በምዕራብ ዩክሬን በምትገኝ አንዲት መንደር ወንዶች አይታዩም
newsare.net
በምዕራብ ዩክሬን የምትገኘው ማኪቭ ከተማ፣ ብዙም ወንዶች አይታዩባትም። በርካቶች ሸሽተዋል ወይም ውጊያ ላይ ናቸው አልያም የሩሲያን ወረራ ለመመከት ሲፋለሙ ሕበምዕራብ ዩክሬን በምትገኝ አንዲት መንደር ወንዶች አይታዩም
በምዕራብ ዩክሬን የምትገኘው ማኪቭ ከተማ፣ ብዙም ወንዶች አይታዩባትም። በርካቶች ሸሽተዋል ወይም ውጊያ ላይ ናቸው አልያም የሩሲያን ወረራ ለመመከት ሲፋለሙ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ችግሩ በዩክሬን ባሉ በርካታ ከተሞች የሚታይ ነው። ጦርነቱ ወትሮውንም እየቀነሰ የመጣውን የሕዝብ ቁጥር አባብሶታል። ከጦር ሜዳ የቀሩትና ሕይወታቸውን መልሰው ለመገንባት የሚጥሩት የቀሩት ነዋሪዎች የዩክሬን የወደፊት ዕጣ ያሳስባቸዋል። በጦርነቱ ሕይወታቸውን ለሰጡ ወታደሮች መታሰቢያ በማኪቭ ዋናው አውራጎዳና ላይ ይታያል። ፎቶዎቹ መስዋቶቹ ደስተኛ በነበሩበት ጊዜ የተነሱት ነው። ከፎቷቸው በላይ “ክብር ለጀግኖች” የሚል ጽሁፍ ይታያል። ይህም ጦርነቱ የወለደው መፈክር ነው። ማኪቭ ከተማ የምትገኘው ከጦር አውድማው 600 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው። ጦርነት ያደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት እንደዚህች ከተማ የሚያሳዩ ጥቂት ናቸው። በከተማዋ ዕድሜያቸው ለውትድርና የደረሱ ወንዶች የሚገኙት በፎቶ ግራፍ ላይ ብቻ ነው። ወይም ደግሞ በከተማዋ የመቃብር ሥፍራ ነው። ሌሎቹ ወንዶች ለቀው ሄደዋል። “ተመልከት፣ ሰው የት ነው ያለው? ተደብቀዋል። ስጋት አድሮባቸዋል” ይላል ሹፌሩ አሌክስ ካሞቪስኪ። ከ30 ዓመታት በላይ በጀርመን ኖሯል። ወደ ትውልድ ከተማው የተመለሰው ሰነዱን ለማደስ ነበር። ጓደኞቹ እና ዘመዶቹ በከተማው የሉም። “አሳዛኝ ነው!” ሲልም አክሏል። ካሞቪስኪ እንደሚለው ለውጊያ ዕድሜያቸው የደርሱ በርካታ ወንዶች ወደ ግንባር እንዳይላኩ ወደ ገጠር ሄደው ተደብቀዋል። በማኪቭ ከተማ መንገዶች ላይ የተዘዋወረው የቪኦኤ ዘጋቢ ያገኛቸው አብዛኞቹ ሴቶች ናቸው። ወንዶች በመሄዳቸው ሕይወት ይበልጥ ከባድ እንደሆነ በርካታ ሴቶች ተናግረዋል። “እድሜዪ የገፋ ሴት ነኝ። ከሰባ ዓመቴ በላይ ነኝ። በእርግጥ ከልጆቻቸው ጋራ ለተተዉት ወጣት ሴቶች ይበልጥ ከባድ ነው። ወንድ ከቤት ካለ፣ ጠባቂ ብቻ ሳይሆን፣ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን የሚያቀርብም ነው። በሁሉም ጉዳይ ላይ ይረዳል። በተለይም በገንዘብ ጉዳይ” ብለዋል አስተማሪ የነበሩትና አሁን ጡረታ ላይ የሚገኙት ኒዮሊና ኮቫሌንኮ። በምዕራብ ዩክሬን የሚገኙ በርካታ ከተሞች ውስጥ የወንዶች አለመኖር ትልቅ ችግር ፈጥሯል። ማኪቭ ከተማ ግን ከጦርነቱም በፊት ቢሆንም የነበረው የሕዝብ ቁጥር መቀነስ ቀውስ ማሳያ ነች፡፡ መንግሥት እንደሚለው፣ የሕዝቡ ቁጥር በእ.አ.አ 1991 ከነበረው 52 ሚሊዮን፣ በእ.አ.አ 2024 ወደ 32 ሚሊዮን አቆልቁሏል። አንጀሊና ቦንዳል የከተማዋ ነዋሪና ተማሪ ነች።“ይህ እጅግ ያስፈራኛል። በርካታ ቤተሰቦች ሃገሪቱን ለቀው በመውጣታቸው በሃገሪቱ ሁሉም ነገር ተቀይሯል። ሃገሪቱም ተቀይራለች፡፡ ብዙ ሰዎች ለቀው ስለወጡ በጣም ያሳዝናል። ምንም ጓደኛ የለኝም። ቤተሰቤ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ከሃገር ወጥቷል። ያሳዝናል” ብላለች የከተማዋ ነዋሪና ተማሪ የሆነችው አንጀሊና ቦንዳል። አንጀሊና ቦንዳር ገና 15 ዓመቷ ነው። አንድ ጎረቤቷ በጦርነቱ ሕይወቱን አጥቷል። ሌሎቹ ጎረቤቶቿ አሁንም ውጊያ ላይ ናቸው። አብዛኞቹ ጓደኞቿ ለቀው የወጡት ገና በልጅነታቸው ነው። አንድ ቀን ዩክሬንን መልሶ የመገንባት ሥራው በእርሷ ትውልድ ላይ እንደሚወድቅ አውቃለች፡፡ ያንን ሃላፊነት ለመጋፈጥ ዝግጁ ስለመሆኗ ግን እርግጠኛ አይደለችም።