የአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ
ባለፈው ሰኞ፣ ታኅሣሥ 28 ቀን 2017 ዓ.ም, ከዚኽ ዓለም በሞት የተለዩት አንጋፋው ፖለቲከኛ እንዲሁም የምጣኔ ሀብት እና የፋይናንስ ባለሞያ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ሥርዐተ ቀብር፣ እሑድ፣ ጥር 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በዐዲስ አበባ ከተማ ጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር ተፈጽሟል።
ከሥርዐተ ቀብራቸው አስቀድሞ፣ በዓድዋ ድል መታሰቢያ አዳራሽ በተከናወነው የአስከሬን ሽኝት መርሐ ግብር ላይ በተነበበው ዜና ሕይወት፣ አቶ ቡልቻ፥ ከአባታቸው አቶ ደመቅሳ ሰንበቶ እና ከአእናታቸው ወይዘሮ ናስሴ ሰርዶ፣ በምዕራብ ወለጋ ቦጅ በርመጅ አሌ ኤቢቻ በተባለ ስፍራ፣ በ1922 ዓ.ም. እንደተወለዱ ተገልጿል።
የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጊምቢ ከተማ ያጠናቀቁት አቶ ቡልቻ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአቃቂ እና በአርሲ ነገሌ ኩየራ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ሚስዮን ተምረዋል። በከፍተኛ ትምህርት ዝግጅታቸው፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከያኔው ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከአሜሪካው ሴርኪውዝ ማክስዌል ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ የመንግሥት ፋይናንስ ማግኘታቸውን የሕይወት ታሪካቸው አስፍሯል።
በአስከሬን ሽኝት ሥነ ሥርዓት ላይ ያገኘናቸው ፕሮፈሰር መረራ ጉዳና ስለ አቶ ቡልቻ ሲናገሩ፣ «ላመኑበት ዓላማ የኖሩ ሰው ናቸው፤» ብለዋል። አቶ ብሥራት ቡልቻ፣ የአቶ ቡልቻ ደመቅሳ የመጀመሪያ ልጅ ናቸው። አባታቸው በሕይወት ዘመናቸው፣ ሰው እንዲማር የሚያግዙና ለአገራቸው ሳይሰለቹ ሠርተው ያለፉ ናቸው፤ ብለዋል።
የአቶ ቡልቻ ባለቤት ወይዘሮ ሄለን ገብረ እግዚአብሔር በበኩላቸው፣ ባለቤታቸው «ሀገር ወዳድ፣ ለተቸገሩ የሚረዱ፣ ለቤተሰባቸው አርኣያ እና ተወዳጅ ሰው ነበሩ፤» ብለዋል።
በሽኝት ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የዐዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፣ አቶ ቡልቻ፣ አገራቸውንና ሕዝባቸውን በብቃትና በታማኝነት ያገለገሉ ሰው ናቸው፤ ብለዋል።
አቶ ቡልቻ፣ በኢትዮጵያ በዘመናዊ የግል ንግድ ባንኮች ምሥረታ ታሪክ ተጠቃሽ የኾነው የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ መሥራች እንደነበሩም፣ የወቅቱ የአዋሽ ባንክ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀሓይ ሽፈራው ተናግረዋል።
በንጉሣዊ መንግሥት ወቅት፣ በዓለም ባንክ ውስጥ ኢትዮጵያን ወክለው ለአራት ዓመታት በቦርድ አባልነት የሠሩት አቶ ቡልቻ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ውስጥ ተቀጥረው፣ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የልማት ፕሮግራም አምባሳደር በመኾን ዕድሜአቸው ለጡረታ እስከሚደርስ ድረስ አገልግለዋል።
የምጣኔ ሀብት እና የፋይናንስ ባለሞያው አቶ ቡልቻ፣ በቀደመው የፖለቲካ ሕይወታቸው፣ በዐፄ ኀይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት ማስፈጸሚያ ክፍል ውስጥ ረዳት ዳይሬክተር እና ዳይሬክተር ጀነራል በመጨረሻም ምክትል ሚኒስትር ኾነው አገልግለዋል።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን በማቋቋም እና በሊቀ መንበርነት በመምራት በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የበኩላቸውን ሚና ተጫውተዋል። በፓርቲው አባልነታቸው በአገራዊ ምርጫ ተወዳድረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመራጭ ኾነው ይሰጧቸው በነበሩ አስተያየቶች በብዙዎች ዘንድ ይታወሳሉ።
ዜና ዕረፍታቸውን ተከትሎ መልእክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ «አቶ ቡልቻ፣ በሚችሉት ኹሉ አገራቸውንና አፍሪካን ያገለገሉ፣ በአቋማቸው ጽኑ፣ ሕዝቦችን ለማቀራረብ የተጉ፣ እውነት ብለው ያመኑትን የትም እና መቼም ቢኾን የሚናገሩ ነበሩ፤» ብለዋል።
አንጋፋው ፖለቲከኛ እና የምጣኔ ሀብት እንዲሁም የፋይናንስ ባለሞያ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፣ ባለትዳር እና የስድስት ልጆች አባት ነበሩ።