newsare.net
የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ ውድመት የደረሰበት የጋዛ ክልል የሚተዳደርበትን አስመልክቶ ያቀረቡትን ሐሳብ ተከትሎ የእስራኤል መከላከያ ሚኒእስራኤል ፍልስጤማውያን ጋዛን ለቀው እንዲወጡ ለማስቻል እንዲያቅዱ ጦሯን አዘዘች
የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ ውድመት የደረሰበት የጋዛ ክልል የሚተዳደርበትን አስመልክቶ ያቀረቡትን ሐሳብ ተከትሎ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ፍልስጤማውያን ከጋዛ ሰርጥ እንዲወጡ የሚያስችል እቅድ እንዲያወጣ ሰራዊቱን አዟል። የመከላከያ ሚንስቴር እስራኤል ካትስ ትላንት ሃሙስ ሲናገሩ፡ «የእስራኤል መከላከያ ኃይሎች የጋዛ ነዋሪዎች በፈቃዳቸው አካባቢውን ለቀው መሄድ የሚያስችላቸው እቅድ እንዲያዘጋጅ መመሪያ ሰጥቻለሁ» ብለዋል። ካትዝ እቅዱ «የመውጫ መንገድ እና የየብስ ማቋረጫ፤ እንዲሁም በባህር እና በአየር ለመጓጓዝ የሚያስችሉ አማራጮች ዝግጅት ያካትታል» ብለዋል። የመከላከያ ሚንስትሩ አክለውም፤ የጋዛ ነዋሪዎች በጦርነቱ ወቅት በሃማስ ታጣቂዎች ላይ በተነጣጠሩት የእስራኤል የምድር ጦር እና የአየር ድብደባዎች የተጎዳውን አካባቢ ለቀው እንዲወጡ ትረምፕ የያዙት “ቆራጥ እቅድ” ያሉትን በደስታ መቀበላቸውን ተናግረዋል። ትረምፕ በበኩላቸው ትላንት ሃሙስ በሰጡት አስተያየት እስራኤል ከሃማስ ጋር ያካሄደችው ጦርነት ካበቃ በኋላ የጋዛ ሰርጥን ለዩናይትድ ስቴትስ አሳልፋ መስጠት አለባት፤ ምንም አይነት የአሜሪካ ወታደር በዚያ ማሰማራትም አያስፈልግም ብለዋል። የሜዲትራኒያንን ባህር የሚያዋስነው አካባቢ ያለውን ጠባቡን የጋዛ ሰርጥ ዩናይትድ ስቴትስ በባለቤትነት እንድታስተዳድረው ያላቸውን ፍላጎት አስመልክቶ ‘ትሩዝ ሶሻል’ በተባለው የማሕበራዊ ግንኙነት መድረካቸው ላይ ያሰፈሩት ትረምፕ፤ በእርሳቸውም እቅድ መሠረት ቁጥራቸው ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ፍልስጤማውያን “አዳዲስ እና ዘመናዊ ቤቶች ባሉባቸው ለደህንነታቸው አስተማማኝ በሆኑ እና ይበልጥም በተዋቡ፣ በክልሉ በሚገኙ አካባቢዎች ውስጥ ገና ድሮ እንዲሰፍሩ የሚያስችል ነው” ብለዋል። ትረምፕ የሚሉት ሥፍራ እዚያው ጋዛ ውስጥ ይሁን እስካሁን ሃሳቡን ባልተቀበሉ ሆነ ሌሎች ሃገራት ዝርዝር አልሰጡም። «በእርግጥ ደስተኛ የመሆን፣ ደህንነታቸው የመረረጋጋጥ እና ነጻ የመሆን እድል ይኖራቸዋል» ሲሉ ጽፈዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሃማስ በትላንትናው እለት ሁሉም ፍልስጤማውያን አንጃዎች ትረምፕ ጋዛን ለመቆጣጠር ያቀረቡትን ሃሳብ በመቃወም ተባብረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርቧል። “ችግሩን ይበልጥ አያባብሱ” - ጉቴሬዥ ‘ችግሩን አናባብስ’ ሲሉ ያሳሰቡትን የመንግሥታቱን ድርጅት ዋና ጸሐፊ ጨምሮ፣ የትረምፕ የጋዛ ውጥን ከዓለም ዙሪያ መጠነ ሠፊ ነቀፌታ ገጥሞታል። «መፍትሄ ፍለጋ ፍልስጤማውያንን ከጋዛ በማውጣት ችግሩን ይበልጥ ማባባስ የለብንም» ያሉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶንዮ ጉቴሬሽ «ለመሰረታዊው ዓለም አቀፍ ሕጎች ከበሬታ መቆም ያስፈልጋል። ከማንኛውም አይነት የዘር ማጽዳት ድርጊትም መራቅ አስፈላጊ ነው» ብለዋል። አንድን ሕዝብ ከሚኖርበት አካባቢ በኃይል ወደ ሌላ ሥፍራ ማዛወር በዓለም አቀፍ ሕግ በጥብቅ የተከለከለ እና ከዘር ማጽዳት ሊቆጠር የሚችል ድርጊት ነው። የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ዋልተር ሽታይንማየርም ከትላንት በስቲያ ረቡዕ በሰጡት አስተያየት፤ የትራምፕ ዕቅዶች “በአንዳንድ ወገኖች ላይ ጥልቅ ጭንቀት እና አልፎ ተርፎም የመሸበር ስሜት ጭምር ሊቀሰቅሱ የሚችሉ” እናም “በአለም አቀፍ ኅግ ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው” ብለዋል። 22 አባላት ያሉት የአረብ ሊግ በበኩሉ የትራምፕ እቅድ «አለመረጋጋት ሊያስከትል የሚችል» እና ‘የፍልስጤምን ሀገር የመሆን እድልም የማያቃና” ብሎታል። የብሪታንያው ጠቅላይ ሚንስትር ኪር ስታርመርም በተመሳሳይ፤ ፍልስጤማውያን “ወደ ቤታቸው መመለስ ይችሉ ዘንድ መፈቀድ አለበት” ብለዋል። ቀያቸውን መልሰው እንዲገነቡ ሊፈቀድላቸው፤ እኛም በመልሶ ግንባታው እና ‘የሁለት ሃገር መፍትሔ በሚባለው ዕቅድ አብረናቸው ልሆን ይገባል’ ብለዋል። ትረምፕ የጋዛ ባለቤት ስለመሆን የሰነዘሩትን ይህን ሃሳብ ተከትሎም አውስትራሊያ፣ ቻይና፣ ጀርመን፣ አየርላንድ፣ ሩሲያ፣ ሳውዲ አረቢያ እና ስፔን፤ ሁለቱ አገሮች እስራኤል እና ፍልስጤም እንደ ሃገር ጎን ለጎን በሰላም የሚኖሩበትን መንገድ ለመፍጠር የታለመውን ‘የሁለት ሀገራት መፍትሄ’ የተባለ እቅድ መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል። የፍልስጤማውያኑ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስም ‘የመንግስታቱ ድርጅት የፍልስጤምን ህዝብ እና የማይገሰሱ መብቶቹን እንዲያስጠብቅ’ የሚል ጥሪ አሰምተዋል። ትራምፕ ሊያደርጉ ያቀዱት “አለም አቀፍ ህግን በእጅጉ የሚጥስ ነው” ሲሉም ኮንነዋል። Read more