newsare.net
የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላ አሊ ካሜኒ ዛሬ ቅዳሜ ባሰሙት ንግግር በኢራን እና አጋሮችዋ ላይ ለሚደርሰው ጥቃት “ከባድ ምላሽ” እንደሚሰጡ በመግለጽ እስራኤልየኢራን መንፈሳዊ መሪ እስራኤልና አሜሪካ ከባድ ምላሽ እንደሚጠብቃቸው ዛቱ
የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላ አሊ ካሜኒ ዛሬ ቅዳሜ ባሰሙት ንግግር በኢራን እና አጋሮችዋ ላይ ለሚደርሰው ጥቃት “ከባድ ምላሽ” እንደሚሰጡ በመግለጽ እስራኤል እና ዩናይትድ ስቴትስ ላይ ዝተዋል፡፡ የካሜኒ ንግግር የተሰማው፣ እስራኤል እ.ኤ.አ ጥቅምት 26 በኢራን ወታደራዊ ሰፈሮች እና ሌሎች ቦታዎች ላይ ባነጣጠረ ጥቃት ቢያንስ አምስት ሰዎችን መግደሏን ተከትሎ የኢራን ባለስልጣናት ሌላ ምላሽ እንደሚሰጡ ያሰሙት ዛቻ እየጨመረ ከመጣ በኋላ ነው፡፡ ከሁለቱም ወገኖች የሚሰነዘር ተጨማሪ ጥቃት ሰፊውን መካከለኛ ምስራቅ ሊያካልል ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል፡፡ በጋዛ ሰርጥ በእስራኤልና ሀማስ ጦርነት፣ እንዲሁም እስራኤል ሂዝቦላን ለማጥቃት ሊባኖስ ላይ በምታካሂደው ወረራ ሳቢያ በተለይ ችግር ውስጥ ያለውን ቀጠና ወደባሰ ክልላዊ ግጭት እንዳያስገባ ተሰግቷል፡፡ ይህ ስጋት የተሰማው በተለይ ማክሰኞ ከሚካሄደው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በፊት መሆኑም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡ ካሜኒ «ጠላቶች የጽዮናዊው መንግስትም ይሁን የዩናይትድ ስቴትስ በኢራን ፣ በኢራን ህዝብ እና የተቃውሞ ግንባሩ ላይ እያደረጉት ላሉት ነገር በርግጠኝነት ከባድ ምላሽ ይሰጣቸዋል »በማለት ሲናገሩ የኢራን መንግስት በመገናኛ ብዙሃን በለቀቀው ቪዲዮ አሳይቷል። መንፈሳዊ መሪው በዛቻው ስለተገለጸው ጥቃት ዓይነት፣ ጥቃቱ ሰለሚፈጸምበት ጊዜ እና ቦታ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጡም። የዩናይትድ ስቴትስ ጦር በመላው መካከለኛ ምስራቅ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን አንዳንድ ወታደሮችም እስራኤል ውስጥ ከውጭ የሚመጡ ጥቃቶችን ከሚመክት የጸረ ሚሳይል መሣሪያ ታጣቂ ቡድን ጋር እንደሚሰሩ ተመልክቷል፡፡ የ85 አመቱ ካሜኒ ቀደም ሲል በሰጡት አስተያየት “ባለስልጣናት የኢራንን ምላሽ ይመዝናሉ” ያሉ ሲሆን የእስራኤል ጥቃት “መጋነን ወይም በቀላሉ መታየት የለበትም” ሲሉ የበለጠ ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድን መርጠዋል። ካሜኒ በቴህራን ዩኒቨርሲቲ የሻህ አገዛዝን በተቃወሙ ተማሪዎች ላይ የኢራን ወታደሮች የተኩስ እሩምታ የከፈቱበትንና እኤአ ህዳር 4 ቀን 1978 የሚከበረውን ቀን አስመልክቶ ከዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ጋር ዛሬ ቅዳሜ ተገናኝተዋል። ጥቃቱ በርካታ ተማሪዎችን የገደለ እና ያቆሰለ ሲሆን፣ በወቅቱ ኢራንን አስጨንቆ የነበረውን ውጥረት የበለጠ በማባባስ በመጨረሻም ሻህ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡና እኤአ የ1979 የእስልምና አብዮት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ በስብሰባው ቦታ ካሜኒን የተቀበሉ ታዳሚዎች “ በደም ሥራችን ውስጥ ያለው ደም ለመሪያችን የተሰጠ ስጦታ ነው” የሚል መፈክር እያሰሙ በደማቅ አቀባበል እንደተቀበሏቸው አሶሴይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ አንዳንዶቹም የተገደሉት የሂዝቦላህ መሪ ሃሰን ናስራላህ እኤአ በ2020 የአሜሪካ ወታደሮች “ በሬሣ ሳጥን ይመለሳሉ” ሲሉ በዛቱበት ንግግር ያሳዩትን የእጅ ምልክት አሳይተዋል፡፡ ኢራን የአሜሪካ ኤምባሲው የታጋቾች ቀውስ የተፈጸመበትን 45ኛ ዓመት ነገ እሁድ ታከብራለች። እ.ኤ.አ. ህዳር 4 ቀን 1979 እስላማዊ ተማሪዎች ኤምባሲው ላይ ያደረሱት ጥቃት ለ444 ቀናት የቆየ ቀውስ አስከትሏል፡፡ ይህ ቀውስ በቴህራን እና በዋሽንግተን መካከል ለአስርት አመታት የዘለቀውን ጠላትነት አጠናክሮ ቀጥሏል። Read more