newsare.net
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀም ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ለማዘዋወር በመሞከርሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ የአምስት ዓመት እስር ተፈረደባቸው
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀም ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ለማዘዋወር በመሞከር ተጠርጥረው የከባድ ሙስና ወንጀል ክስ በተመሠረተባቸው እነ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን ላይ ዛሬ ሐሙስ ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም የእስር ቅጣት ወስኗል። ቀሲስ በላይ ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ በሚቆጠር የአምስት ዓመት እስር እና 10 ሺሕ ብር እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔ ማሳለፉን ከቀሲስ በላይ ጠበቆች አንዱ አቶ ዮናታን ዘውዴ ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል። ቀሲስ በላይ የእስር ጊዜያቸውን ከጨረሱ በኋላም ለሁለት ዓመት ከማንኛውም ማኅበራዊ ተሳትፎ እንዲገደቡም ፍርድቤቱ ወስኗል፡፡ ከቀሲስ በላይ ጋራ አንድ ላይ ክስ ቀርቦባቸው የነበሩት 2ኛና 3ኛ ተከሳሾች ላይ ደግሞ እያንዳንዳቸው ሦስት ዓመት ከሦስት ወር እስራት እና የ3 ሺህ ብር ቅጣት እንደተላለፈባቸው ጠበቃ ዮናታን ተናግረዋል፡፡ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች በአድራሻቸው ባለመገኘታቸውና በተደጋጋሚ ቀጠሮ ባለመቅረባቸው ክሳቸው መቋረጡ ታውቋል። በቀሲስ በላይ መዝገብ ስር ከተከሰሱት በሦስቱ ላይ ፍርድቤቱ ባለፈው ጥር 7 ቀን 2017 ዓ.ም “ በከባድ አታላይነት የሙስና ወንጀል” የጥፋተኝነት ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡ በቀሲስ በላይ ላይ ፍርድቤቱ የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው ካስገቡት የቅጣት ማቅለያ መካከል የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውና ህመምተኛ መሆናቸውን ጨምሮ አራት ማቅለያዎችን በመቀበል የወንጀል ደረጃቸው ከነበረበት “ እርከን 25” ወደ እርከን 21 ዝቅ በማድረግ መሆኑን ጠበቃቸው አቶ ዮናታን ተናግረዋል፡፡ ይሁንና በዚህ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለጠቅላይ ፍርድቤት ይግባኝ ለመጠየቅ እየተዘጋጁ መሆኑንም ጠበቃቸው ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ጠቅላይ ቤተክህነት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ/ም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአፍሪካ ኅብረት ሒሳብ ቁጥር ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀም ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማዘዋወር በመሞከር ተጠርጥረው መከሰሳቸው ይታወሳል፡፡ Read more