newsare.net
ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን እንደቻለች ይፋ ያደረገችበት መግለጫ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ለሦስት ወራት የውጭ ርዳታ ለማቆም ካስተላለፈችው ውሳኔ ጋራ የተገናኘ አመንግሥት: ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን እንደቻለች ማስታወቁ «ከአሜሪካ ርዳታ መቆም ጋራ በተገናኘ አይደለም፤» አለ
ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን እንደቻለች ይፋ ያደረገችበት መግለጫ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ለሦስት ወራት የውጭ ርዳታ ለማቆም ካስተላለፈችው ውሳኔ ጋራ የተገናኘ አይደለም፤ ሲል መንግሥት አስታውቋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለአሜሪካ ድምፅ በጽሑፍ በሰጠው ምላሽ፣ አኹን ኢትዮጵያ ራሷን የቻለችው፣ በአንድ የምርት ዓይነት ማለትም በስንዴ እህል ምርት እንደኾነ አስታውሷል። በአገሪቱ ውስጥ፣ አስቸኳይ የምግብ ርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች መኖራቸውም፣ በብሔራዊ ደረጃ የምግብ እጥረት ስለ መኖሩ አያሳይም፤ በማለት አብራርቷል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ትላንት ማክሰኞ፣ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን ችላለች፤ ሲል አስታውቋል። ኢትዮጵያ፣ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ለማርካት፣ በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር በሚጠጋ ወጪ ስንዴ ከውጭ ታስገባ እንደነበር ያወሳው መግለጫው፣ አሁን ይህን ማስቀረት መቻሉን ጠቁሟል። «ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገር ውስጥ ምርት ላይ ከፍተኛ ጭማሬ በመታየቱ ኢትዮጵያ ከውጭ በሚገባ የስንዴ ምርት ላይ ጥገኛ መኾኗ ቀርቷል፤» ሲል አመልክቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት መግለጫ የወጣው፣ ዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ርዳታ ለሦስት ወራት ለማቆም የደረሰችበትን ውሳኔ ካስታወቀች ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ነው። ኾኖም፣ በዚኽ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ የሰጡ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት፦ ምግብ፣ መድኃኒት እና ሌሎች የአጣዳፊ ጊዜ ድጋፎች ከዕቀባው ውጪ እንዲኾኑ ትእዛዝ መተላለፉን ግልጽ አድርገዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፣ ሕይወት አድን መርሐ ግብሮች ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ የሚያስችል “ጥቅል ማሳሰቢያ” መስጠታቸውንም ገልጸዋል። “ምግብ፣ መድኃኒት ወይም ማንኛውም ሕይወት አድን የኾነ አጣዳፊ አገልግሎት በዕቀባው አይካተትም፤« ሲሉም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ክፍል፣ በጽሕፈት ለአሜሪካ ድምፅ በሰጠው ምላሽ፣ አገሪቱ በስንዴ ምርት ራሷን መቻሏን ይፋ ያደረገችበት መግለጫ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ለሦስት ወራት የውጭ ርዳታ ለማቆም ካስተላለፈችው ውሳኔ ጋራ የተገኘ አለመኾኑን አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያ ይህን ስኬት በማሳየት፣ በማደግ ላይ ያሉ ሌሎች ሀገራትም፣ ራስን የመቻል መንገድ እንዲከተሉ ይነቃቃሉ ብላ ተስፋ እንደምታደርግም አመልክቷል። ጽሕፈት ቤቱ በትላንቱ መግለጫው፣ የኢትዮጵያ ዓመታዊ የስንዴ ምርት መጠን እያደገ መሞጣቱንም ገልጿል። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2022/23 የምርት ዘመን፣ ኢትዮጵያ 15ነጥብ1 ሚሊየን ቶን ስንዴ እንዳመረተች ጠቁሞ፣ በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ወደ 23 ሚሊየን ቶን ማደጉን ጠቅሷል። አገሪቱ በስንዴ ምርት ራሷን ቻለች ማለት፣ ስንዴ ከውጭ መግባቱ ይቆማል ማለት እንዳልኾነ ግን መግለጫው አስረድቷል። በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የሰብአዊ ርዳታ ተቋማት፣ አኹንም ከሀገር ውስጥ ገበያ ስንዴ ከመግዛት ይልቅ ከውጭ ሀገራት ማስገባትን ሊመርጡ እንደሚችሉ ነው የጠቆመው። የሰብአዊ ርዳታ ተቋማት፣ ስንዴንና ሌሎች አቅርቦቶችን የሚገዙት፦ ከመንግሥት ጋራ በመቀናጀት፣ በአገሪቱ የምግብ ድጋፍ የሚያሰፈልጋቸውን ዜጎች ለመድረስ ነው። እ.አ.አ. በመጋቢት ወር 2024 በመንግሥት እና በዓለም አቀፍ አጋሮች ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ የሰብአዊ ድጋፍ ሰነድ፣ በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ድጋፍ እንደሚጠብቁና ይህንም ለማሟላት ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ አመልክቷል። ገንዘቡ የተጠየቀው፣ የምግብ ርዳታ የሚያስፈልጋቸውን 10ነጥብ4 ሚሊዮን ዜጎችን ፍላጎት ለማሟላት ጭምር እንደኾነ ሰነዱ አመልክቷል። አገሪቱ በስንዴ ራሷን መቻሏን ማስታወቋ፣ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ርዳታ የሚፈልጉ ዜጎች መኖራቸውን ከሚጠቅሰው ከዚኽ ሰነድ ጋራ እንዴት እንደሚጣጣም የተጠየቀው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬዝዳንት ክፍል ማብራሪያ ሰጥቷል። በአገሪቱ የተከሠቱ ድርቅ፣ ጎርፍ እና የመሬት መንቀጥቀጥን የመሳሰሉ አደጋዎች የተረጂዎችን ቁጥር እንደሚጨምሩ ጠቅሷል። ፈተናዎቹ ግን፣ አገሪቱ በምግብ ራሷን ለመቻል ያላትን ቁርጠኘነት አልቀነሱትም፤ ብሏል። ኢትዮጵያ አኹን ራሷን እንደቻለች የገለጸችው በአንድ የምርት ዓይነት ማለትም በስንዴ እንደኾነም አስታውሷል። የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥን፣ ከአገራዊ የምግብ ዕጥረት ጋራ አለመደበላለቅ እንደሚያስፈልግም አስገንዝቧል። ከመቶ ሚሊዮን በላይ ከኾነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ »ርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች አሉ« ማለት፣ »በምንም መንገድ በአገር አቀፍ ደረጃ የምግብ እጥረት መኖሩን አያሳይም፤" ብሏል የጽሕፈት ቤቱ መግለጫ። ዩናይትድ ስቴትስን በመሳሰሉ የበለጸጉ ሀገራትም፣ በምግብ ድጋፍ እና በሌሎች የርዳታ ፕሮግራሞች ላይ የሚተማመኑ ሰዎች መኖራቸውን የጠቀሰው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ክፍል፣ ያ ግን አገራዊ የምግብ እጥረትን አያመለክትም፤ ብሏል። የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሞያ መሸሻ ዘውዴ፣ የመንግሥት መግለጫ የሚያመለክተው፣ ወቅታዊውን የስንዴ ምርት መጠን እንደኾነ ጠቁመዋል። ራስን ለመቻል ዋስትና የሚኾነው ግን፣ የተገለጸው የምርት መጠን ቀጣይነት እንደሚኖረው ማረጋገጥ ሲቻል እንደኾነ ሳያሳስቡ አላለፉም። መንግሥት ይፋ ያደረገው መረጃ አንድን የምርት ዓይነት ብቻ የተመለከተ እንደኾነ የጠቀሱት አቶ መሸሻ፣ በስንዴ ራስን መቻል ማለት በአጠቃላይ የምግብ እህል ምርት ራስን ከመቻል የተለየ መኾኑን አስታውሰዋል። ኢትዮጵያ ስንዴ ከውጭ መግዛት ያቆመችው፣ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ እንደኾነም፣ የመንግሥት መግለጫ አክሎ አውስቷል። Read more