳታ ለመሆኑ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም፣ ባለሥልጣናት ጥንቃቄ ማድረግን መርጠዋል» ሲሉ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር ሽፈራው ተክለማሪያም ማስታወቃቸውን ደግሞ ሮይተርስ ዘግቧል። ከአንዳንድ ሥፍራዎች ሰዎች መውጣት መጀመራቸውንና በትንበያው መሠረት ሰዎችን ሥርዐት ባለው መንገድ እንደሚያስወጡም ኮሚሽነሩ ጨምረው አስታውቀዋል።አካባቢው ከመስከረም ወር ጀምሮ መሬት መንቀጥቀጥ ሲስተዋልበት ቆይቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት እስካኹን የመሬት መንቀጥቀጡ በዋና ከተሞች እስካኹን የጎላ ተጽዕኖ እንዳላሰደረ ገልጾ፣በባለሞያዎች የሚሰጡ የጥንቃቄ መልዕክቶችን እንዲከታተሉ እና በጥብቅ እንዲተገብሩ አሳስቧል። በሌላ በኩል በኢትዮጵያ አብዛኞቹ ህንፃዎች ለርእደ መሬት ተጋላጭ መኾናቸውን ባለሞያዎች ገለጸዋል። በኢትዮጵያ ያሉት አብዛኞቹ ህንፃዎች በዲዛይን ወቅት በሚፈጠር ክፍተትና በግንባታ ጥራት ጉድለት የተነሳ ለርዕደ መሬት አደጋ የተጋላጡ እንደሆኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለሞያዎች ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ ህንፃዎች ርዕደ መሬትን እንዲቋቋሙ በሚያስችል መልኩ ዲዛይን እንዲደረጉ አስገዳጅ የህንፃ ኮድ ብታዘጋጅም፣ መስፈርቱን ከመከተል አኳያ ክፍተቶች አሉ ብለዋል፡፡ መንግሥት በበኩሉ፣ “በህንፃዎች ግንባታ ወቅት፣ መስፈርቱ እንዲተገበር ጥብቅ ክትትል እየተደረገ ነው፣ ህንፃዎቹም የተወሰነ የርዕደ መሬት መጠንን የመቋቋም አቅም አላቸው” ብሏል። Read more