newsare.net
የእሳት አደጋ ሠራተኞች ብርቱ ትንቅንቅ እያደረጉ ላሉበት አደገኛ የሰድድ እሳት ቃጠሎ፣ ከ130 ሺሕ በላይ የሎስ አንጀለስ አካባቢ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንበስፋት እየተዛመተ ላለው የሎስ አንጀለስ ሰደድ እሳት በሺሕዎች የተቆጠሩ አካባቢያቸውን እንዲለቁ ታዘዙ
የእሳት አደጋ ሠራተኞች ብርቱ ትንቅንቅ እያደረጉ ላሉበት አደገኛ የሰድድ እሳት ቃጠሎ፣ ከ130 ሺሕ በላይ የሎስ አንጀለስ አካባቢ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ታዘዋል። እስካሁን ቢያንስ አምስት ሰዎች በአደጋው ሕይወታቸውን ማጣታቸው እና ከ1 ሺሕ በላይ ሕንፃዎች መውደማቸው ታውቋል። ትላንት ከቀትር በኋላ ላይ አዲስ የተቀሰቀሰው እና በጥድፊያ እየተዛመተ ያለው ቃጠሎ ‘ሆሊውድ ሂልስ’ በመባል የሚታወቀው ማዕከላዊ ሎስ አንጀለስ የሚገኝ የመኖሪያ መንደር ነዋሪዎች ህይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ ቤታቸውን ጥለው እንዲሸሹ በማስገደድ የቅርብ ጊዜው ነው። ለሰደድ እሳቱ መዛመት አመች ያደረገው፡ በአካባቢው ያለው ደረቅ የአየር ጠባይ እና ኃይለኛ ነፋስ ተቀላቅለው እስከ ነገ አርብ ድረስ አሁን በያዘው ፍጥነት እንደሚቀጥል የሚቲዎሮሎጂ ባለሞያዎች ጠቁመዋል። በአንጻሩ የእሳቱን መዛመት ለመከላከል የተሰማሩትን አውሮፕላኖች ሥራ አስተጓጉሎ የነበረው ኃይለኛ ንፋስ ከትላንት ረቡዕ አንስቶ ሥራቸውን መልሰው እንዲቀጥሉ በሚያስችል ሁኔታ መቀነሱም ተጠቁሟል። «ዛሬ ማምሻው ላይ ያለው ቀለል ያለ የንፋስ ሁኔታ የሰደድ እሳቱን መዛመት ለመከላከል የሚያግዙ አውሮፕላኖች እና ብዛት ያላቸው ተጨማሪ መከላከያዎች ወደ እሳቱ ለማቅረብ አስችሎናል” ያሉት የፓሳዴና የእሳት አደጋ ዋና አዛዥ ቻድ አውጉስቲን “ይህም አደጋውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ስለመቻላችን ተስፋ ሰጥቶናል” ብለዋል። የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የሰደድ እሳቱን መዛመት ለመዋጋት ለሚያስፈልገው ሥራ የሚውል የገንዘብ እና ሌሎች እርዳታዎች ለካሊፎርኒያ ክፍለ ግዛት ለመልቀቅ የሚያስችል የፌደራል የአደጋ ጊዜ አዋጅ አጽድቀዋል። ዋይት ሀውስ ትላንት ረቡዕ ማምሻው ላይ እንዳስታወቀው ባይደን “በቀጣዩ ቀናት ውስጥ ሙሉ ትኩረታቸውን የፌዴራል መንግስቱ ለሚሰጠው ጠቅላላ ምላሽ አመራር ለመስጠት” ወደ ጣሊያን ሊያደርጉት የነበረውን ጉዞ ሰርዘዋል። »ሰደድ እሳቱን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር፣ አካባቢውን መልሶ የመገንባቱ ጥረት መስመሩን እና ብሎም ወደ ቀድሞው የተረጋጋ ሁኔታ መመለሱን እስክናረጋገጥ ድረስ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ተዘጋጅተናል። ብዙ ጊዜ መውሰዱ የማይቀር ነው” ያሉት ባይደን፣ “ያለጥርጥርም ረዥም ጉዞ የሚጠይቅ ነው” ሲሉ አክለዋል። የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚንስቴርም “ተጨማሪ የእሳት አደጋ ሰራተኞችን እና እገዛዎችን” ወደ ግዛቱ ለመላክ ቃል ገብቷል። የአደጋ ጊዜ ባለሥልጣናት መሰንበቻውን የታየውን ደረቅ የዓየር ሁኔታ ተንተርሰው በሎስ አንጀለስ አካባቢ የሰደድ እሳት ሊቀሰቀስ እንደሚችል ቢያስጠነቅቁም፣ የሰደድ እሳቱ መዛመት ግን ከተጠበቀውም የከፋ መሆኑ ተዘግቧል። «የሎስ አንጀለስ አውራጃ የእሳት አደጋ መከላከያ ለአንድ ወይም ለሁለት ዋና ዋና የሚሰኙ የቃጠሎ አደጋዎች መዘጋጀቱን ጠቁመው፣ የነፋሱ ማየል እና በአካባቢው ያለው ዝቅተኛ እርጥበት ተደማምረው ለደረሱት አራት ከፍተኛ ቃጠለዎች መዘጋጀቱን አዳጋች አድርገውታል» ሲሉ የአውራጃው የእሳት አደጋ መከላከያ አዛዥ አንተኒ ማሮን ትላንት ረቡዕ ተናግረዋል። ከሆሊዉድ እና አካባቢው በተጨማሪ በፓሲፊክ ፓሊሴድስ፣ አልታዴና፣ ፓሳዴና እና ሲልማር የተባሉት መንደሮች ቃጠሎው ከበረታባቸው አካባቢዎች ውስጥ ናቸው። በእስካሁኑ ቃጠሎ በርካታ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ሃብት የወደመ ሲሆን፤ እሳቱ አሁንም መዛመቱን አላቆመም። ማሮን ይህንን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት “እሳቱን ማጥፋት የተቻለበትን ሥፍራ መጠን የሚያረጋግጥ ስሌት እስካሁን የለንም” ብለዋል። የአካባቢውን የእሳት አደጋ ሰራተኞች ለመርዳት ቁጥራቸው ሁለት ሺህ የሚጠጋ የብሄራዊው ጥበቃ አባላት መሰማራታቸውም ታውቋል። በአውሎ ንፋስ እየተገፋ ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው የተዛመተው እሳት ከፍተኛ ጉዳት ባደረሰበት የፓሲፊክ ፓሊሴድስ አካባቢ የአደጋ ሰራተኞች እሳቱን ለማጥፋት ይጠቀሙባቸው የነበሩትን ውሃ ማጠራቀሚያዎች ማራቆቱም ተመልክቷል። በፓስፊክ ፓሊሴድስ የደረሰው ቃጠሎ በሎስ አንጀለስ ታሪክ እስከዛሬ ከታዩት ሁሉ በአውዳሚነቱ የከፋው ሲሆን፤ እስካሁን በተረጋገጠው ከ1 ሺሕ በላይ ሕንፃዎች ተቃጥለዋል። የፓሊሴድሱ ቃጠሎ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2008 ከደረሰው እና ‘የሳየሬ እሳት’ የሚል ስያሜ ከተሰጠው በከተማይቱ ሰሜናዊ ዳርቻ የሚገኙ 604 ሕንፃዎችን ካወደመውም ታሪካዊው የእሳት አደጋም የከፋ ነው። Read more