newsare.net
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ በክሪፕቶ ግብይት መሪ የኾኑ ግለሰቦችን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በዋይት ሐውስ ጋብዘው ዲጂታል ሀብት መገንባትን በተመለከተ ምክክርዶናልድ ትረምፕ የክሪፕቶ ግብይት እና ዲጂታል ሀብትን በተመለከተ ከመስኩ መሪዎች ጋራ ምክክር አደረጉ
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ በክሪፕቶ ግብይት መሪ የኾኑ ግለሰቦችን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በዋይት ሐውስ ጋብዘው ዲጂታል ሀብት መገንባትን በተመለከተ ምክክር አድርገዋል። ፕሬዝደንቱ የቢትኮይን ሀብት ክምችትን ለመፍጠር ያላቸውን ፍላጎት በተመለከተም ተወያይተዋል። “አንዳንዶቻችሁ ሰዎች ስለ ጉዳዩ ምንም በማያውቁበት ወቅት ለረዥም ጊዜ ስትሠሩ ቆይታችኋል። እናም እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ። ይህ ትልቅ ቀን ነው” ብለዋል ትረምፕ፡፡ ስብሰባው አሜሪካ በክሪፕቶ መገበያያ ላይ ያላትን የፖሊሲ ለውጥ ያመለከተ ነው። የመስኩ መሪዎች በቀድሞው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር ወቅት የነበሩ ደንቦችን በተመለከተ ቅሬታ ሲያሰሙ ቆይተዋል። ትረምፕ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅትም ክሪፕቶን እንደሚያሳድጉ ቃል ገብተው ነበር። የመስኩ ባለሀብቶችም ለምርጫ ዘመቻቸውና ለበዓለ ሲመታቸው በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ለግሰዋል። በአንዳንድ የክሪፕቶ ኩባንያዎች ላይ የነበረው ክስም እንዲሰረዝ ተደርጓል። “በባይደን አስተዳደር ወቅት በክሪፕቶ ላይ የታወጀውን ጦርነት የእኔ አስተዳደር ለማስቆም እየሠራ ነው” ሲሉ ተናግረዋል ትረምፕ፡፡ ትረምፕ በተጨማሪም የቢትኮይን መጠባበቂያ እንዲቋቋም ፕሬዝደንታዊ ትዕዛዝ ፈርመዋል። የፒው ጥናት ተቋም እንደሚለው አብዛኞቹ አሜሪካውያን የክሪፕቶ መገበያያ አስተማማኝነት ያሳስባቸዋል። የክሪፕቶ መገበያያ ለተጠቃሚውም ኾነ ለፋይናንስ ሥርዓቱ አደጋ እንዳለው ነቃፊዎች ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ የትረምፕ አስተዳደር የክሪፕቶ መጠባበቂያ መመሥረቱ ኢንቨስተሮች በዲጂታል ሀብት ላይ እንዲተማመኑ ያደርጋል ይላሉ። “የክሪፕቶን መገበያያ ሕጋዊ ለማድረግ የተወሰደ ርምጃ ነው። መንግሥት ተቀብሎት የሚቀጥል ከሆነ፣ ግብይቱ ሕጋዊ ነው ማለት ነው” ብለዋል ፖል ኩፔክ ከአሜሪካ ኢንተርፕራይዝ ኢንስቲቱት፡፡ አንዳንድ ታዛቢዎች ደግሞ አሜሪካ በክሪፕቶ መገበያያ መሪ መሆን አለባት ባይ ናቸው። “ትይዩ የሆነ ሁለተኛ የመገበያያ የፋይናንስ ሥርዐት እየፈጠርን ነው። አሜሪካ የፋናንስ ኅይል እንዲኖራት በመስኩ መሳተፏ የአሜሪካ ዜጎችን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው” የሚሉት የኦላፍ ግሮት ከሃስ የንግድ ኮሌጅ ባልደረባ ናቸው። የቢትኮይን መጠባበቂያ የመጀመሪያ ሥራ የሚሆነው፣ መንግሥት ምን ያህል ቢትኮይን እንዳለው ማወቅ ነው። የዋይት ሃውስ ባለሥልጣናት እንደሚገምቱት መንግሥት 200ሺሕ ቢትኮይን እንዳለው ይገምታሉ። ይህም ወደ 17 ቢሊዮን ዶላር ገደማ መሆኑ ነው። ዘገባው ሚሼል ኩዊን ነው። Read more