የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን የአዲሰ አበባ ጉብኝት
newsare.net
ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ለአንድ ቀን የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የነበሩት የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በዚኽ ወር መጀመሪያ በኢትዮጵያና በሶማየፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን የአዲሰ አበባ ጉብኝት
ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ለአንድ ቀን የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የነበሩት የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በዚኽ ወር መጀመሪያ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል በቱርክ ለተፈረመው የአንካራ ስምምነት ድጋፋቸውን ገልጸዋል ። ፕሬዝደንቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋራ በመኾን በሰጡት የጋራ መግለጫ የሁሉንም ሉዓላዊነት ከማክበር ጋራ የተያያዘው ስምምነት ሊደገፍ የሚገባው ነው ብለዋል። በቱርክ ፕሬዝደንት ረሽፕ ታይፕ ኤርዶዋን ሸምጋይነት የተካሄደውን ሦስተኛ ዙር ድርድር ተከትሎ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼኽ መሐሙድ እና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዲፕሎማሲያዊ ውዝግባቸውን ለመፍታትና አንዳቸው የሌላውን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ መስማማታቸው ይታወሳል ። ሁለቱ አገራት በመጭው የካቲት ወር በዝርዝር ጉዳይ ላይ ውይይት እንደሚጀምሩም ይጠበቃል። የሁለቱን ሀገራት ስምምነት ያደነቁት ፕሬዝደንት ማክሮን፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ እንዲሳካ ፈረንሳይ ባላት አቅም የበኩሏን ሚና መጫወት እንደምትፈልግ ጠቅሰዋል። በንግግር፣ በውይይት፣ ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ፣ ዓለምአቀፍ ሕጎችን እና ጎረቤት ሀገሮችን ባከበረ መልኩ መሠራት የሚችልበትን መንገድ ሀገራቸው ለማመቻቸት እንደምትፈልግ አመልክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ለማግኘት ያላትን ፍላጎት በተመለከተ ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ጋራ በዝርዝር መወያየታቸውን ተናግረዋል። ከዚህ አንጻር ማክሮንን ድጋፍ መጠየቃቸውና ፣ ፕሬዝደንቱም ጥያቄውን መቀበላቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። «መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ከፈረንሳይ እና ከፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በዚህ ረገድ የሚጨበጥ ውጤት የሚጠብቅ መኾኑን ከወዲሁ ልገልጽ እፈልጋለሁ» በማለትም ተናግረዋል ። በኢትዮጵያ የፌደራል መንግሥትና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል በፕሪቶሪያ የተፈረመው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም የሰላም ስምምነት በሁለቱ መሪዎች ውይይት ከተነሱት ነጥቦች አንዱ መኾኑን የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ገልጸዋል። ሀገራቸው ከዚህ ስምምነት አተገባበር አንጻር ድጋፍ ማድረግ እንደምትፈልግም ተናግረዋል። ሀገራቸው በሽግግር ፍትህ አማካኝነት የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እንደምትፈልግም አመልክተዋል። ፕሬዝዳንት ማክሮን በዛሬው የአዲስ አበባ ቆይታቸው፣ በመንግሥታቸው የገንዘብ ድጋፍ የታደሰውንና በአዲስ አበባ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመንግሥት ወይም ኢዮቤልዩ ቤተመንግሥት ጎብኝተዋል። ፈረንሳይ ለብሔራዊ ቤተመንግሥቱ እድሳት የ25 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ማድረጓንም ተናግረዋል። ቤተመንግሥቱ የቀዳማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ የብር ኢዮቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ በ1948 ዓ.ም. የተገነባ ነው።